ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ

የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር፤ 13ኛ ዓመት ዕረፍት ነሐሴ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በመንበረ ጻባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
ልደት፣ ዕድገትና ትምህርት
ቅዱስነታቸው ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ክፍለ ሀገር በዐድዋ አውራጃ በመደራ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ አራደች ተድላ ተወለዱ፡፡ ከስድስት ዓመታት ዕድሜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የአበው መነኮሳትን ሥርዓት የተከተለ ገዳማዊ ኑሮን በአባ ገሪማ ገዳም እያጠኑ አባቶችን እያገለገሉ አደጉ፡፡ ቀጥሎም ትምህርታቸውን በበለጠ ለማስፋፋት በጭህና በአባ ሐደራ ገዳማት በመዘዋወር ከመምህር ወልደ ሐዋርያት፣ ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር፣ ከመምህር ኪዳነ ማርያም፣ ከመምህር ጳውሎስ፣ ከመምህር አምሳሉ፣ መምህር ገብረ ማርያም ከሚባሉ መምህራን ጸዋትወ ዜማን መዝገብ ቅዳሴን፣ ግዕዝ ሰዋሰውን በሚገባ ተምረዋል ፡፡
ማዕረገ ክህነት
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ዲቁናን ከአቡነ ማርቆስ፣ ምንኩስናን ባደጉበት በአባ ገሪማ ገዳም ቅስናን ከአቡነ ይስሐቅ ተቀብለው ገዳማዊ አገልግሎታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ በ1949 ዓ.ም. ገዳሙን አስፈቅደው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት በነበሩት በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፣ የሐረርጌ ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ፕሬዚዳንት በነበሩት በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በአዳሪነት ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን በመከታተል የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ በቆዩባቸው ዓመታት ይሰጥ የነበረውን ትምህርት በመከታተል ከቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሽልማትን አግኝተዋል፤ ንጉሠ ነገሥቱ ተማሪዎቹን ለመጎብኘት በመጡ ቁጥር ቅዱስነታቸውን ያነጋግሩአቸውና ያበረታቷቸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ፡፡
የውጭ ሀገር ትምህርት
ቅዱስነታቸው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት እንዳጠናቀቁ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያና በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዘሐረርጌ ፈቃድ የትምሀርት ዕውቀታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያሻሽሉ ወደ ውጭ ሀገር ወደ አሜሪካ ተላኩ፡፡ በአሜሪካ ሀገር በትምህርት በቆዩባቸው ዓመታትም በተለያዩ ዕውቅና ባላቸው ዩኒቨርስቲዎች፤በቅዱስ ቪላዲሚር ራሽያ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት በዲፕሎማ፤ ከየል ዩኒቨርስቲ በርክሌይ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ባችለር ኦፍ ድቪኒቲ ዲግሪ፣ ከፕሪስተን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምሀርት ቤት ማስተር ኦፍ ቲዮሎጂ፣ ከፕሪስተን ዩኒቨርስቲ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን ከፍተኛ የመጨረሻ ዶክትሬት ዶክተር ኦፍ ፊሎሶፊን አግኝተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በቋንቋ ረገድም ግዕዝ፣ትግርኛ፣አማርኛ በሚገባ ያውቃሉ፤በውጭ ሀገር ዓለም አቀፋዊ ቋንቋዎችም እንግሊዝኛ፣ጀርመንኛ፣ፈረንሳይኛ የሚናገሩ ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ ለምርምር ያህል፣ዕብራይስጥ፣ግሪክኛና ላቲን በመጠኑ ያውቁ ነበር፡፡
የምንኩስና ሕይወት አገልግሎት
ቅዱስነታቸው ከሕፃንነት ዕድሜ ጀምሮ ሥርዐተ ምንኩስናን በተቀበሉበት በመደራ አባ ገሪማ ገዳም፣በገዳሙ ቤተ ማኅበር ውስጥ እንጀራ በመጋገር፣ በአጠቃላይ ከገዳሙ አርድእት አንዱን በመሆን በተጠሩበት ሁሉ ፍጹም ታዛዥነታቸውን በማሳየት ከዐሥራ አምስት ዓመታት ያላነሰ በዲቀና፣ በምንኩስና፣ በቅስና አገልግለዋል፡፡
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ በትምህርት ገበታ ላይ በነበሩበት ጊዜም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፈቃድ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መደበኛ ቀዳሽ በመሆን ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክና በድርሰት፣ በስብከተ ወንጌል በጋዜጣ ዝግጅትና በሬድዮ ክፍል የበላይ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የስደተኞች ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊና የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነርም ሆነው አገልግለዋል፡፡
የውጭ ሀገር አገልግሎትም ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተክርስቲያናችን ወኪል ሆነው እንዲያገለግሉ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ በታዘዙት መሠረት፤ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል፤ በአኀት አብያተ ክርስቲያናት ቋሚ ኮሚቴ፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ባይብል ሶሳይቲ፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የከተማና የኢንዱስትሪ ተልእኮ፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር እምነትና ሥርዓት ኮሚሽን፣በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የመካከለኛ ኮሚቴ አባል በመሆን ተመርጠው አገልግለዋል፣በተሰበሰቡት የመካከለኛ ኮሚቴ ስብሰባዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመልእክተኛነት ደረጃ አገልግለዋል፡፡
ኤጲስ ቆጶስነት
ለውጭ ሀገር አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት አገልግሎት አንድ ኤጲስ ቆጶስ መርጦ መሾም አስፈላጊ በመሆኑ፤ በግብረ ገብነታቸውና በትምህርታቸው ከታወቁት መነኰሳት መካከል አባ ገብረ መድኅን ገብረ ዮሐንስ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከሌሎች ሁለት አበው መነኰሳት ጋር መስከረም 16 ቀን 1968 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ እድ የኤጲስ ቆጶስነቱ በዐለ ሢመት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ተከብሮ ስማቸውም “ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ” ተብሎ ተሰየመ፡፡
ሐዋርያዊ አገልግሎት በእስር ቤት
ቅዱስነታቸው በደርግ መንግሥት ወደ እሥር ቤት መግባታቸው ይታወቃል፤ ሁኖም በመታሠራቸው ሃይማኖታዊ ሥርዐታቸውን አላቋረጡም፤ በእስር ቤት ወንጌልን በመስበክ የብዙዎችን ሕይወት ቀይረዋል፡፡ ይልቁንም ከ500 በላይ የሚሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን በልዩ ዘዴ ተጻጽፈው ወደ እስር ቤት በማስገባት ለእስረኞቹ አድለዋል፡፡ የራሳቸውን ችግርና መከራ ሳያስቡ በእስር ቤት ያሉ ወገኖቻቸው እንዲጽናኑና መከራውን እንዲታገሡ ሲያስተምሩና ሐዋርያዊ ተልእኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተው ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ በደል ሳይፈጽሙ መታሰራቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ተሰጥቷቸው በነጻ ተለቀዋል፡፡
ሐዋርያዊ አገልግሎት በሰሜን አሜሪካ
በወታደራዊው ዘመነ መንግሥት ቅዱስነታቸው ወገኖቻቸው ተሰደው ወደሚገኙበት ሀገር ከሔዱ በኋላ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምእመናንን በማሰባሰብና በማጽናናት ትምህርተ ወንጌልን በበለጠ በማስፋፋት ሐዋርያዊውን አገልግሎት አጠናክረው ቀጠሉ፤ በዚሁ መሠረት፡- የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በኒውዮርክ፤ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዳላስ ቴክሳስ፣ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ፤የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ፤የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በፊኒክስ አሪዞና፤የቅድስትሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በታምፓ ፍሎሪዳ፤የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በላስ ቬጋስ ነባዳ በሥነ ሥርዓት አቋቁመው እስከ አሁን ድረስ ምእመናን ምእመናት እየተገለገሉባቸው ይገኙሉ፡፡
ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮ በበለጠ ለማጠናከርና አምልኮተ እግዚአብሔርን ለማጽናት ሃይማኖታዊ ባህልን ጭምር ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፡- የመድኃኔ ዓለም፣የቅድስት ማርያም፣ የኪዳነ ምሕረት፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሚካኤልና የቅዱስ ገብርኤል መንፈሳውያን ማኅበራትን አቋቁመዋል፡፡ ከዚህ በላይ የተገለፀው ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በዲቁና በምንኩስና፣ በቅስና በሊቀ ጳጳስነት ሕይወት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቆይታቸው ከፈጸሟቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መካከል ጥቂቱን ክፍል ብቻ የሚያመለክት ሲሆን ቀጣዩ የታሪክ ይዘት ወደ ፓትርያርክነቱ ሥልጣን የመጡበትንና ከትልቁ ሥልጣን ባሻገር ያከናወኗቸውን ተግባራት ከዚህ እንደሚከተለው እንመለከታለን ፡፡
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ
አምስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር ለማግኘት አፈጻጸሙ የጠየቀው መሥዋዕትነት ከባድ እንደነበር ቢታወቅም ፈተናውንና መሰናክሉን ሁሉ በማለፍ በሀገር በቀል እና በዓለም አቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውን ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ሊቀ ጳጳስ ሁሉንም አሟልተው የተገኙ በመሆናቸው ሰኔ 28 ቀን 1984 ዓ.ም. አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደር እንዲመሩ ተመረጡ፡፡
የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት
ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ከሆኑበት ጊዜ አንሥቶ ወንጌልን በማስፋፋት የቤተ ክርስቲንን አስተዳደር ለማጠናከርና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማስፋት ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኰሌጅ፣ የፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኰሌጅ እንዲከፈቱ አድርገዋል፤ በደርግ መንግሥት ተወርሰው የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎችንና ንብረቶችን እንደገና ለማስመለስ ችለዋል፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ብዙ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን መርቀው ከፍተዋል፤ የቤተ ክርስቲያኗን የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆ ከማስፋት አኳያም በመላው ዓለም ተዘዋውረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከትን በመጎብኘት መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኦርየንታል ኦርቶዶክስ፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ እንዲሁም ከሌሎች የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠነክር ያላሰለሰ ጥረትን አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔን ለመሻት የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች ከኤርትራ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ለሰላም ውይይት፡- በኦስሎ -ኖርዌይ፣ በጀርመን – ፍራንክፈርት፣ በአሜሪካ – ኒውዮርክ፣ በናይሮቢ – ኬንያ በተደረጉ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን የሃይማኖት መሪዎቸ ስብሰባ መርተዋል፡፡ በኒውዮርክ በተባበሩ መንግሥታት በተካሔደው የሃይማኖትና የመንፈሳዊ መሪዎች ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳትፈዋል፡፡ በዋሽንግተን አሜሪካ በኋይት ሐውስ በተካሔደው የዓለም የኤድስ ቀን ስብሰባ ተገኝተዋል፡፡ ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔርን ቃል በማሰራጨት ኤድስን ለመቋቋም ያላሰለሰ ጥረትን ማድረጋቸው ተገልፃል፡፡ የሰላምንና የስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የናንሰን ሜዳይ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኰሚሽን ተሸልመዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ዘመነ ክህነት የሀገርና የዓለም አቀፍ ይዘቷን እያጠናከረችና እያሰፋች የመጣችበት ወቅት በመሆኑ፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ስላለባት ቅዱስነታቸው ዘወትር በቢሮ ከሚያከናውነው የሥራ ፕሮግራም ባሻገር፣ ከውጭው ክፍለ ዓለም ጋር በመገናኘት ስለሀገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን፤ ስለዓለም ሰላም፣ ስለሰው ልጅ ደኅንነት፣ ዓለሙ በሚያውቀውና በሚገባው ቋንቋ በማስተማር ከአኅትና ከሌሎቹም ቀረቤታ ካላቸው፤ ከሌላቸው አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎችም የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ወደየአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በየገዳማቱና አድባራቱ እንዲሁም በገጠር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ከቤተ መቅደሱ ክህነታዊ አገልግሎት ጀምሮ በሚሰጡት ቀኖናዊ መመሪያ፤ አባታዊ ቡራኬ፣ ቃለ ምዕዳንና ትምህርተ ወንጌል፤ካህናት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸው፤ምእመናንም በእምነታቸውና በአንድነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖተ ምግባር እንዲጸና ሀገር እንዲለማ በማድረግ፣ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፤ወጣቶች ከአበው የተቀበሉትን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖቱንና ሥርዓቱን ጠብቀው በትምህርትና በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከሩና ማስፋፋቱ፤የሰው ዘር ሁሉ ከረሀብ፣ከእርዛት፣ከበሽታና ከድንቁርና ተላቆ በሰላም፣ በአንድነት በመተሳሰብና በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማድረግ፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሩን ማመቻቸት፤የሰበካ ጉባኤን ማጠናከር፤የቤተ ክርስቲያኒቱን የዓለም አቀፉን ግንኙነት ማጠናከሩ፤በተለያየ ምክንያት ከየሀገራቸው የወጡትን፣የተሰደዱትን በያሉበት መርዳቱና ማጽናናቱ፤የተቸገረ እንዲረዳ፣ሰብሳቢ ያጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት፣ በአንድነት ተሰባስበው እየተረዱ፤ እየተማሩ እንዲያድጉ ማድረግ፤ የፈረሰ፣ የተጎሳቆለ፣ የተጎዳ ቤተ ክርስቲያን እንዲታደስ፣ እንዲጠገን፣ አዳዲስም እንዲሠራ ማድረግ የቅዱስነታቸው የዘወትር ተግባር ነበር፡፡
ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ በመንበረ ፓትርያርክ ቅጽረ ግቢ የሚገኘውን ታሪካዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በታሪካዊነታቸው፣ በይዘታቸው፣አቻ የሌላቸው የሀገር ቅርስ እንዲጠበቅ በማድረግ፤ ትምህርት ቤቶች እንዲሰፉ፤ቅዱሳት መጻሕፍት ከየዓይነታቸው በብዛት እየታተሙ እንዲሰራጩ፤ ሐዋርያዊ ተልዕኮ እንዲፋጠን ወጣቱ ትውልድ በሃይማኖት እንዲታነጽ፣ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝባቸውን ወገኖች እንዲረዱ፣ ሰላም በሀገራችን፣ በአካባቢያችንና በዓለሙ ሁሉ እንዲሰፍን ቅዱስነታቸው ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጠንካራ ሥራ ከሀገር፣ ከአህጉርና ከወገን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን አግኝቶ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የናንሰን ሜዳይ ተሸልመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሁነው እንዲሠሩ በአንድ ድምፅ በዓለሙ ኅብረተሰብ ተመርጠዋል፤ እንዲሁም ቅዱስነታቸው በኢየሩሳሌም “ቅዱስ ዮሐንስ የማልታ ክርስቲያናዊ ንቅናቄ” ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ታላቁን ባለክንፍ መስቀል ኒሻን ተሸልመዋል፡፡
የቅዱስነታቸው ዕረፍት
በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሕያው ሁኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው?” /መዝ. 88፡48/ ብሎ እንደተናገረው ቅዱስነታቸው በጾመ ፍልሰታ ለማርያም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመቀደስና ሐዋርያዊውን ተልዕኮ በመፈጸም አንደኛውን ሱባኤ ካጠናቀቁ በኋላ፤ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በዐሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሔደው በመታከም ላይ እንዳሉ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
የቅዱስነታቸው አስከሬን ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በመላ ሕዝበ ክርስቲያን ታጅቦ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ከተደረገ በኋላ በዚሁ ካቴድራል ሥርዓተ ጸሎቱ ሲፈጸም አድሮ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤የሃይማኖት መሪዎች፤ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ከውጭ ሀገር የመጡ እንግዶች፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች፤የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተጠሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ዘመድ ወዳጆቻቸው በተገኙበት ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት የቀብሩ ሥነ ሥርዐት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
የቅዱስነታቸው በረከት ይደርብን!
©EOTC TV