ቲቪ ኬር ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት ለአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት ተወካዮች የቲቪ በሽታን አስመልክቶ ለአንድ ቀን የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

0848

ሰኔ 14 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ በሀገረ ስብከቱ ሥር ለሚገኙ የአድባራት እና ገዳማት ተወካዮች ለአንድ ቀን የቆየ  የግንዛቤ መስጨበጫ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በስልጠናው መጀመሪያ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ስልጠናውን በጸሎት በከፈቱበት ወቅት ለአድባራት እና ገዳመት ተወካዮች ባስተላለፉት መልእክት ቤተክርስቲያናችን የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማስፋፋት ጎን የምዕመናን ጤና እንዲጠበቅ ትሠራለች፡፡ ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍስን በሽታ ብቻ ሳይሆን የሥጋንም በሽታ ፈውሷል፡፡ ስለዚህ በዘመናችን እንደወረርሽኝ ሕዝባችንን እያጠፋ ያለውን የቲቪ በሽታን ለመከላከል የአድባራት እና ገዳማት አገልጋዮች በርትተው ማስታር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም አርቲስት ፈቃዱ ተክለ ማርያም ሰው የተወሰነለትን ዕድሜ በጤና ይኖር ዘንድ ቲቪን መከላከል እንደሚገባው እና ማንም ሰው በቲቪ በሽታ መሞት እንደሌለበት በመጥቀስ ለሰልጣኞቹ መልእከት  አስተላልፈዋል፡፡
በማያያዝም ዶክተር ኃይሉበዛ ዓለሙ የቲቪን በሽታ ምንነት አስመልክተው ሳይንሳዊውን ትምህርት ከመንፈሳዊ መልእክት ጋር እያዛመዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጡ  በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ለኩሉ ዘሥጋ ወለኩሉ ዘነፍስ የሚለው ቃል ቤተክርስቲያናችን የነፍስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሥጋም ጉዳይ ያሳስባታል፡፡
ነቢዩ ዳዊት አቤቱ በሲኦል ማን ያመሰግንኻል እንዳለው እግዚአብሔርን የሚአመሰግነው በህይወት ያለ ሥጋ ነው፡፡ ቲቪ የሚባለው በሽታ በተለምዶ ነቀርሳ፣ የብርድ በሽታ በመባል ይጠራል እንጂ ቲቪ ነቀርሳም የብርድ በሽታም አይደለም፡፡ ቲቪ በቆሻሻ ምክንያት ሊመጣ እና ከአንዱ አፍ በሚወጣው አየር ወደ ሌላው አፍ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ ቆሻሻን በመሬት እንዲቀብሩት ለሕዝቡ ንገር በማለት አዝዞአል፡፡

08490

ስለዚህ እኛም ቆሻሻን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ የቲቪ ቫይረስ ቀስ በቀስ የሚአድግ እና በሰው ውስጥ ለብዙ ጊዜ ተደብቆ የሚኖር በሽታ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የቲቪ ቫክቴሪያ በዓለም ላይ በርካታ ሰዎችን አጥቅቶአል፡፡ ኢትዮጵያ በቲቪ በሽታ በዓለም 8ኛውን ደረጃ ይዛለች፤ የቲቪ ባክቴሪያ በአብዛኛው የሚኖረው በሳንባ ውስጥ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በሽተኛውንም ጤነኛውንም ትቀበላለች፡፡
ስለዚህ ከአገልግሎት በኋላ መስኮቶች ተከፍተው አየር እንዲገባ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለሆነም በአየር ላይ የተንሳፈፉ ቫክቴሪያዎች ይጠፋሉ፡፡ ቤተክርስቲያን የመስኮት ችግር የለባትምና፡፡ የቲቪ ባክቴሪያ የሰውን ልጅ ካዳከመ በኋላ የዘር ፍሬ እንዳይኖረው እና መካን እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ አእምሮንም ሊያስት ይችላል፡፡
የቲቪ በሽታ ምልክቶች
ቫክቴሪያው ሲራባ ሳል ይከሰታል፤ ደም የተቀላቀለ አክታ ይፈጥራል፣ ትኩሳት ይከሠታል፣ በመኝታ ጊዜ በላብ መጠመቅ ይሆናል፣ ክብደት ይቀንሳል፣ የምግብ ፍላጎት ይቀንሳል፣ ውጋት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ በሰውነት ላይ ዕጢ መውጣት፤ 
ይሁን እንጂ የቲቪ በሽታ በህክምና ሙሉ በሙሉ ይድናል፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱን በጥንቃቄ እና ባለማቋረጥ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ መድኃኒት ከእግዚአብሔር የሚገኝ ስለሆነ በጸበል ጊዜ መድኃኒት ማቋረጥ አይገባም፡፡ መድኃኒት አቋርጡ የሚሉ አስተማሪዎች ካሉ ልንታገላቸው ይገባል፡፡ አንድም ሰው በቲቪ በሽታ ሊሞት አይገባም፡፡
በመቀጠልም ሁለተኛው ትምህርት አቅራቢ ዶክተር ሐጎስ ገ/መድኅን በቅርብ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የቲቪ አይነት እና መድኃኒቱን የተላመደ ቲቪ እየተስፋፋ መሆኑን፤ በዓለም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መድኃኒቱን በተለመደ ቲቪ የሰው ዘሮች እየተጠቁ መሆኑን መድኃኒቱን የተላመደ ቲቪ ካጠቃቸው ቻይና፣ ብራዚል፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ ሀገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆንዋን እና መድኃኒቱን የተላመደ ቲቪ በጣም አሳሳቢ መሆኑን የሚሰጠውም መድኃኒት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚደርስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም የውይይቱ ተሳታሪዎች በርካታ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን በማቅረብ ጥሩ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ {flike}{plusone}