ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚያከናውናቸውን የአገልግሎት አሰጣጥና የልማትና ሥራዎችን ጎበኙ።በጉብኝቱ ወቅት የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዓይናለም እንደገለጹት የክፍለ ከተማው ፖሊስ የአባላቶቹን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ የተለዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በጎ አድራጊ ግለሰቦች ተሳትፎ ጭምር በመከናወን ላይ ይገኛሉ ካሉ በኋላ የፖሊስ ሠራዊት ልጆች ወላጆቻቸው ሥራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ በእንክብካቤ ተጠብቀው የሚቆዩበት የሕጻናት ማቆያም ሠርተን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የሠራዊቱ ማረፊያ በሚል ቤቶች በቆርቆሮ የተሠሩ በመሆናቸው ሠራዊቱን ለብርድና ለሙቀት ከመዳረጋቸውም በላይ ለኑሮ ምቹ ባለመሆናቸው በከፍተኛ ችግር ላይ ስለሚገኙ ይህንን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ሕብረ ተሰቡ በሰላም ወጥቶ በእንዲገባ ከፍተኛ የጸጥታና የሰላም ማስከበር ሥራ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ቤተክህነት በሚያከናውናቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና የአደባባይ በዓላት ዙሪያ ከቤተክርስቲያናችን ጎን በመቆም በርካታ ሥራዎችን የሚሰራና አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ሁሉ የሚያደርግልን በመሆኑ ምስጋናችንን አናቀርባለን ብለዋል።
በመጨረሻም የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤታችን በሚገኝበት ክፍለ ከተማ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፖሊስ መምሪያው በሚያከናውናቸው ማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ዙሪያ በጋራ እንሠራለን ፤ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በሚያቀርበው ጥናት መሠረትም አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብርም እናደርጋለን በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።
