ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ‹‹ አስተዳደራዊ አስተሳሰብን ማበልፀግ ›› በሚል ርዕስ ከመዋቅር ውጭ ሀብትን የሚአካብቱ ማኅበራትን አስመልክተው ከአድባራትና ገዳማት ተወካዮች ጋር ውይይት አደረጉ

h0386

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፍያን ጋር የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልፀግ በሚል ርዕስ ለግማሽ ቀን የቆየ ውይይት አድርገዋል
ቅዱስነታቸው በጽሑፍ ባቀረቡት የመግቢያ ንግግር
ምክር ሠናይት ለኩሉ ዘይገብራ ለሚፈጽማት ሰው መመካከር መልካም ናት ውይይት መልካም ነው፡፤ የእግዚአብሔር ቃልም የሚያስተምረን መመካከር፣መረዳዳትና መወያየት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ውይይት ግንዛቤን ያሰፋል፣ለአንድ ዓላማ ያነሳሳል፣ፍቅርና ሰላም ያሰፍናል፣አንድ አመለካከት ይፈጥራል፣መንገድ የሳተም ይመልሳል፣የወደፊት አቅጣጫም ያስተካክላል፡፡
o ዛሬ የምንወያይበት ርእሰ ጉዳይ የቤተክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ለማበልፀግ ነው፡፡
የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልፀግ ለምን እንፈልጋለን ወይም ለምን እንዲኖር እንገደዳለን? ብንል
o    ዘመን ይለወጣል፣በዘመን ውስጥ የሚኖር ሰውም አስተሳሰቡ እንደየሁኔታው ይለወጣል፡፡ ይህ ለውጥ በአወንታዊ ጎኑ እድገት ሲሆን በአሉታዊ ጉኑ ደግሞ ውድቀት ሊያስከትል ይችላል፡፡
o  ዘመን በመለወጡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ሁልጊዜ አሉ፡፡
o    እኛም ለለውጡ አስተዋፅኦ አለን፡፡
o    እኛ ለአወንታዊ ለውጥ የምናደርገው አስተዋፅኦ የመሪ ድርሻ ይዘንና ሕዝቡን አንቀሳቅሰን ነው? ወይስ እንዲሁ እንደ ነገሩ በተገኘ አጋጣሚ አጋጣሚውን እየመለስን? ብለን ልንጠይቅ ይገባናል፡፤ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ያለን የቤተክርስቲያን መሪዎች ይህ ጥያቄ በአንክሮ ልናየው ይገባል፡፡
o    ቤተክርስቲያናችንና ሀገራችን በእናንተና በምዕመናን ጸሎትና ጠንካና ሥራ በመላ ሕዝባችን ጥረት እድገትዋና ሰላምዋ እውን እየሆነ ነው፡፡ ይህም በበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ለዚህም ታላቁን ድርሻ የያዝነው እኛው ነንና ጠንክረን ልንቀጥልበት ይገባል፡፡
o  ዘመኑን ሳንዋጅ ቀርተን እንዲሁ እያዘገምን፣አሠራራችን ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ በሳል የሆነ አመራር የማንሰጥ ከሆነ ሳናስበው ራሳችንን የምንመራውን ሕዝብ አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን፡፡
o    እናንተ የምታስተዳደርዋት በአዲስ አበባ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ብንመለከት ከተማዋ የአፍሪካ የፖለቲካዊ መዲና፣ዓለም አቀፍ የዲፖሎማት መናኸሪያ፣የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ማእከል ናት፡፡ በተጨማሪ የብዙ ሙራን፣ጋዜጠኞች፣ደራስያን፣ተቺዎችና ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች የሚገኙባት ዓለም አቀፍ ከተማ ሆናለች፡፡
o    በከተማዋ የሚኖሩ ምእመናንና የምእመናን ልጆችም በትምህርትና በኑሮ እየበለፀጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለውጡ በሚፈጥረው እድገት ስለ አሠራራችን በቂ እውቀት አላቸው ከውጭ የሚመጡ ሰዎችም ታላቅዋን ቤተክርስቲያን ከብዙ አቅጣጫ ይመለከቷታል፣ጥንታዊት ስለሆነችም የዳበረ አሠራር እንደሚኖራት ይጠብቃሉ፡፡
ስለዚህ ዘመኑ ጠንካራ በሁሉም ዘንድ የተከበረ የቤተክርስቲያን መሪና አገልጋይ ይፈልጋል፡፡ ምእመናንና ምእመናትም ታማኝ፣ንጹሕ፣በሳል፣ስለነገሮች ሁሉ ቀድሞ የሚያስብና የሚያቅድ፣ስለቤተክርስቲያን ዕለት ዕለት የሚጨነቅና ጸጋ እግዚአብሔር የበዛለት ካህንና አገልጋይ ይፈልጋሉ፡፡
ራሳችንን ለመፈተሽ አንዳንድ ተጨባጭ ጥናቶችንና ኩነቶችን እንመልከት
ከሃይማኖታዊ ገጽታ ስናየው
o   ጥንታዊት፣ታሪካዊት ሐዋርያዊትና ዓለም ዓቀፋዊት፣ለሀገር ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገች የታላላቅ አባቶች መሪዎች መፍለቂያ የሆነች ቤተክርስቲያን አለችን፡፡
o    የብዝኃ ሕይወት መገኛም ናት፡፡
o    በአባቶቻችን ትጋት ያገኘናቸው ምእመናን በቁጥር የሚቀንሱበት ሁኔታ ተከስቶአል፡፡
ለምሳሌ ባለፉት አሥር ዓመታት ብቻ በአዲስ አበባ 7 በመቶ ቀንሷል፣ኦሮምያ 10 በመቶ ቀንሷል ደቡብ ክልል 7.8 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህ አኃዝ አሁንም እየቀጠለ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡ የምእመናን ቁጥር የመቀነስ ጉዳይ በአሉታዊ ጎኑ ሃይማኖታዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ ያስከትልብናል፡፡
o   ሃይማኖታዊ ተልእኮአችንን መሠረት አድርገን ብንመለከት ወደ መንግስተ እግዚአብሐሄር የምናቀርበው ሕዝብ እያጣን መሆኑን ያሳያል፡፡
ከኢኮኖሚያዊ ዓቅም አኳያ ስንመለከት
የቤተክርስቲያን ሀብት እየቀነሰ ይሄዳል፣ስለዚህ የሚዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እየበዙ ይሄዳሉ፡፡ ይህም እየታየ ያለው አደጋ ነው፡፡
ከማኅበራዊ ገጽታ አንጻር ስናየው፣
የቤተክርስቲያን እሴቶች በሀገሪቱ የነበራቸውን ጠቀሜታ ይቀንሳሉ፣ጥንታውያን እሴቶቻችን እየቀነሱ ከሄዱ የሃይማኖታችንና የሀገራችን መሠረታዊና ማኅበራዊ እሴቶች ይጎዳሉ፡፡ ይህ ወርቃማ ባህላችን ከተጎዳ ደግሞ ጭካኔ፣ስግብግብነት፣ስንፍና ወንጀል ይበዛሉ፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ይቀንሳል ብሎም ይጠፋል፡፡ የትውልዱ ሥነ ምግባር ይጎዳል፡፡ ይህም እየታየ ያለ አደጋ ነው፡፡
->  የተጋረጡብንን አደጋዎች በመንፈሳዊ ኃ    ይል ለመመከት ሃይማኖችንንና መልካሙ ታሪካችንን በመጠበቅ ወደ ራሳችን መመልከት ግድ ይለናል፡፡ ምክንያቱም አደጋ ላይ እየጣሉን ያሉ ችግሮች አስቀድመን በመለየት መፍትሄ ማስቀመጥ የወቅቱ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ ላንሳ
አንዳንድ ሰዎች ችግራችንን ግልፅ አድርገን እንወያይ ስንላቸው ሌሎች ሃይማኖቶች በኛ ላይ ሊዘባበቱ ይችላሉና ዝም ማለት ይሻላል ብለው ይመክራሉ፡፡ ይህ አባባል ምን ማለት ነው ብለን እንየው፡
1)    በመመካከር ልናገኘው የምንችለውን መፍትሔ እንዳናገኝ በችግር ውስጥ እየተሸከረክርን እንድንኖር ያደርጋል፡፡
2)    በምንፈጥረው መፍትሔ ቤተክርስቲያን ለምእመናንና ለሕዝቡ የምትሰጠው የተሻሻለ አገልግሎት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
3)    የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ስራ በዘመኑ ስልት እንዳይቃኝና ሃይማኖታችን እንዳይስፋፋ ያደርጋል፡፡
4)    የቤተክርስቲያንን ሃብትና ንብረት ያለምንም ቁጥጥር የሚሰበስቡና የሚዘርፉ አንዳንድ ግለሰቦችንና ማኅበራት ዝርፊያቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስችላል፡፡
5)    በዚህ ዘመን ማናቸውም የሚደረግ ነገር ሁሉ ለሕዝቡ ያልተደበቀ በመሆኑ ምእመናን በየቀኑ እያዘኑበት ያለ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ ችግራቺንን  ይዘን በየቀኑ ዝም እንድንል የሚመክሩን የቤተክርስቲያን መሻሻልና መጠናከር የማይፈልጉ ወይም የችግሩን አሳሳቢነት ያልተረዱ ከማለት በቀር ሐሳቡ ዘላቂ ችግርን ከመፍታት አንጻር መልስ የለውም፡፡
የብልሹ አሠራር አደጋ፣
በቤተክርስቲያን ቋንቋ ብልሹ አሠራር ማለት ትምህርተ ወንጌልን የሚጻረር አሠራር መፈጸም ማለት ነው፡፡
በዝርዝር ስንመለከተው
o    ፍትሕ ማጉደል፣ፍትሕንም ለማጉደል መደለያ (ጉቦ) መቀበል፣በዘር፣በአካባቢ በመደራጀት ንጹሑን ሰው መበደል ያልደከሙበትን የሕዝብን ሀብት ያለ አግባብ ማባከን፣
o    ለምእመናን ትጉና መልካም አርአያ አለመሆን፣
o    ከራስ ባላይ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር አለመቆርቆር፣ዋነኛው የአደጋው መገለጫዎች ናቸው፡፡
ካለን ተጨባጭ ልምድ ለማስረዳት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከአምስት በላይ ከሚሆኑ አድባራትና ገዳማት የተውጣጡ ምእመናንና ካህናት መልካም አስተዳደር አጥተናል በሚል በሰልፍ መጥተዋል፡፡
የአቤቱታው ጥልቀት ይዘት ስንመለከተው
o    በቤተክርስቲያን የተሰጠው ኃላፊነት ተጠቅመው ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸው በአንዳንድ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በመዋቅር ውስጥ እንደሰንሰለት ተያይዘው ለራሳቸው ጥቅም የሚሰሩ ግለሰቦች መበራከት፣
o    ይህ ብዙዎችን አስተዳዳሪዎች ባይወክልም በኃላፊነት ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚፈፅሙት በመሆኑ ለቤተክርስቲያን ቀጣይ ህልውና አደጋ እየሆነ መምጣቱ፣
o    ከሁሉም በላይ ምእመናን ከቤተክርስቲያን እጅግ የላቀ መንፈሳዊ ተግባር ስለሚጠብቁ ይህ ባልሆነበት ጊዜ ምእመናን ክፉኛ የመንፈስ ስብራት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይታያል፡፡
መዋቅራዊ አሠራር ያለመጠበቅ አደጋ
o    ቤተክርስቲያን ግልፅ የሆነ መዋቅር ያላት ስትሆን በቤተክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራትና ግለሰቦች መዋቅሩን ይፈታተናሉ፣
o    በቤተክርስቲያን ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት በቤተክርስቲያን ስም ከቤተክርስቲያን መዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት ማካበት ፈፅሞ የተከለከለና በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ መሄዱ
o    በዚህ ወቅት የሚታየው የማኅበራት ዝንባሌም ሀብት ማካበት፣ለቤተክርስቲያን ብቻ የተፈቀደውን አሥራትና በኩራት ወደ ራሳቸው መሰብሰብ፣ከቤተክርስቲያን እውቅና ውጭ ቤተክርስቲያንን በሚተካ መልኩ የውጭና የሀገር ውስጥ ሥራዎችን በሌለ ሥልጣን መሥራት
o     በሰበሰቡት ሀብት አባቶችን መከፋፈል፣አልፎም የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ማሾም፣ማሻርና ማስፈራራት ላይ መድረሳቸው ይህ አካሄድ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ጥንካሬና ሕልውና ፍጹም አደጋ ነው፡፡
o    በቤተክርስቲያን  ስም ያለአግባብ ሀብትና ንብረት ያካበተ ማንኛም ኃይል ባስፈለገ ጊዜ እምቢተኛ በመሆን ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል ሊዳርጋት ይችላል፡፡ ይህም ሌላው ትልቁ አደጋ ነው፡፡
o    ሌላው አደገኛው ነገር ሕግና ስርዓት የማይቆጣጠረው ማኅበር ጽንፈኛ አሸባሪ የመሆን እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም መንገዶች ለራሱ ጥቅም ብቻ እንዲውሉ ይፈልጋልና በዓለማችን የምናየውና ንጹሑን እየጎዳ ያለው ትዕይንት ሃይማኖታዊ ሽፋንን ይዞ ነው እንጂ ሃይማኖት ፀረ ሰላም ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ይህንን ያልተገባ አካሄድ ሥርዓት እንዲይዝ በአቋም ልንቃወመው ይገባል፡፡

0411

በመጨረሻ
ከላይ በዝርዝር የተመለከትነውን መሠረተ ሐሳቦች ለቤተክርስቲያንና ለሀገር የማይበጁ በመሆናቸው እያንዳንዳችን ራሳችንን በመፈተሸና በማፅዳት ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ሁላችንም የድርሻችንን እንድንወጣ በማሳሰብ ይህ ውይይት ዓመቱን ሙሉ በተከታታይ ከሚመለከታቸው የቤተክርስቲያን አካላትና ምእመናን እንደሚካሄድ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ስለሆነም ምንም ጊዜም የማይቀለበስን የማይሸራረፍ የቤተክርስቲያችን ልዕልና ንጽሕናና ቅድስና ሐቀኝነትና ፈሪሃ እግዚአብሔርን ተላብሰን ብምናደርገው የማያቋርጥ እንቅስቃሴ በየስፍራው በኃላፊነት የምትገኙ ኃላፊዎች ከቅድስት ቤተከርስቲያናችን ጎን በጽናት እንድትሰለፉ አበክረን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በማለት አባታዊ የመክፈቻ ንግግራቸውን ካቀረቡ በኋላ በቀጠልም በንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ አወያይነት ከመዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ ሀብትንና ንብረትን በማካበት ስለሚንቀሳቀሱ ማህበራት ከተሰብሳቢዎች በርካታ ሀሳብ ከተሰጠ በኋላ የሚከተለው የጋራ አቋም መግለጫ ቀርቧል፡፡
1.    ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን ያቀረቡትን ችግሮች በትክክል ተለይተው የተቀመጡ ስለሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት ያስቀመጡት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሙሉ በሙሉ ተቀብለናል ለተግባራዊነቱም እንተጋለን፡፡
2.    በየአድባራቱና ገዳማቱ ያለውን አሰራር በማዳበር ከምዕመናንና ከሀገራችን የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በታማኝነት አንሠራለን፡፡
3.    በአንድ አንድ ግለሰቦች የሚታየውን የሀብትና የንብረት ዘረፋ እንዲሁም ያልተገባ ጥቅም የማግበስበስ ተግባር አጥብቀን    በዕለት ዕለት ሥራችንም በጥቅመኞች ላይ ጥብቅ ክትትል እናደርጋለን፡፡
4.    የቤተ ክርስቲያን ሕግና ደንብ በማይፈቅደውና ለቤተክርስቲያናችን አደጋን በሚአስከትል በቤተክርስቲያን ስም ሀብትና ንብረት በማካበት ላይ ያሉት ማህበራት ሥርዓትና ደንብ ተከትለው ያካበቱትን ሀበትና ንብረት በቤተክርስቲያናችን ቁጥጥር ስር እንዲውል እንዲያደርጉ ጥሪአችንን እናቀርባለን፡፡ በቤተክርስቲያናችንም ሕግና ሥርዓት አንዲመሩ እንጠይቃለን፡፡
5.    ከላይ የተዘረዘሩትን የአቋም መግለጫዎች ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ከፍተኛ የሥልጣን አካልም በመሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ ውሳኔ እንዲአስተላልፍ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

{flike}{plusone}