ተቀፀል ፅጌ አጼጌ

0027

በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን ሲከበር የቆየው የተቀ    ፀል ፅጌ በዓል በዘንድሮውም ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራትና ገደማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮአል፡፡
በበዓሉ ላይ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናት፣ዩኒፎርም የለበሱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ለበዓሉ ተስማሚ የሆኑ ያሬዳዊ ወረቦችን አሰምተዋል፡፡ ከሁለት ሊቃውንትም ቅኔያት ተበርክተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ገሪማ በኢ.ኦ.ተ.ቤ የውጭ ግንኙነት ዋና ኃላፊ በዓሉን አስመልክተው በጹሑፍ የተደገፈ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተቀፀል ፅጌ አፄጌ በሚል ርዕስ ጀምረው ከስድሰተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በዓሉ በየዓመቱ መስከረም 25 ቀን በታላቅ ሥነ ሥርዓት ሲከበር ከቆየ በኋላ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግን መስከረም 10 ቀን እንዲከበር ተደርጎአል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓሉ የአፄ መስቀል በዓል እየተባለ መጠራት ጀመረ፡፡
ይህም የተባለበት ምክንያት የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ ምድር የገባው መስከረም 10 ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ በተነሣበት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል የነጭና የቢጫ ቀለም ያለበት ከእንቁ ፈርጥ የተሠራ ዘውድ ተቀዳጅተው በሚታዩበት ጊዜ ካህናቱ ተቀፀል ፅጌ አፄጌ ገብረ መስቀል ብለው አሸብሽበዋል በዚያን ጊዜ ወንዱም ሴቱም፣ትልቁም፣ ትንሹም አበባ በመያዝ በደስታና በእልልታ በዓሉን ያከብሩ ነበር፡፡
በበዓሉ ወቅት መስከረም 25 ቀን ሊከበር የቻለበትም የስስት ወራት የዝናም ጊዜ ፍፃሜ ስለሚሆን ለበዓሉ አመቺ ጊዜ ስለነበር ነው፡፡ ቀደም ሲል በቤተ መንግሥት አደባባይ ሲከበር የቆየው የተቀፀል ፅጌ በዓል በ1967 ዓ.ም በደረሰው ድንገተኛ የመንግሥት አስደተዳደር ለውጥ ምክንያት በዓሉ ለ20 ዓመታት ያህል ሳይከበር የቆየ ሲሆን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ግን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት መልካም ፈቃድ እና ጥረት መከበር ጀምሮአል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ለ2007 ዓ.ም ያደረሰን አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይህንን አዲስ ዓመት የሰላም፣የፍቅር፣የአንድነት፣የበረከት፣የረድኤት ዓመት ያድርግልን ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2007 ዓ.ም በየዓመቱ ሲከበር የቆየውን በዓል ለማክበር የተሰበሰባችሁ ሊቃውንት፣የሰንበት ት/ቤት መዘምራን በየበኩላችሁ የዘመራችሁት መዝሙር እግዚአብሔር የሚቀበለው መዝሙር ነው ፡፡ምድሪቱ በመስከረም ወራት አሸብርቃ አብባ ለምልማ ትታያላች እናንተም ያንን መስላችሁ ነው የምትታዩት፡፡ ይህንን በዓል ለማክበር በዚህ ስለተገኛችሁ ልትመሰገኑ ይገባል፡፡ እንዲህ አይነቱን የሰመረ እና የደመቀ በዓል ስናከብር ሰማያዊ ዋጋ እናገኛለን፡፡ የመስቀል በዓል በዩኒስኮ  ሊመዘገብ የቻለው እናንተ በባህላዊ አለባበስ በያሬዳዊ ዝማሬ ስለአሣማራችሁት ነው፡፡ መስከረም 16 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም የምናከብረውን ታላቁን የመስቀል በዓል በሰላምና በፍቅር ለማክበር አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ በማለት ቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳን በማስተላለፍ የበዓሉ ፍጸሜ ሆኖአል፡፡

{flike}{plusone}