‹‹ተዘከሩ መዋዕለ ዘቀዲሙ የቀደመውን ዘመን አስቡ›› (ዕብ. 10÷32)
ኢትዮጵያ ሀገራችን የብሉይ ኪዳን ሥርዐትን መቀበሏ፥ ከነገደ እስራኤል ለመመሳሰል ብላ ወይም የልማድ ተጽዕኖ ደርሶባት ሳይሆን፤ ከጥንት ጀምሮ በሕገ ልቡና ከነ መልከጼዴቅ፥ ከነዮቶር የተማረችው እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ቶራህ የሚባለውን የአይሁድ እምነት መጽሐፍ ቅድመ ክርስትና ትጠቀምበት ነበር፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው ክፍለ ዘመን በሰሜን አፍሪካ ብሉይ ኪዳን ወደ ጽርእ ቋንቋ ተተርጒሞ የመላው ዓለም ሀብት ሁኖ ስለነበር፥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በኢትዮጵያ ምድር መኖራቸው የሚያጠያይቅ ካለመሆኑም ባሻገር፥ ዋነኛ ተጠቃሽ ማስረጃችን የልማድ ተሳላሚ ወይም ሀገር ጎብኚ ሳይሆን ኦሪትን ከነመጽሐፉ የተቀበለውንና የሚያምነውን በተግባር ያረጋገጠው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው።ይህ ሰው የአይሁድ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን በዓመት ሦስት ጊዜያት ማለትም በበዓለ ፋሲካ፥ በበዓለ ሰዊትና በበዓለ መጸለት ወይም በዳስ በዓል ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ለእግዚአብሔር መስገድ ነበረበት። ፋሲካና የእሸት በዓል በኀምሳ ቀናት ልዩነት ሲከበሩ፥ ወቅቱም ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፤ የዳስ በዓል ግን መስከረም መጨረሻ አካባቢ የሚውል ነው። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሥልጣኑና ሀብቱ ያልሰጠውን ደስታ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገኝቶለት ነበርና፤ ይህን ሃይማኖታዊ ግዴታ ለመወጣት የሲና በረሓን አቋርጦ፥ ሁለት ድንበር የሆነውን የኑቢያንና የግብጽን ግዛት አልፎ መንፈቅ ድረስ ሊፈጅ የሚችለውን መንገድ በመጓዝ ለሃይማኖቱ መሥዋዕትነት ይከፍል ነበር።
ጃንደረባው ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት በጆሮንድ ወይም የገንዘብ ሚኒስትር በመሆኑ፥ አማኝ የሆነ ወደ የትኛውም የሥልጣን ከፍታ ላይ ቢወጣ እምነቱን አክብሮ መያዝ እንደአለበት ሕይወቱ አስተማሪ ይሆናል። ባለሥልጣናት በእግዚአብሔር ጸጋ ዐርፈው፥ ሰንበትንም በዝማሬና በጸሎት አሳልፈው ሰኞ ወደ ሥራ ቢገቡ የቀና ፍርድና አመራር ይሰጣሉና፤ ዛሬም በሥጋ የሚያገለግሉንን መሪዎች በነፍስ በማገልገል የሚያስቀድሱና የሚቈርቡ ባለሥልጣናትን ለማየት ሰፊ ሥራ መሥራት ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡
ጃንደረባው ለእግዚአብሔር ሰግዶ ሲመለስ በሠረገላው ላይ ሁኖ ከነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ስለ ነገረ መስቀል የሚተርከውን የትንቢት ክፍል ምዕራፍ 53ን በማንበብ ላይ ሳለ፥ እግዚአብሔር አምላክ የትንቢት ተስፋው ከወራት በፊት በተከናወነው የፍጻሜው ደስታ ይተካለት ዘንድ ቅዱስ ፊልጶስን ላከለት (የሐዋ. ሥራ 8÷26)። ፊልጶስም ወደ ሠረገላው ቀርቦ የሚያነብበውን በመስማት “በውኑ የምታነብበውን ታስተውለዋለህን?” በማለት ጠየቀው፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ግን ትሑት ሆኖ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” አለ። ቀደምት ባለሥልጣናት የክህነት ክብር እንደሚበልጥ ስለሚያውቁ የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ያከብሩ፥ ከዙፋናቸው አጠገብም ያስቀምጡ ነበርና፥ ቅዱስ ፊልጶስን በሠረገላው ላይ እንዲቀመጥ ጋብዞ መጠየቅ ጀመረ። ያመነውን በትክክል ይዞ ያልተረዳውን በትሕትና የሚጠይቅ ለመልሱ ቅርብ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ኦሪትን በትክክል ተከትሏልና ወደ ወንጌል ደረሰ።
በቅዱስ ፊልጶስ ስብከት ይህ ሰው ምሥጢረ ሥጋዌን ተረድቶ በራሱ ጥያቄ ልጠመቅ አለ፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እኔ አምናለሁ” በማለትም እምነቱን በአዋጅ መሰከረ። ጃንደረባው ታማኝ የነበረ የቤተ መንግሥትና የንግሥቲቱ ቅርብ ሰው እንደመሆኑ በዚህ ሥልጣኑ ከሠረገላ ነጂዎች ጀምሮ በብዙ ሠራዊት ተከብቦ እንደ ተጓዘ እርግጠኞች ነን። እርሱ ሲያምንና ሲጠመቅ አብረውት የነበሩትም ተጠምቀው፥ ዜና ወንጌልን ይዘው ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ወንጌል ሰማርያ ከመድረሱ በፊት ክርስትና በ34 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ገባ ።
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የየራሳቸው የክርስትና መዲና እንዳላቸው ሁሉ፤ አኵስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መዲና፥ የሀገር ታሪክና የሃይማኖት ሥሩ የሚገኝባት ሥፍራ ናት። ቀዳማዊ ምኒልክ አባቱን ጠይቆ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ካህናተ ኦሪትንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ በመምጣቱ በአኵስም ላይ የብሉይ ኪዳን ማእከል የነበረችው ታቦተ ጽዮን አለች፤ የሐዲስ ኪዳን የሕይወት ማእድ የሆነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም አለ። አይሁድ ኦሪትን ቢቀበሉ ሐዲስ ኪዳንን አልተቀበሉም፤ አሕዛብ ሐዲስ ኪዳንን ቢቀበሉ ብሉይ ኪዳንን አያውቁትም፤ ኢትዮጵያ ግን ከኦሪት ወደ ሐዲስ ኪዳን በመምጣት የሁለቱም ኪዳናት ባለቤት ሁናለች፤ ቤተ ክርስቲያናችንም ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ ይዛ ትገኛለች ።
በባቢሎን ምርኮ መቅደሱ ከመፍረሱ በፊት እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ወደ ኢትዮጵያ ምድር እንዲመጣ አደረገ፤ በሮማውያንም በ70 ዓ. ም. ዘሩባቤል የሠራው መቅደስ በመፍረሱ እስራኤላውያን እስከ ዛሬ ድረስ መቅደስ አልባ ናቸው። በኢትዮጵያ ግን ኦሪትም ሐዲስም ሳይናወጥ፥ ወራሪም ሳያጠፋው ጸንቶ ይኖራል፤ አልጠፋም ማለት ግን እሳት አልነበረም ማለት አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበሉ የአፍሪካ ሀገራት ግብጽ፥ ሱዳን ወይም ኑቢያ፥ አልጄሪያ፥ ሊብያ፥ ቱኒዝያ ዛሬ የክርስትና አቅም ተዳክሞባቸው ይታያሉ። በኢትዮጵያ ግን ፈተና የበዛበት ቢሆንም ክርስትና ጸንቶና ሁል ጊዜ ትኩስ ሆኖ መገኘቱ እንደ ታሪክ የምንማረው፥ እንደ ቅርስ የምንጐበኘው፥ እንደ ባህልም የምንይዘው ብቻ ሳይሆን ዛሬም ጣዕመ ዓለምን የናቁ ክርስቲያኖችን እያፈራ ያለ ነው ።
ርእስ አድርገን በተነሣንበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኀይለ ቃል እየተመራን የቀደመው የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር አመሠራረትን ስናስታውስ፥ ቀዳማዊ ታዜር ወይም አልዓሜዳ በሚያስተዳድርበት ዘመን ከሶርያ ጢሮስ አካባቢ ተነሥቶ ወደ ሕንድ በመርከብ የሚጓዝ፥ ሜሮጵዮስ የተባለ ግሪካዊ ነጋዴ የጫነው ምግብና ውኃ አልቆበት ወደ ቀይ ባሕር ወደብ ሲጠጋ በአካባቢው የነበሩ ጠባቆች ሜሮጵዮስንና ሌሎች ሰዎችን ገድለው ሁለት ወጣት ልጆቹን ለባሕረ ነጋሽ ያስረክባሉ፤ ባሕረ ነጋሹም ለቀዳማዊ ታዜር ያስረክባቸዋል ። እነዚህ ወጣቶችም ብልህ ስለነበሩና በንጉሡም ዘንድ ታማኝነትን ስላገኙ ኤድስዮስ ጠጅ አሳላፊ ፍሬምናጦስ የግምጃ ቤት ኀላፊና የጽሕፈት ሚኒስትር ሁነው ተሹመው ንጉሡ ብዙ ሳይቆይ ዐረፈ። መንግሥቱንም የሚረከቡት ኢዛናና ሳይዛና ሕፃናት በመሆናቸው እናቲቱ ንግሥት ሶፍያ ሞግዚት ሁና፥ እነ ፍሬምናጦስ አስተማሪ ሆነው በኑዛዜው መሠረት ቆይተዋል።
እግዚአብሔር ነገርን ሁሉ ለበጎ እንዲያደርግ ሐዋርያው ተናግሯልና፥ አባታቸው በመገደሉ ምክንያት እነዚህ ወጣቶች ለኢትዮጵያ በረከት ሆኑ፤ በመርከቡ ውስጥ ላሉ ሁሉ የጨከኑ ገዳዮች እነዚህን ወጣቶች በምሕረት ማለፋቸውም ተኣምር ነው። እግዚአብሔር ከሞት አስመልጦ ለነገሥት ሥርዐተ መንግሥትን አስተማሪ፥ ለሕዝቡ የወንጌል ሰባኪ፥ ለሀገራችንም በረከት አደረጋቸው። በዘመኑ የነበሩት የሀገራችን ሰዎችም በቆዳቸው ቀለም ሳይበረግጉ ወንጌለ መንግሥትን ለመስማት መጨከናቸውም አስደናቂ ነው።
በእርግጥ ጥንታዊው የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ከውጭ ሀገራት ጋር ሰፊ ግንኙነት ስለነበረው ወደ ሀገሩ የሚመጡትን እንግዶች በርኅራኄ ተቀብሎ የሀገሩን ቋንቋና ባህል ያጠኑ ዘንድ በአኵስም ቤተ ቀጢን ተብላ በምትጠራ የእንግዳ ማረፊያ ትምህርት ይሰጥ ነበር። ይህም የሕዝቡ ባህልና የእምነት ክብር እንዳይገሰስ፥ እንግዶቹም ቋንቋ ባለማወቅ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው የሚያደርግ ታላቅ ጥበብ ነው ።
በእኛም ዘመን የውጭ እንግዶችን ስንቀበል ባህሉንና ቋንቋውን ብናስጠና ከመበረዝና እንግዶችም ሀገሩን ከመዳፈር እንዲታቀቡ ከማስቻሉ ጐን ለጐን ስለ ኢትዮጵያ መንገደኛ የነገራቸውን ይዘው ያንን ታሪክ እያሉ እንዳይጽፉ ሃይማኖትን፥ ታሪክንና ባህልን፥ ምክንያት ያለውንም አኗኗር በዐዋቂዎች ለማስረዳት የተሻለ ነው፤ መንገደኛው ሁሉ ታሪክ አዋቂ አይደለምና። የእኛ ታሪክ ተብሎ በሌሎች የተጻፈልንም በአብዛኛው ሊቃውንት ያልተጠየቁበት ነውና ቤተ ቀጢን የእንግዶች ማረፊያና ማስተማሪያ በዚህ ዘመን ልትታሰብ ይገባታል።
የወንጌል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ፍሬምናጦስ ወደ ሀገሩ ሲመለስ፥ በአኵስም የተጀመረው የወንጌል ጒዞ ፍሬ እንዲያፈራና እንዲስፋፋ ጳጳስ ይላክ ዘንድ ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጠይቆ ለማለፍ ወደ ግብጽ ሄደ። በዚያም አባቶች የኒቅያ ጉባኤን ለመሳተፍ ተሰባስበው ነበርና ሲመለሱ ወደ መንበረ ማርቆስ ቀርቦ፦ በኢትዮጵያ የወንጌሉን ማበብ፥ ቤተ መንግሥቱም ለክርስትና ያለውን ፍቅር ካስረዳ በኋላ፤ የሚባርክና የሚሾም፥ የሚቀድስም ጳጳስ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ሐሳቡን አካፍሎ ለመሄድ ሲነሣ፥ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ፦ ‘የሀገሩን ባህልና ቋንቋ የሚያውቅ ካንተ የተሻለ ሰው አናገኝም’ በማለት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ አድርጎ ሾሞ ወደ ወደ ኢትዮጵያ መለሰው።
ኢትዮጵያውያንም ቀድሞ በሰባኪነት ያገለግላቸው የነበረው ፍሬምናጦስ ጳጳስ ሁኖ ሲመጣ በታላቅ ክብር ተቀብለውታል፤ በአባትነቱም አምነው አባ፥ በሰበከው ወንጌል ተስበው ሰላማ፥ ባገኙት መንፈሳዊ ዕውቀት ተደስተው ከሣቴ ብርሃን በማለት ጠርተውታል። አባ ሰላማ የደከመለት ወንጌል ሥራ መሥራቱን የምናየው ፍጹም ሕይወታቸው የተለወጠው ነገሥትና አዝማደ መንግሥት ስማቸው በመቀየሩ ነው። ኢዛና አብርሀ ወይም አበራ ተባለ፤ ይህ ብርሃንም የወንጌል ብርሃን ነው። ሳይዛና ደግሞ አጽብሐ ወይንም አነጋ ተባለ፤ በእግዚአብሔር ቃል የሚገኘውን የጨለማን ማለፍና የብርሃንን መምጣት የሚገልጥ ስያሜ ነው ። የሁለቱ ልጆች እናት የሆነችው ንግሥት ሶፍያም አሕየዋ የሚል ስም አግኝታለች። ይህ ሁሉ የአባ ሰላማ ድካም ሥራ እንደ ሠራ የሚያሳይ ሲሆን ከሁሉ በላይ አብርሀና አጽብሐ የተባሉት ወንድማማቾች በአንድነት በሰላም መንገሣቸው አስደናቂ ነው ።
በኋላ ዘመን ታላቅ የነገሠ ከሆነ ታናናሽ ወንድሞቹ፥ ታናሽ የነገሠ ከሆነ ታላላቅ ወንድሞቹ እንዳይቀናቀኑትና ሕዝብ የንጉሥነት ዘር ካላቸው መካከል አንዱን ነጥቆ እንዳያነግሥ ስለሚፈራ በአምባ ማርያም ላይ ማሰር የተለመደ ነበር። አብርሀና አጽብሐ ግን በወንጌል ዓለምንና ኃላፊውን (ሥጋዊውን) ሥልጣን ንቀው በአንድነት ነግሠው የቅድስናን ማዕረግን ያገኙ የኢትዮጵያ ነገሥት ናቸው። በሥጋዊው ዓለም የማይቻለው በመንፈሳዊው ዓለም ይቻላልና፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከሊቀ ጵጵስናቸው ጀምሮ ጥረት ሲያደርጉበት የነበረው ሐሳብ በፈቃደ እግዚአብሔር ሲፈጸም፥ ‹‹ወንድሜ እንኳን ደኅና መጡ›› ብለው በክብር በተቀበሏቸው ዐራተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሩቅ ዘመን ታሪክ በቅዱስ አባታችን ዘመነ ፓትርያርክነት ተደግሞ ለማየት መታደላችንም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ካከናወኗቸው ታላላቅ ተግባራት መካከል፥ የመጀመሪያው፦ አንድ ካህን ለዐሥራ ሁለት ቤተሰብ መምህርና አባት እንዲሆን የሚያደርገው የአበ ነፍስ ሥርዐት ነው። ያ ካህን ሕፃናቱን ፊደል በማስቈጠር፥ ቤተሰቡን በማጽናናት፥ ከቤተሰቡ እንደ አንድ አካል ሁኖ ውሳኔ በማሳለፍ፥ ከልደት እስከ ሞትና እስከ ተዝካር ያንን ቤተሰብ የሚራዳ ነው። በመሆኑም የዚህ ዓለም ኑሮ ያለ አማካሪ፥ የነፍስ ጒዞ ያለ ሰባኪ፥ የትውልድ ሕንጸትም ያለ እረኛ አይሆንምና፥ በዛሬው ዓለም የቤተሰብ ሐኪም፥ አማካሪ እየተባለ የሚጠራውን ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ 1600 ዓመታት በፊት ጀምራው እናገኛለን ።
ሌላው የአበ ልጅ ሥርዐት ነው፤ በዐርባና በሰማንያ ቀን ተጠምቀው ከሥላሴ ለሚወለዱት ሕፃናት የክርስትና አባትና እናት ይሠየምላቸዋል። ዐላማዎቹም፦ የመጀመሪያው፤ ሳያውቅ የተጠመቀውን ሕፃን ነገረ ሃይማኖትን እያስተማሩ እንዲያሳድጉ ነው፤ ስለ እርሱም ተገብተው “አአምን በክርስቶስ አምላኪየ እክሕደከ ሰይጣን” በማለት እምነታቸውን ያውጃሉ። ሁለተኛው፤ የሰው ልጅ በተለያየ ነገር ካልተሳሰረ መበተኑ እርግጥ ነውና፥ መንፈሳዊ ዝምድናን ለማስፋፋት ነው። ሦስተኛው፤ ወላጆቹ ቢሞቱ ልጁ ያለ አሳዳጊ ቀርቶ ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይመጣ፥ ትውልድም እንዳይጐዳ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የማኅበራዊ ኑሮ ጠባቂ እንደመሆኗ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ኑሮ የልብ ምቱ ያለው ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።
ከአባ ሰላማ በፊት የነበረው የሳባ ፊደል አንድ ድምፅ ብቻ የሚሰጥ ሆኖ ከካዕብ እስከ ሳብዕ ስላልነበሩት፥ አባ ሰላማ ከሊቃውንት ጋር ሁነው ድምፅ ሰጪ ፊደላትን አዘጋጅተዋል፤ ይህንን ያደረጉበት ዐላማ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመተርጐም ከመሆኑም በላይ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት መጻሕፍት ፍቅር ፊደል እስከ መፍጠር ያደረሳት እንደሆነ እንረዳለን። ዛሬ በአፍሪካ ያለው ብቸኛው የእኛ ፊደል ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችው ሀብት፤ ኢትዮጵያውያንም በጎ ነገር ሲያገኙ ወደ ሀገር ቋንቋ በመተርጐምና ኢትዮጵያዊ መልክ በመስጠት የመጠቀማቸው ክሂሎትን የሚያሳይ ነው።
አባ ሰላማ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከግሪክ፥ ከሱርስት፥ ከዐረብ ቋንቋዎች ወደ ግእዝ ከመተርጐም በተጨማሪ ሊቀ ካህናቱ እንበረምን “ሕዝበ ቀድስ” ብለው ረዳት ጳጳስ አድርገው በመሾም፤ በመላው ኢትዮጵያ አብረው ዞረው ወንጌልን ሰብከዋል። “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” በማለትም የመጀመሪያዋን ማኅበር በአኵስም መሥርተዋል። ማኅበረ ጽዮን ምድራዊት የአብርሃምን የሥጋ ዘር ብቻ ስትቀበል ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ግን ሁሉን ሰብሳቢ መሆኗን የሚገልጥ ነው ። በአኵስምም ከአብርሀና አጽብሐ ጋር በመሆን በአቡነ ሰላማ ዘመነ ሢመት ባለ 12 መቅደስ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአባ ሰላማ የቅዱስነት ማዕረግ ሰጥታ በዓለ ዕረፍታቸውን ሐምሌ 26 ቀን ስታከብር የግሪክና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያንም ቅድስናቸውን ዕውቅና ሰጥተው ይቀበሉታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከመጀመሪያው ጳጳስ ከአባ ሰላማ ጀምሮ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን የተላኩ 111 ጳጳሳት የመሯት ሲሆን፤ የሚላኩት አባቶች ዐረፍተ ዘመን ሲገታቸው ወይም በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ ሌላ አባት ለማስመጣት ከብዙ ደጅ ጥናት ጋር የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ሀብት በእጅ መንሻነት እየተላከ መባከኑ፤ የሚመጡት አባቶች የሀገሩን ባህልና ቋንቋ ባለማወቃቸው ምክንያት ሐዋርያዊ አገልግሎት መስተጓጐሉ፤ ኢአማንያን ጭምር የሐሰት ደብዳቤ በመያዝ በስመ ጳጳስ ወደ
ኢትዮጵያ ገብተው በደል መፈጸማቸው፤ በአባት እጦት ምክንያት መስፈርት የሌለው ሢመተ ክህነት መስፋፋቱ፤ አንዳንድ ግብጻውያን አባቶች በሀገር አስተዳደር ውስጥ በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ ለማሳደር ይዘውት ይመጡ የነበረው ተልእኮና የመሳሰሉት ምክንያቶች መንፈሳዊ ቁጭት የፈጠሩባቸው በየዘመናቱ የተነሡ የኢትዮጵያ መሪዎች፥ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ባደረጉት በሳል ውይይት እንዲሁም በከፈሉት ዋጋ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው ተሠይመዋል፡፡
ከእርሳቸው በመቀጠልም፡-
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፥ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት፤
ሐዋርያዊት የሆነች የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበርን በየተራ ተረክበው ከእግዚአብሔር በተቀበሉት የአባትነት ጸጋ መርተዋል፤ ሀልዎተ እግዚአብሔርን የሚቃወም ሥርዐት በምድራችን ላይ በሰፈነበት ጊዜ ዋጋ እየከፈሉ በጥበብ አሻግረዋል፤ ምቹ ሁኔታ በተፈጠረበት ወቅትም ክብሯን በልዕልና ገልጠው ለመላው ዓለም በሞገስና በግርማ የምትታይበትን፥ ለአፍሪካውያንም አርኣያ የምትሆንበትን ዕድል ፈጥረዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ቅዱሱን መንበር ከተረከቡበት ዕለት አንሥቶም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማጽናት፤ ክብሯ እንዲጠበቅ፥ ልጆቿም በነፃነት እንዲኖሩ አመራር በመስጠት፤ ይልቁንም የሁሉ መሠረት ሰላም በመሆኑ ክርስትና ድንበር የለውምና ለሀገራችን ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን የእስራኤል፥ የፍልስጥኤም፥ የሩሲያና የዩክሬን ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም እንዲያገኙ፤ በስደት ዓለም ላይ ተጨማሪ ስደት የገጠማቸው ወገኖች መጠለያ ሥፍራ እንዳይቸገሩ፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለዓለም ታላቅ ብርሃንን ያበሠረው ክርስትናን እንዲዳከም ብሎም እንዲጠፋ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ከክፉ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤ በዓለም ደረጃ የተያዙ የጦርነት ቀጠሮዎች ተሰርዘው ችግረኞች የምግብና የደኅንነት ዋስትና እንዲያገኙ በመምከር፥ በማስተማር፥ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ፥ እንዲሁም ለግፉዓን ድምፅ በመሆን አባታዊ የሰላም ጥሪያቸውን ለሚመለከተው ሁሉ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ማጠቃለያ
በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት ያገኘንበትን፥ አባቶቻችንም ስለ ስሙ መከራን እየታገሡ ክርስቶስን የመሰሉበትን ዘመን ማሰብ፤ ታላቅ ዋጋ የሚገኝበትን መታመን ባለመጣልም የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየፈጸምን የተሰጠውን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቅ እንደሚገባን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ያስገነዝባል (ዕብ. 10÷32)፡፡ ስለሆነም የቀደመውን ማሰብ ያለንበትን ዘመን የሚያሳምር፥ የመኖርን ተስፋ የሚያለመልም ከመሆኑ ባሻገር መነሻን አለመዘንጋት በተሟላ ክብር ወደነገ የሚያሸጋግር ጠንካራ ድልድይ ነውና ‹‹ሥርወ ሃይማኖት፤ ሥርወ ታሪክ›› ከሚገኝባት የሃይማኖት መዲናችን አኵስም ጋር ያጋጠመንን መራራቅ በመቀራረብ እንዲታረም፤ የተዛነፉ የታሪክ ክፍሎች በይቅርታ እንዲስተካከሉ፤ በልዩ ልዩ ምክንያት አዝነውና ተገልለው በየቤታቸው የተቀመጡ ሊቃውንትና መምህራን በፍቅር ተሰባስበው ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ዕውቀትና ዐቅም መጠቀም ትችል ዘንድ ከልባችን ተነሥተን በእውነት ለመሥራት የሚያስፈልገን መንፈሳዊ ጥብዐት፥ ዛሬ የቅዱስ አባታችንን 13ኛ ዓመት በዐለ ሢመት እንዲሁም 67ኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የነፃነት በዓል የምናከብር በየደረጃው ያለን መሪዎች፥ አገልጋዮችንና ምእመናንን የሚጠባበቅ የቤት ሥራችን ነው፡፡
ተዘከሮ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ
ዕቀቦ ዓመታተ ብዙኀ ወመዋዕለ ነዊኀ በጽድቅ ወበሰላም፤
አግርር ፀሮ ታሕተ እገሪሁ ይስአል ለነ ኀበ እግዚአብሔር ከመ ይስረይ ለነ ኀጣውኢነ፡፡
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቊ. 123)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን፡፡
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ (ቆሞስ)
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሓፊ
