ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከህፃንነት ጀምሮ ያደጉበትን ፣ ተምረው ያስተማሩበትንና ሥርዓተ ምንኩስና የተቀበሉበትን የጪኽ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴን ገዳም ጎበኙ!!
ቅዱስነታቸው ለገዳሙ የብራና መጽሐፍ ሲያበረክቱ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎችን ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን በማስከተል ዓርብ ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም የጉዞ መነሻቸውን ከመንበረ ፓትርያርክ በማድረግ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በመቐሌ ከተማ ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ላይ የደረሱ ሲሆን በመቐሌ አየር ማረፊያ በደረሱበት ወቅት ፣ የመቐሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ የደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ፣ የደቡባዊ ምሥራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ አረጋሽ በየነ እና በርካታ ሊቃውንት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉዞአቸውን ወደ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ሚካኤል ያደረጉት ቅዱስነታቸው በቤተ ክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ቅዱስነታቸውም የተሰማቸውን መንፈሳዊ ደስታ ገልፀው ቡራኬና ቃለ ምዕዳን በመስጠት በቀጥታ “አቡነ መርሐ ጨለቆት የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” ወደ ሚገኝበት ጨለቆት ደብረ ምህረት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ነው፡፡
በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ጥረት ተሠርቶ ለምረቃ የበቃውን “አቡነ መርሐ ጨለቆት የገጠረር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” ባለ 16 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ቅዱስነታቸው በይፋ ባርከው የከፈቱ ሲሆን በጨለቆት ደብረ ምህረት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ለተገኘው በርካታ ምዕመናን ትምህርተ ወንጌል በመስጠትና ቃለ ቡራኬ በማስተላለፍ የፕሮጀክት ምረቃ በዓሉን አክብረዋል፡፡
የሁለተኛው ዕለት የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎትና ጉብኝት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከአዲስ አበባ ከተማ ያስከተሉአቸውን የሊቃነ ጳጳሳትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ልዑካን ቡድን በመያዝ ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2007 ዓ.ም በመቐሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሥርዓተ ቅዳሴ በማድረስና በዕለቱ ለተሰበሰበው በርካታ ማህበረ ምዕመናን የወንጌል ትምህርት ከሰጡ በኋላ በዚሁ ዕለት የመቐሌ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ መርሐ ግብር የሚአስመርቃቸው ደቀ መዛሙርት የምስክር ወረቀት በመስጠትና አባታዊ መመሪያ በማስተላለፍ መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡
የሦስተኛው ዕለት የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎትና ጉብኝት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ከሰኔ 26-27 ቀን 2007 ዓ.ም ካከናወኑአቸው ሐዋርያዊ ተግባራትና ከአደረጉአቸው ጉብኝቶች ሰኔ 28 ቀን 2007 ዓ.ም ያከናወኑአቸው ሐዋርያዊ ተግባራትና ጉብኝት ለየት የሚአደርገው፣ ከህፃንነታቸው ጀምሮ ያደጉበትን፣ ተምረው ያስተማሩበትንና ሥርዓተ ምንኩስና የፈጸሙበትን ታሪካዊውን የተንቤት ጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴን ገዳም ከሀገር ከወጡ ከ50 ዓታት በኋላ መጎብኘታቸው ሲሆን ፤ ቅዱስነታቸው ካከናወኑአቸው ሐዋርያዊ ተግባራትና ካደረጉት ጉብኝት በመጀመሪያ በተንቤን ወይና ደጋማ አካባቢ በሚገኘው በሀገረ ሰላም ከተማ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን በመጎብኘትና ለበርካታ ምዕመናን ትምህርተ ወንጌል በመስጠት በጉጉትና በናፍቆት ሲጠበቅ ወደነበረው ጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ጉዞ የተደረገ ሲሆን ቅዱስነታቸው በጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ክልል እንደደረሱ በርካታ ምዕመናን በእልልታና በጭብጨባ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል በገዳሙ አውደ ምህረት በተካሄደው መርሐ ግብር በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ መዝሙራት ቀርበዋል፡፡
አንድ ታዋቂ የዜማና የቅኔ ምሁር በምድረ ተንቤን ኢይኩን ሀከክ ወበገዳማቲሃ ኢይብቁል ሶክ ጸሊ ኃበ አምላክ ማትያስ ፓትርያርክ መካነ ሕይወት ከመትትባረክ” በማለት ከቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት በማቀነባበር በጥዑም ዜማ ሰሙ በኋላ በርካታ መወድስ ቅኔያት አበርክተዋል፡፡ ካበረከቱአቸውም ቅኔያት መካከል፡-
ጉባኤ ቃና፡- መካነ ሕይወት ትብል በዘኢሳይያስ ድምፅ፣
ለፓትርያርክ ወልድየ ፀዋዕክዎ እምግብፅ፣
-ዘአምላኪየ መካነ ሕይወት እም ማህቶተኪ አህትዊ፣
-እስመ በጽሐ ናሁ ማትያስ መርአዊ፣
-ከመ በኃይሉ ያሰስል ረሀበ ሥጋነአዊ
-በቃለ ውዳሴ ጥዑም ዘአይፀረዕ፣
-መካነ ሕይወት እም ለእግዚአብሔር ተአኩቶ፣
-እምደህረ ብዙህ ዘመን ዘኁልቆ ዘመን አህትቶ፣
-እስመዮም በፍስሐ ለማትያስ ፍሬ ማህፀና በዐይና ርዕየቶ
-ኪያሁሰ በአሚን ዘከመ ኢረሰአ ፍጸመ ይእቲ ኢረስአቶ
-አሀውሂ ካህናት ዘአልብክሙ አስትቶ፣
-ጻኡ ተቀበሉ ወተደለው በተትህቶ፣
-ለመርአዌ ሰላም ማትያስ ሶበ ተሰምአ ምፅአቶ፣
-ምስለ መኳንንት ጳጳሳት ለምስጢረ ሰላም ከመ ይክስቶ፣
-ወአስራተ ፅዮን ቆመ ከመ ያርሁ ሆህቶ፣
በመቀጠልም መምህር ዘመንፈስ ቅዱስ የተባሉት የገዳሙ አስተዳዳሪ የገዳሙን ጥንታዊነትና የቅዱስነታቸውን የልጅነት ሕይወት አስመልክተው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፡፡ መካነ ሕይወት ጪህ ቅድስት ሥላሴን ገዳም የገደሙት አፄ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ሀብተ ማርያም የተባሉ በዋሻ የሚኖሩ መናኝ ባህታዊ ባሉበት ጊዜ አፄ ዮሐንስ ጸሎት ለመቀበል በመጡበት ወቅት ነብርና ዘንዶ ከፊታቸው ይቆም ስለነበር አፄ ዮሐንስ ሲመጡ ንጉሡን ከዘንዶና ከነብር በማዳን እንደሚነግሥ ትንቢት በመናገር ይህን ገዳም ቀቀማና ጪህን ገድምልኝ ብለውት ስለነበር ትንቢቱ ተፈጽሞ ንጉሡ ነገሠ፡፡ ከዚያም በአንድ ቀን ጧት ቀቀማን ማታ ጪህን ገደመ…፡፡ በገዳሙ ዘወትር ሰአታትና ጸሎተ ማህበር አይታጎልም፡፡ ገዳሙ የእርሻም ሆነ ሌላ ገቢ የለውም፡፡
ብፁዕ አቡነ ማትያስ ወደዚህ ገዳም ሲመጡ በጣም ህፃን ነበሩ፡፡ በገዳሙ ታዛዥ ፣ ቅን ናቸው፡፡ እንደአቡነ ተክለሃይማኖት በተግባርቤት ወፍጮ በመፍጨት እንጀራ በመጋገር አገልግለዋል፡፡
አንድ ቀን ክፉ ነገር ተናግረው አያውቁም፡፡ ኦሆ በሀሊ ናቸው፡፡ ሲፈጠሩ ጀምሮ ቅዱስ ናቸው፡፡ በማለት አብራርተዋል፡፡ በማያያዝም ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንች እና ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የበላይ ኃላፊ በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ሰፋ ያለ ትምህርት የሰጡ ሲሆን የቅዱስነታቸውን አባታዊ ሲመት ሁላችንም አምነን ተቀብለናል ፣ ከህፃንነታቸው ጀምሮ ባገለገሉበትና ሥርዓተ ምንኩስናን በተቀበሉበት በዚህ ታሪካዊ ገዳም ከቅዱስነታቸው ጋር በመገኘታችን እጅግ በጣም ተደስተናል ብለዋል፡፡ በመጠቀልም ቅዱስነታቸው ለመካነ ሕይወት ጪህ ቅድስት ሥላሴ ገዳምና ለሌሎችም የተንቤን ገዳማት ያበረከቱትን ስጦታ አስመልክቶ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የልዩ ጽ/ቤት ኃላፊ ሲአብራሩ በቅዱስነታቸው አስተባባሪነት ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም ተሠርቶ ለፍጻሜ የሚበቃበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በዛሬው ዕለት የመሠረት ድንጊያ ለሚቀመጥለት ለጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ ገዳምና ኪዳነምሕረት ገዳም ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር የግንባታ መጀመሪያ የሚሆን አንድ መቶ ሺህ ብር በአክሱም ሀገረ ስብከት በኩል ለገዳሙ እንዲሰጥ ገንዘቡ ተላልፏል፡፡ ለገዳሙ መነኮሳት ለጥራ ጥሬ መግዢያ የሚሆን ሃያ ሺህ ብር ቅዱስነታቸው ለግሰዋል፡፡ ለቀቀማ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ገዳም አስር ሺህ ብር፣ ለደብረ መድኃኒት ዐቢዬ እግዚ ገዳም አምስት ሺህ ብር ለአባ ሀደራ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ገዳም አምስት ሺህ ብር ፣ ለመድኃኔዓለም ገዳም አምስት ሺህ ብር ፣ ለኪዳነምሕረት ገዳም አምስት ሺህ ብር ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም አምስት ሺህ ብር ፣ ለአባ ዮሐኒ ገዳም አምስት ሺህ ብር ፣ ለቅዱስ ዮሐንስ ገዳም አምስት ሺህ ብር ፣ በአጠቃላይ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ተደርጎአል ብለዋል፡፡
ከንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ማብራሪያ አያይዘው አጭር መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ከህፃንነታቸው ጀምሮ ላደጉበትና ለተማሩበት ፣ የምንኩስናን ሥርዓትም ላከናወኑበት ለተንቤን ጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ቤተ መዘክር ህንፃ ግንባታ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም የተንቤን ጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ ውጤት የሆኑት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መልእክታቸውን ሲአስተላልፉ ይህች ዕለት የተቀደሰች ዕለተ ሰንበት ናት፡፡ ከሀምሳ ዓመታት በኋላ ወደተማርኩበት ፣ ከመንፈስ ቅዱስ በምንኩስና ወደ ተወለድኩበት ገዳም መጥቼ ገዳሜን በመጎብኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም አጅበውኝ ስለመጡ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ጉብኝቱን በማክበር የተቀበላችሁትን እጅግ እናመሰግናለን፡፡ ይህ ገዳም ታላቅ ገዳም ነው፡፡ ብዙ አበው መነኮሳት አልፈውበታል ፡፡ የቅርስ ፣ የታሪክ ፣ የሊቃውንት ቦታ ነው፡፡ ዛፎቹም ጥንታውያን ናቸው፡፡ ይህም የገዳሙን ጥንታዊነት ያሳያል በዚህ ገዳም ያሉ አባቶች ታላላቆች ናቸው፡፡
እግዚአብሔርን ሲአመሰግኑ በጸሎታቸው ሀገርን የሚጠብቁ አበው አልፈውበታል፡፡ ስለዚህ ገዳሙ የታሪክ ፣ የጸሎት ፣ የአምልኮት ገዳም ስለሆነ ሊጠበቅና ሊከበር ይገባዋል፡፡ አፄ ዮሐንስ በተንቤን ብዙ ገዳማት ገድመዋል፡፡ ጪህና ቀቀማ ባንድ ቀን የተገደሙ ገዳማት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አበምኔት መምህር ዘሚካኤል ይባላሉ የቀቀማ ደግሞ መምህር ገብረጊዮርጊስ ይባሉ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ባህታውያን ናቸው፡፡ የጪህና ቀቀማ ገዳማት መሥራች መምህራን ናቸው፡፡ ቀጣዩ መምህር ገብረ ማረያም ይባላሉ፡፡ ሦስተኛው መምህር ገብረ ክርስቶስ ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ በነበርኩበት ዘመን የነበሩት መምህር አሥራት ይባላሉ፡፡ እኔ ከዚህ ገዳም የወጣሁት በ1958 ዓ.ም ነው፡፡ በቀጥታ የሄድኩትም ርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን የትርጓሜ መጻሕፍት ለመማር ነው፡፡ አሁን ገዳሙን እያስተዳደሩ ያሉት መምህር ዘመንፈስቅዱስ ያን ጊዜ ትንሽ ህፃን ነበሩ ከእኔ ጋር የነበሩት መነኮሳት በሞተ ሥጋ አልፈዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ከነበሩት መነኮሳት መካከል አንድ ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡
ይህ ሀገር የእነ አፄ ዮሐንስ ፣ የእነ እራስ አሉላ ሀገር ነው፡፡ የታሪክ ፣ የሃይማኖት ፣ የሰላም ፣ የፍቅርና የአምልኮት ሀገር ነው፡፡
ስለዚህ ቅርሳቸውና ታሪካቸው ተጠብቆ እንዲኖር በጥብቅ አሳስባለሁ በማለት ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አስተላልፈው እንደጨረሱ በጠራራ ፀሐይ ከየት አቅጣጫ እንደመጣ በውል ያልታወቀ ግዙፍ የሆነ የምህረት ዝናም ምደረ ተንቤን አጠልቅልቋል፡፡ የዚህ የድንገተኛ ዝናም መፍሰስ የአካባቢውን ምዕመናን አስገርሟል ፤ አስደስቷልም፡፡ ለበርካታ ደቂቃዎች ያህል በመፍሰስ ምድረ ተንቤን ያጨቀየው ይህ የምህረት ዝናብ ጋብ እንዳለ አዲስ ለሚገነባው ለተንቤን ጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ ገዳም ቤተ ሙዝየም የመሠረት ድንጊያ በቅዱስነታቸው ተቀምጦአል፡፡ ከዚያም በተንቤን ጪህ መካነ ሕይወት ቅድስት ሥላሴ አሻጋሪ ላይ ወደ ሚገኘው ወደራስ አሉላ ገዳም ጉዞው የቀጠለ ሲሆን የራስ አሉላ የትውልድ ቦታ በሆነው ለሚገነባው ሙዝየም የመሠረት ድንጊያ ተቀምጧል፡፡
በመጨረሻም በዕንዳ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የጉብኝት ተግባር ከተከናወነ በኋላ የታሪካዊው ሐዋርያዊ አገልግሎትና ጉብኝት ሥራ ተጠናቋል፡፡ {flike}{plusone}