ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጅማ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አገልግሎት አካሄዱ
ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ከሌሊቱ በአስር ሰዓት ከመንበረ ፓትርያርክ ጉዞአቸውን የጀመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ልዩ የሥራ መሪዎች ዕሁድ ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም ከጧቱ አንድ ሰአት ከሰላሳ ሲሆን በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኘው አበልቲ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም የደረሱ ሲሆን በቅዱስነታቸው መሪነት የኪዳን ጸሎት ከተደረገ በኋላ በገዳሙ ሥር የተቋቋመው የአብነት ት/ቤት የጉብኝት ሥራ ተከናውኖአል፡፡
በመቀጠልም በገዳሙ ስም የተከፈተውን የጤና ኬላ ቅድስነታቸው ባርከው ሪቫኑን በይፋ ቆርጠዋል፡፡ በጤና ኬላውም የሚገኙትን የሕክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እና የሕክምና መስጫ መሳሪያዎችን ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ጐብኝተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መርሐ ግብሩን በአስተባብሩበት ወቅት የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ይህንን የአብነት ት/ቤት የግንባታ ሥራ በምናከናውንበት ወቅት ትልቅ ድጋፍ ያደረጉልን የውጭ ዜጐች ሲሆኑ በተጨማሪም ማህበረ ቅዱሳንም ለአብነት ት/ቤቱ ግንባታ ድጋፍ አድርጐልናል፡፡ ቀደም ሲል አጋሮ የተፈጸመውን የካህናት፣ ግድያ ተከትሎ ቁጥራቸው 130 የሚደርሱ ካህናት እና 190 የሚደርሱ ዲያቆናት ቤተ ክርስቲያንን ዘግተው የሄዱብን በመሆኑ የሀገሩ ተወላጅ እና የየአካባቢውን ቋንቋ የሚናገሩ፣ ህፃናትን በማሰባሰብ መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ትምህርት እንዲማሩ ለማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በማብራሪያቸው እንደገለጹት ተማሪዎቹ ከዚሁ አካባቢ ማህበረሰብ የተወለዱ ከሆነ መከራ ሲገጥማቸው ቤተክርስቲያንን ዘግተው ሊሄዱ ስለማይችሉ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከዚህ ቀደም ከስድሳ የማያንሱ ልጆች ተመርቀዋል፡፡ በአብነት ት/ቤቱ የድጓ፣ የቅኔ፣ የመጽሐፍ፣ የቅዳሴ እና የዝማሬ መምህራን የተመደቡ ስለሆነ ትምህርቱም በአግባቡ እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም ለዚሁ ገዳም ማጠናከሪያ እንዲሆን ለተገነባው የጤና ማዕከል በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ በጐ አድራጊዎች የበጀት ድጋፍ አድርገውልናል በማለት ብፁዕነታቸው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ በመቀጠልም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ሰው ካለው ካካፈለ እግዚአብሔር ስጦታውን ይቀበልለታል፡፡ እግዚአብሔር ለሰዎች ሀብት የሚሰጠው ሰዎች እንዲአካፍሉ ነው፡፡ ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ፣ ለሃይማኖት ማስተማሪያ ለበጐ አድራጐት ሥራ የሚውል ስጦታ የሚሰጥ ምዕመን የተባረከ ነው፡፡ ከኢጣሊያ የመጡ ክርስቲያናች ያደረጉት ድጋፍ ካላቸው ገቢ ቢሆንም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የሥራ ሰው ናቸው፤ የሥራም ችሎታ አላቸው፡፡ ሰው ለሥራ ከተነሳ እግዚአብሔር ይረዳዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የሠሩት ሥራ ሁላችንንም አስደስቶናል፡፡ ብፁዕነታቸው የሠሯቸው ህያው ሥራዎች ሁሉ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ኣርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው የሠሩት ሥራ ሰፊ ነው፡፡ አሁን ብዙ ሥራዎችን ጐብኝተናል ከዚህ ቀደምም ጐብኝተናል ገና ያልጐበኘናቸውም ሥራዎች አሉ፡፡ ለቤተክርስቲያናችን ከተሰጡት መንፈሳውያን ሀብቶች አንዱ ቋንቋ ነው፡፡ ሐዋርያት ቋንቋ ተገልጾላቸው በየሀገሩ ቋንቋ አስተምረዋል፡፡ ሰው በሚረዳው ቋንቋ ትምህርት ያስፈልገዋል፡፡ ብሔራዊ ቋንቋዎችን አማርኛ ቢሆንም እንኳን ማንኛውም ሰው በሚሰማው ቋንቋ ማገልገል የቤተክርስቲያናችን ግዴታ ነው፡፡ ቋንቋ ያገናኛል፣ ቋንቋ ያግባባል፣ ቋንቋ ያቀራርባል፡፡
በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጥረት እየተሰጠ ያለው የቋንቋ ትምህርት በጣም ያስመሰግናል፡፡
እናንተም ተማሪዎች የዲቁናውን፣ የቅስናውን ሙያ አጥንታችሁ ቤተክርስቲያንን ልታገለግሉ ይገባችኋል፡፡ በዚህ አካባቢም ሆነ በጂማ አካባቢ ያላችሁ መምህራን እነዚህን ልጆች ማሠልጠን ሀገሪቱን መርዳት ስለሆነ ትልቅ ዋጋ አላችሁ፡፡
ሃይማኖታችሁን ስለጠበቃችሁ ትመሠገናላችሁ በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ለአዳሪ ት/ቤቱ 50ሺ ብር ዕርዳታ ሰጥተዋል፡፡
ከዚያም ቅዱስነታቸው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ከአበልቲ 25 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው የናትሪ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ደጆችሽ አይዘጉ የተባለው በጐ አድራጊ ማህበር የገንዘብ፣ የጊዜ፣ የዕውቀት የጉልበት አስተዋፅኦ በማድረግ ያስገነባውን የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ህንፃ ባርከው ሪቫኑን በይፋ በመቁረጥ የምረቃ መርሐግብር ተከናውኖአል፡፡ በካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ህንፃ ምረቃ ወቅትም በማሠልጠኛው የሚማሩ ደቀ መዛሙርት በተለያዩ የአካባቢው ሕዝብ ቋንቋዎች የተሰማቸውን ደስታ እና ምስክርነትም ሰጥተዋል፡፡ በልዩ ልዩ ቋንቋ መልእክት ያስተላልፉ የነበሩት ደቀ መዛሙርት “በጨለማ ይኖር የነበረ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ” የሚለውን የምሥጢረ ሥጋዌ (የተዋሕዶ) ምስጢር ያለበትን ቃል የገለፁ ሲሆን እንደዚሁም በነቢዩ ኢሳይያስ አንተን ተስፋ የሚአደርጉ አያፍሩም በማለት የምዕመናንን ልብ የሚነካ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር አብረው ከመጡት ብፁዓን አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ አብርሃም የምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተሰማቸውን መንፈሳዊ ሐሴት በገለፁበት ጊዜ “በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ” በሚል የመጽሐፍ ቃል ጀምረው ማብራሪያ ሲሰጡ መስማት ራሱን የቻለ ነው፡፡ ማየት ደግሞ ራሱን የቻለ ነው፡፡ አንድ ነገር ከሆነው በላይ ገኖ፣ ከብሮ ይነገርለታል፡፡ በጂማ ሀገረ ስብከት ብዙ ሰምተናል፡፡ ስናየው ደግሞ ከሰማነው በላይ ነው፡፡ ወደ ሀገረ ስብከቱ ጎራ ካልን ብዙ እናያለን፡፡
በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ሀገረ ስብከት የለውን አሠራር ከመስማት አልፈን በዐይናችን ስላየን እጅግ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ቤተክርስቲያን የማትዘጋ መሆንዋን እያየን ነው፤ ቤተክርስቲያን በልጆቿ ትኮራለች፡፡ ይህ ማሠልጠኛ በየቋንቋው ትምህርት መሰጠቱና መነገሩ በዓለ ጰራቅሊጦስን ያስታውሳል፡፡ ደጆችሽ አይዘጉ የሚለውን በተግባር ስለገለፃችሁት እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ይህ ውጤት በቀላሉ ሊመጣ አይችልም፡፡ የገጠሪቱ ቤተክርስቲያን ፊደል ባታስቆጥረን ኑሮ ብፁዓን መባል ቅዱሳን መባል አይኖርም ነበር፡፡ ይህ ቦታ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ ለአገልግሎት የተመቸ ነው፡፡ በማለት ብፁዕ አቡነ አብርሃም መልእክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው እንዲህ አይነቱን ሥራ ነው፡፡ ልጆች ሃይማኖታቸውን የሚማሩበት ሥራ ተሠርቶ ሥናይ ሁላችንም ተስፋችን ይለመልማል፡፡ ይህንን ሥራ በመሥራት ቤተክርስቲያንን ያስመሰገናችሁ ልጆቻችን እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ሥራ እያደገ እንዲሄድ ያስፈልጋል፡፡ የተቸገሩት እንዲረዱ፣ ሰባኪ የሌላቸው ሰባኪ እንዲአገኙ እንመኛለን፡፡ ቤተክርስቲያን የተለየ ካዝና የላትም፤ ካዝናዋ ምዕመናን ናቸው ምዕመናን በዚህ ማሠልጠኛ ልጆቻችሁን አስተምሩ እግዚአብሔር ይባርካችሁ በማለት ቅዱስነታቸው በናትሪ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል የተገነባውን የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም የምረቃ መርሐ ግብር በጸሎት አጠናቅቀዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን በጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በሳል እና ጠንካራ አመራር ሰጪነት እየተሠራ ያለው የመልካም አስተዳደር፣ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ፣ ሁለገብ የልማት ሥራ በእጅጉ የሚአስደስት መሆኑን ከቦታው ድረስ በመሄድ ለመረዳት የቻለ ሲሆን በተመለከትናቸው ቦታዎች ሁሉ የተለያዩ የፍራፍሬ፣ የንብ እርባታ እና መሰል የልማት ሥራዎች መስፋፋታቸው ቤተ ክርስቲያናችን ከተረጅነት ተላቃ ለሌላውም ምሳሌ የሚሆን ተግባር እየፈጸመች ያለች መሆንዋን ለመገንዘብ ዕድሉ ገጥሞናል፡፡
ከቅዱስ አባታችን ጀምሮ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በምዕመናን እና በተለያዩ ምሁራን ምስጋና የተቸራቸው የልማት አርበኛው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የልማት ጀግና ከመባላቸውም በተጨማሪ ለተራቡ፣ ለታረዙ፣ የሚአዝኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ የተሰጣቸው አባት ሲሆኑ ለሚሠራ ሰው የሠራውን ያህል ደመወዝ እንዲሰጠው ባለመታከት የሚጥሩና የሚግሩ አባት በመሆናቸው እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመናቸውን እንዲአረዝም እንመኛለን፡፡
በሌላ ዜና
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በአድአ ወረዳ ሥር የሚገኘው የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የቅዳሴ ቤት በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር ዕንግዶች እና በርካታ ማህበረ ምዕመናን በተገኙበት ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2006 ዓ.ም በታላቅ ደምቀት ተከብሯል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አዲሱን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ከባረኩ በኋላ በዓውደ ምህረቱ ላይ በተደረገው መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ከሁሉ በፊት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፣ እንደ እግዚአብሔር መመሪያ ሰጪነት ለዚሁ ጊዜና ሰአት ስላደረሰን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡ ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን፡፡ በዚሁ ጊዜና ሰአት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በመካከላችን ተገኝተው ጥሪአችንን ሰምተው፣ የሕዝቡን ጥሪ፣ የሀገረ ስብከቱን ጥሪ አክብረው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመካከላችን ስለተገኙ በራሴና በሕዝቡ ስም ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ይህንን ቅዱስ ቦታ ለማግኘት በብዙ ውጣ ውረድ፣ በብዙ ድካም ከቦታው ጀምሮ እስከ ህንፃው ድረስ ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋራ በመነጋገር ይህንን ቅዱስ እና ማዕከላዊ ቦታ ከማስገኘትም በላይ ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑን አሳንፀው ለዚህ ክብር ያበቁ ምዕመናንን በቅዱስነትዎ ፊት እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡ በብዙ ልፋት፣ በብዙ ውጣ ውረድ፣ በብዙ ድካም ማዕከል የሆነ ቦታ አስገኝተው በሕይወት አሁን በመካከላችን ያልተገኙ ወደ እውነተኛው ቦታ የሄዱ ወደፈጣሪያቸው የተጓዙ ስላሉ ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
ስለዚህ ይህንን ህንፃ ቤተክርስቲያ አንፃችሁ ወጥታችሁ፣ ወርዳችሁ፣ ደክማችሁ ለዚህ ጊዜ የደረሳችሁ ምዕመናን እንኳን ደስ አላችሁ እላችሁአለሁ፡፡
ቅዱስነተዎ መንበረ ፕትርክናውን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ አቅጣጫ እየመጡ ሲጐበኙን የቆዩ ቢሆንም ይህ ታላቅ አገልግሎት ግን ለመጀመሪያ ጊዘ ስለሆነ ቅዱስነተዎንም እንኳን ደስ አለዎት እላለሁ፡፡ ጊዜው የምስጋና ጊዜ ነው፣ ሌሊቱም የምስጋና ሌሊት ነው፤ ለዚሁ የምስጋና ጊዜ ያደረሰን እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን በማለት ብፁዕነታቸው የዕንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸውን አጠናቅቀው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመጨረሻውን ቡራኬ እና ቃለ ምዕዳን፣ መመሪያ እንዲሰጡ ጋብዘዋቸዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “ተፈሳህነ ወተሀሰይነ በኩሉ መዋዕሊነ ወተፈሳህነ ህየንተ መዋዕል ዘአህመምከነ ወህየአተ ዓመት እንተርኢናሃ ለእኪት” ነቢዩ ዳዊት በደረሰው ድርሰት ፈጽሞ ደስ አለን ደስታችንም ከፍተኛ ነው፣ ለደስታችን ወሰን የለውም፣ ብዙ ደክመን፣ ብዙ ተቸግረን ነበርና በማለት እንደገለፀው እናንተም ቤተክርስቲያንን ለመሥራት ወጥታችሁ ወርዳችሁ ለዚህ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ እኛም ዛሬ የእናንተ ደስታ ተከፋዮች ስለሆን ደስ ብሎናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ደስታ እድሜ ይጨምራል፡፡
ይህ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን አምሳያ የለውም ይህ ግሩም ህንፃ ቤተክርስቲያን የተሠራው ፈቃደ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው፡፡ የሠራችሁትም በጉልበታችሁ፣ በዕውቀታችሁ እና በገንዘባችሁ ስለሆነ ሁልጊዜ ስትደሰቱ ትኖራላችሁ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ንብረት ነው፡፡ ከብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ጋር ሆናችሁ ይህን ቤተ ክርስቲያን ስለ ሠራችሁ እግዚአብሔርን ደስ ይለዋል፡፡ መመስገኛው ስለሆነ፤ በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል ስም የሠራችሁት ቤተክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን የምትቀበሉበት፣ ወጣት ልጆቻችሁ ጋብቻ የሚፈጽሙበት፣ ክርስትና የምትነሱበት፣ ከዚህ ዓለም ስትለዩ በክብር የምትሸኙበት ስለሆነ በጣም ደስ ሊላችሁ ይገባል፡፡
እግዚአብሔርም ጥረታችሁን እና ልመኛችሁን ስለሰማ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ቤተክርስቲያን እናንተን በማግኘቷ ባለፀጋ ናት፡፡ ይህን ቤተክርስቲያን ለመሥራት የቻላችሁት እምነታችሁ የፀና ስለሆነ ነው፡፡
ለወደፊቱ ትምህርት ቤት፣ ማሠልጠኛ፣ ተግባረዕድ ልትሰሩበት ትችላላችሁ፡፡ እኛም ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ ስላደረጋችሁልን አቀባበል በጣም እናመሰግናለን፡፡ የሃይማኖት አባት ማክበር ሃይማኖታዊ እና መንፈሳዊ ግዴታችሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡
ይህ ህንፃ ቤተክርስቲያን በዛሬው ዕለት ከተራ ህንፃነት ወደቅዱስነት ተለውጧል፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ይቀደስበታል፣ ቅዱስ ቁርባን ትቀበሉበታላችሁ በሥርዓቱ መሠረት በሜሮን እና በውሀ ተባርኮ ሥርአተ ቤተክርስቲያን ተፈጽሞበታል፡፡ ቅዱስ ቦታ ሆኗል በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ አባታዊ መልእክት አስተላልፈው የዕለቱ መርሐ ግብር የተጠናቀቀ ሲሆን በማግሥቱ ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በአዲሱ ህንፃ ቤተ መቅደስ የቅዳሴ ቤቱ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ {flike}{plusone}