ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በግብፅ ካይሮና በእስክንድርያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው አዲስ አበባ ገቡ

28690

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቷን ልዑካን አስከትለው በመጐብኘት የ6 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ግብፅ ካይሮ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ፣ የግብፅ ገዳማትና አድባራት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ አምባሳደር መሐመድ ድሪር እንዲሁም የካይሮ መርሶ ሕይወት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በካይሮ መንበረ ማርቆስ የእንኳን ደህና መጣችሁ ደማቅ አቀባበል ተደርጉላቸዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ በግብፅ ውስጥና በውጭም የሚኖሩ ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት እንዲሁም መነኮሳት የተገኙ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቦታው ሲደርሱ በቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ታዋድሮስ መሪነት የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሐ ግብር በደማቅ ፓትርያርካዊ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
በዚህ መርሐ ግብር የተለያዩ የምስጋና መዝሙሮች አክብሮታዊ ቅኔዎች ከቀረቡ በኋላ ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች ንግግር አድርገዋል፡፡
በመጀመሪያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የንግግራቸው ዋና ዋና ሐሳቦችም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
ቅዱስነትዎ ፕትርክናዊ ጉብኝት በግብፅ በመጀመርዎ እጅግ በጣም ደስ ብሎናል ሀገራችንም ትባረካለች፡፡ ይህን የቅዱስነትዎን ሐዋርያዊ ጉብኝት በእጅጉ ስንናፍቀው የቆየን ስለሆነ ግብዣችንን ተቀብለው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለመባረክ እንኳን ወደ ሁለተኛ ቤትዎ በሰላም መጡ፡፡ ሁለቱም አኀት አብያተ ክርስቲያናት የቆየ የግንኙነትና የአብሮነት ታሪክ ያላቸው ስለሆኑ አሁንም ይህንኑ የቆየ መልካምና መንፈሳዊ ግንኙነታችንን አጠናክረን መቀጠልና ማስቀጠል እንፈልጋለን፤ ይህም ደግሞ በቅዱስነትዎ መልካም ፈቃድ ይሳካል ብለን እናምናለን$ ካሉ በኋላ በግብፅ ሕዝብ ስም የእንኳን ደህና መጣችሁ ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በበኩላቸው አስቀድመው ከአየር ማረፊያ ጀምሮ ስለተደረገላቸው የአቀባበል ሥነ ሥርዓትና አክብሮት ከፍ ያለ ምስጋና ካቀረቡ በኋለ በዚህ የአቀባበል መርሐ ግብር ለተሰበሰቡት ሊቃነ ጳጳሳት፣ መነኮሳትና ካህናት እንዲሁም በተለያዩ የግብፅ ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት ይከታተል ለነበረው ሕዝብ ሰፊ ፓትርያርካዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በመግለጫቸው በዋናነት ትኩረት የሰጡት የሁለቱ ሀገራትና የሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ የቆየ ግንኙነት ታሪክን በመጥቀስ ሰፊ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ የቅዱስነታቸው ዋና ዋና ሐሳቦች እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንደ እንግዳ ደራሽ ዛሬ የተጀመረ ክስተት ሳይሆን በሃይማኖታዊና በማኅበራዊ መስተጋብሮት የተሰናሰለ መሠረቱ በጽኑ አለት ላይ የተገነባ እሴት ነው፡፡ በሃይማኖት በኩል ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያህል አንድ ዓይነት እምነት ተቀብለን፣ አንድ ዓይነት ሥርዓትና ቀኖና አክብረን የኖርን መሆናችንን ታሪክ የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከእስክንድርያ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት እየተላኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያገለግሉ እንደነበርና ሁለታችንም የአንድ አባት የቅዱስ ማርቆስ ልጆች መሆናችን የጠንካራ መንፈሳዊ ግንኙነታተን ምስክር ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ጉዳይ የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ ሁላችንም ከአንድ ዓባይ የሚመነጭ ውሃ የምንጠጣ ሕዝቦች ነን፡፡ የምንለያይበት ምንም ነገር የለንም፡፡ ሁላችንም አንድ ሕዝቦች ነን፡፡ ዓባይ የእግዚአብሔር ጸጋ ሆኖ ለፍጡራን ሁሉ የተሰጠ በረከት ነው፡፡ ይህ የአምላክ በረከት ደግሞ ፍጡራን ሁሉ በእኩለነት የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ እንኳንስ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን እኛ፣ እንስሳትና እፀዋት እንኳ ከዚህ የፈጣሪ ጸጋ የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ ስለሆነም ይህ የአምላካችን በረከት የሆነው የማያቋረጥ የጋራ ሀብታችንን በፍትሐዊነትና በእኩልነት መጠቀም ግዴታችንም ጭምር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል$ ብለዋል፡፡

128690

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሆንና የኮፕት ኦርቶዶክስ መሆን የአፍሪካ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ቢሆኑም እንደ ጥንታውያንነታችን ግን ግንኙነታችንን አጠናክረን ጐልቶ ሊታይና ሊጠቀስ የሚችል ሥራ ልንሠራ አልቻልንም፡፡ ስለዚህ ይህን ታሪካችንና ትውፊታችን በዓለም ላይ ደምቆ እንዲታይ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የቆየ ግንኙነታችን ይበልጥ ማጠናከርና የጋራ በሆኑ ተልዕኮዎቻችን የሠመረ ሥራ ለመሥራትም የጋራ ኮሜቴ ማቋቋም ይኖርብናል$ ካሉ በኋላ ደግመው ደጋግመው ለግብፅ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ለኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምዕመናን በአቀባበሉ ሥነ ሥርዓት ስለተደረገላቸው ሁለገብ የአክብሮት አቀባበል ምስጋና በማቅረብ መግለጫቸውን ጨርሰዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ በመቀጠል የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ንግግር አእምሮን የሚያሰደስት፣ ልብን የሚያረካ መሆኑን በሰፊው ከገለጹ በኋላ በጋራ ለመሥራት በኮሚቴነት የሚመሩ አንድ ሊቀ ጳጳስ ሰይመው የትምህርተ ሃይማኖት፣ በገዳማዊ ሕይወት፣ በጤናና በማኅበራዊ ጉዳየች አብረው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በወጣላቸው መርሐ ግብር መሠረት በግብፅ ካይሮና እስክንድርያ የሚገኙ ጥንታውያን ገዳማት፡- የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን፣ የአባ መቃርስ ገዳም፣ የአባ ሚናስና ሌሎች ጥንታውያን ገዳማትን የጐበኙ ሲሆን በጐበኙአቸው ገዳማት ሁሉ ጸሎትና በገዳሙ ለተገኙ ገዳማውያን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ገዳማውያኑም በቅዱስነታቸው ጉብኝት በጣም መደሰታቸውን እየገለጹ ለማስታወሻነት እንዲሆን የገዳሙን ታሪካዊ እሴት የሚገልጹ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከገዳማትና ከኮፕት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ በተጨማሪ የግብፅ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የእስለምና ሃይማኖት መሪ ጋር በሁለቱም ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በመጀመሪያ ከግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ኢንጅነር ኢብራሂም መህሊብ ጋር ተገናኝተው በሁለቱም ሀገራት መልካም ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱም ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቀድመው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ማርቆስ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር እጅግ ልብን የሚማርክ አባታዊ፣ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ንግገር ስለሆነ በዚሁ አጋጣሚ አክብሮቴን እገልጻለሁ፡፡ የሃይማኖት መሪዎች የሰላም መልእክተኞች መሆናቸውን እርስዎ አስመስክረዋል፡፡ የኢትዮጵያን እድገትና ልማት እንፈልጋለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በልማቶቹ ላይ ተሳታፊ መሆን እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይን ገድባ መብራት እንድታገኝ ከመደገፍም አልፈን እንሳተፋለን፡፡ ሆኖም ግን የውሃው መጠን እንዳየቀንስብን አደራ በማለት ገልጸውላቸዋል፡፡

ቅዱስነታቸው በበኩላቸው ከላይ እንደገለጹት ዓባይ የፈጣሪ ጸጋ ስለሆነ ለሁሉም እንደሚበቃና በፍቅር፣ በመስማማት፣ በመተማመን ከተጠቀምንበት እንኳንስ ለእኛ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚበቃ የአምላክ በረከት ነው፡፡ ስለዚህም የሚቀንሰውም ሆነ የሚያስቀረው የለም በዚህ ልትተማመኑ ይገባል በማለት አስረድተዋቸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከዚህ በመቀጠል የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት አብደ ኤልፍታሕ አልሲሲ አግኝተው በተመሳሳይ አጀንዳ የተወያዩ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ለፕሬዚዳንቱ #የግብፅና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚሆኑት የእግዚአብሔር ጸጋ በሆነው በዓባይ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ደግሞ ሰው ሊለያየው አይችልም$ በማለት የገለጹላቸው አገላለጽ በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ከግብፅ የእስልምና ሃይማኖት መሪ (የታላቁ አልአዝሐር መስጊድ ኢማም) ከሸክ መሐመድም አልጠይም ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ስላለው የሃይማኖቶች መቻቻልና ተምሳሌታዊ ፍቅር እንዲሁም ተቋም መሥርተው የጋራ በሆኑ ጉዳዮቻቸው አብረው እንደሚሠሩ የሃገራችንን ልምድ አንስተው ገለጻ ያደረጉላቸው ሲሆን፣ የግብፅም ተመሳሳይ ዓይነት አሠራር መኖሩን አስረድተዋቸዋል፡፡
ይህንን ጉብኝ የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሐመድ ድሪር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጉብኝት በሁለቱም ሀገራት የነበረውን ጥንታዊና ታሪካዊ ግኑኝነት ይበልጥ ወደ ከፍተኛ ወንድማማችነትና ወደ ከፍተኛ መተማመን የሚያመራ የፍቅር ተምሳሌት ሆኖ የሚያገለግል ነው በማለት የቅዱስነታቸው ጉብኝት ጠቀሜታ ቅዱስነታቸው በሚሸኙበት ጊዜ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ በ2008 ዓ.ም. የበመስቀል ደመራ በዓል ላይ እንዲገኙ ግብዣ ያደረጉላቸው ሲሆን በቀጥታ ሥርጭትም ለመገናኛ ብዙኀን የጋራ መግለጫ ከሰጡ በኋላ የጋራ ጸሎት በማድረግና ሻማ በመለኮስ የጉብኝቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡
ምንጭ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ልዩ ጽ/ቤት ድረ-ገፅ

{flike}{plusone}