አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ጽ/ቤት በ39ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ መደበኛ ጉባኤ ላይ ሪፖርቱንና እቅዱን አቀረበ
ተጠሪነቱ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሆነው ታላቁና አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዛሬው እለት በቀን 05/2013ዓ.ም ሪፖርቱንና እቅዱን አቅርቧል፡፡
ሪፖርቱን ያቀረቡት ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ ሲሆኑ ንግግራቸውንም “አቤቱ አንድነታችንን በሰላም ባርክ ጠብቅ፣ከዓለም ይልቅ የወደዱህን ቅዱሳን ካህናትህን፣ምዕመናንንህን በአንድነት ባርክ፣እኛም የምንሠራውን የአንድነታችንን ሥራም ተቀበልልን” በሚለው በቅዱስ ያሬድ ድርሰት ተነስተው አንድነት የቤተክርስቲያን ዋነኛ መገለጫና በአስተዳደር ሂደት ለሚኖሩ ስኬቶች ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡት ሪፖርት በኅብረት የተገኘ የሥራ ፍሬ መሆኑን በመግለጽ፣የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ርእሰ ከተማ በአዲስ አበባ መገኘቱ፣በመንፈሳዊና በአስኳላ ትምህርት የበለጸጉ ሠራተኞችን መያዙ፣የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት መሆኑ አዎንታዊ የሆነ መልካም አድሎች ያሉበት ቢሆንም በአንጻሩ ደግሞ ፈታኝ ተግዳሮቶች ያሉበት ተቋም መሆኑንም በሪፖርቱ አስደምጠዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም ለሀገረ ስብከቱ ዐበይት ተግዳሮቶች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል፡ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት፣ለሀገረ ስብከቱ ቋሚ መተዳደሪያ ደንብ አለመኖር፣ከሀገረ ስብከቱ እስከ አጥቢያ ድረስ የተናበበ የቸግር አፈታትና መፍትሔ ሰጪነት ክህሎት አለመዳበር፣ከዕለት ወደ ዕለት የሥራ ፈላጊ ቁጥር መብዛት፣በተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ካህነትና ምእመናን በግፍ መገዳላቸው፣በእኔነት ስሜት ከመሥራት ይልቅ በነገ አልኖርም አስተሳሰብ የሚከወኑ ሥራዎች ተካተዋል፡፡
ይሁንና ተግዳሪቶቹን በመጋፈጥ ባለፈው የበጀት ዓመት አመርቂና መልካም የሆኑ ሥራዎች የተከወኑ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፡ ለተቋማዊ ሥራዎች ትኩረት በመስጠት የጽሑፍ መመረያዎችን በባለሙያ በማዘጋጀት፣የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንብ በመቅረጽ፣በይዞታና በመሰል ጉዳዮች ዙርያ ከመንግስት ተቋማት ጋር ምክክር በማድረግ፣አብያተክርስቲያናት ባለቸው የመሬት ሀብት በፕሮጀክት የተደገፈ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ወደ ልማት ዘርፍ ለመግባት የሕግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት፣ከፍተኛ መንፈሳዊ እሴት ያላቸውና በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ገዳማትን ለመጠበቅና ለማበልጸግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ሥራዎች መሰራታቸውን ክቡር ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላላን ገቢን በተመለከተ ገዳማትና አድባራት በበጀት ዓመቱ የሰበሰቡት ጠቅላላ ገቢ 1,618,204,923.85 ሲሆን ከ20 በመቶ እና ከልማት የተገኘ ጠቅላላ ገቢ ብር 327,173,307.56 ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት 65 በመቶ ድርሻ ብር 212,662,649.91 ገቢ ሆኗል፡፡በዚህም ካለፈው ዓመት በብልጫ 13,591,173.77 ገቢ ማድረግ መቻሉን ከሪፖርቱ ተሰምቷል፡፡
ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ ፦ ከምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ ነው።