አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀ/ ስብከት ጽ/ቤት ዓመታዊ የሥራ ሪፖርቱን አቀረበ
በ38ኛው መደበኛ ሰባካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ3ኛው ቀን የስብሰባ ውሎ ላይ በርካታ አህጉረ ስብከት ዓመታዊ የሥራ ሪፖረትና ዕቅዳቸውን ካቀረቡ በኃላ ተጠሪነቱ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሆነውና በረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የሚመራው አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም ዓመታዊ የሥራ ሪፖርቱንና ዕቅዱን በጉባኤው ፊት አቅርቧል፡፡
ሀገረ ስብከቱ በተሰማራባቸው የተለያዩ የሥራና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ባደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገበ ከሪፖርቱ ተደምጧል፡፡ የበጀት ዓመት ገቢውም ካለፈው ዓመት አንጻር በእጅጉ የተሻለ መሆኑንም አስመስክሯል፡፡
የሀገረ ስብከቱን የሰው ኃይል አስተዳደር ለማዘመንና ዘመናዊ የሆኑ አሠራሮችን በጽህፈት ቤቱ ለመተግበር የሰው ኀይል አስተዳደር፣ የንብረትና ኃብት አስተዳደር፣ የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደርና የአላቂ ዕቃዎች አስተዳደር የሚባሉ ዘመናዊ አሠራሮችን በትግበራ ላይ ማዋሉንም ለጉባኤው ይፋ አድርጓል
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችም እንደነበሩ ሳያወሳ አላለፈም። እነዚህም መሠረታዊ ችግሮች ተብለው በሪፖርቱ የቀረቡት ከባለጉዳዮች መብዛት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ የሥራ ቅጥሮች፣ ከፍተኛ የሆኑ የዕድገትና የዝውውር ጥያቄዎች መብዛትና በቁጥራቸው የተወሰኑ የማይባሉ ባለጉዳዮች አቤቱታ ለመስማት የሚፈጀው ጊዜ መሆኑን አልካደም።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ያቀረበው ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት መሥራት ከሚጠበቅበት አንጻር ስንመለከተው እምብዛም አስደሳች አይደለም፤ ምክንያቱም ከሀ/ስብከቱ ታላቅነትና አንጋፋነት እንዲሁም በሀገሪቱ ርእሰ መዲና አዲስ አበባ ከመገኘቱ አንጻር በመሠረተ ልማትም ሆነ በስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እንዲሁም ዘመናዊ አሠራሮችን በመዘርጋትና ወጣቱን የሰው ኃይል አሳታፊ በማድረግ ለሌሎች አህጉረ ስብከቶች ምሳሌና አርአያ ሊሆን በተገባው ነበር።
ነገር ግን የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከማስቀጠል ይልቅ የባለ ጉዳዮችን ደብዳቤ ማስፈጸም ብቻ የዕለት ከዕለት ክንውኑ መሆኑን ተገንዝበናል።
ይህም የሚጠበቅበትን ያክል እንዳይሠራ፣ የስሙን ያክል እንዳይከብር እና ለሌሎችም ምሳሌ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖበታል ።
ስለሆነም የሀ/ስብከቱ የሚመለከታቸው አካላትና መላው የጽ/ቤቱ ሠራተኛ እነዚህን ችግሮች ተገንዝቦ ሀ/ስብከቱ አሁን እያስመዘገበው ካለው የፐርሰንት ከፍታ ይልቅ ለጽ/ቤቱ አማራጭ በሆኑ ቋሚ የገቢ ምንጮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጡና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠሉ ድርድር የሌለው መፍትሄ መሆኑን ተረድተን ሀ/ስብከቱ ካለበት ውስብስብ ችግር ልናላቅቀው ይገባል።
ይህ የሚሆኖው ግን ወጥና አሳታፊ የሆነ አሠራር በሀ/ስብከቱ ሲኖር ብቻ መሆኑን ተገንዝበን ወደ አንድነት መንፈስ ስንመጣ ነው። ያም እንደሚሆን ጽኑ ተስፋ አለን።
ይቀጥላል…..
የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል