ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ የቤተክርስቲያናችንን ንዋያተ ቅድሳት ያለአግባብ በሚጠቀሙና ክብር ዝቅ በሚያደርጉ አካላት ላይ በሕግ ሊያስጠይቅ የሚያስችል ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አሳሰቡ

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የቤተ ክርስቲያናችንን ንዋያተ ቅድሳት ያለአግባብ በሚጠቀሙና ክብር ዝቅ በሚያደርጉ አካላት ላይ በሕግ ሊያስጠይቅ የሚያስችል ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አሳሰቡ።
ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት የቤተክርስቲያንኗን የአእምሮ ሀብትና ቅርሶች ለማስከበር የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ዙርያ ባካሔደው የውይይት መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶቿን፣ የአእምሮ ሀብቶቿንና ንብረቶቿን በሕግ ለማስከበርና ለማልማት የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ያለፉት ሁለት ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና በቀጣይ ተግባራት ዙሪያ ከከፍተኛ የቤተክርስቲያኗ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል ።
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት በተካሄደው በዚህ የውይይት ጉባኤ ላይ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ ተገኝተዋል።
የዐቢይ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አያሌው ሲሳይ ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሑፍና ሪፖርት አቅርበዋል።
ኮሚቴው በ2015 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በቤተክርስቲያኒቱ ስም የሚገኙ የአእምሮ ሀብቶችና ቅርሶች በባለሙያ ተጠንተው በባለቤትነት እንዲመዘገቡና ለልማት እንዲውሉ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በሪፖርቱ ከተጠቀሱ ዋና ዋና ተግባራት መካከል
፡-አስፈላጊውን በጀትና የሊቃውንት ኃይል በመመደብ ቅርሶችን በጥናት የመለየት ሥራ መከናወኑ እና በዚህ ተግባር ላይ በርካተ ሊቃውንት መሳተፋቸው ተገልጾል፤ቅርሶቹን በአእምሯዊ ንብረትነት (Intellectual Property) የማስመዝገብ ተግባር መጀመሩ፤የ
ተመዘገቡ ቅርሶችን በቋሚነት የሚከታተልና መብታቸውን የሚያስከብር ማዕከላዊ መዋቅር እንዲዘረጋ ውሳኔ መተላለፉ ጠቅሰዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ባስተላለፉት መልእክት፤ ኮሚቴው እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት የቤተክርስቲያንን ንዋያተ ቅዱሳት ለማስከበርና ገጽታዋን ለመጠበቅ ጉልህ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ይበልጥ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች የቤተክርስቲያኒቱን ንዋየ ቅድሳት በሚያቃልል መልኩ የሚታዩ የውጭ አካላት እንቅስቃሴን በሕግ ሊያስቆም የሚችል ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ መሥራት እንደሚገባ በአጽንዖት አሳስበዋል። ቤተክርስቲያኒቱ ከጊዜው ጋር በፍጥነት መራመድና ሀብቶቿን ማስከበር እንዳለባትም አክለዋል።
በውይይቱ ወቅት የአልባሳተ ክህነት፣ የቅዱስ መስቀል እንዲሁም ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ሀብቶች የሆኑ ቅርሶች ቀኖናንና ዶግማን በጠበቀ መልኩ ብቻ ለሕትመትና ለምርት እንዲበቁ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ዐቢይ ኮሚቴው በቀጣይ ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ እንደሚያቀርብ የገለጸ ሲሆን፣ የቤተክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉለት ጥሪ አቅርቧል።
©eotc tv