ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች እግዚአብሔር ዝናመ ምሕረቱን እንዲያወርድ እና ወርሐ ክረምቱ የተባረከ እንዲሆንልን የአንድ ሳምንት ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ አሳሰቡ
ዓመታዊ የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ በዓለ ንግሥት ሐምሌ 19 ቀነ 2007 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምያ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ አህጉረ ስብከቶችና አድባራትና ገዳማት የመጡ የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች፣ ከመላ ዓለም የተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በተገኙበት ዘንድሮም እጅግ ማራኪ በሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት ተከብሮአል፡፡
በዓሉ በተለመደው ሁኔታ ከዋዜማም ጀምሮ በሊቃውንት ያሬዳዊ ዜማና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ትምህርት እየተሰጠ የተከበረ ሲሆን ሌሊቱን በማኅሌትና በቅዳሴ በዓሉ ተከብሮአል፡፡ ታቦተ ሕጉ ሦስት ጊዜ ዑደት ካደረገ በኋላ የገዳሙ ሊቃውንትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዘምራን መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ እና የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ የዕለቱ ሰማዕታት የሆኑት ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን መነሻ በማድረግ ትምህርታቸውን የሰጡ ሲሆን ዘመኑን ማዕከል በማድረግ ታሪኩን ወደ ዘመኑ የምዕመናን ሕይወት በመመለስ ሰፊ ትምህርት እና ምክር አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ትምህርተ ወንጌል፣ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ እንዲያስተላልፉ ተጋብዘው ሕዝቡን ባርከዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በቃለ ምዕዳናቸው ትኩረት የሰጡት ማንኛውም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራዎቻችን የሠመሩ የሚሆኑት እምነትንና ሐቀኛ አሠራርን ስንከተል ብቻ መሆኑን መነሻ በማድረግ ሰፊ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል፡፡
ቀደምት የኢትዮጵያውያን መገለጫዎች የሆኑት መከባበር፣ መቻቻል፣ መፋቀር፣ መተዛዘን የመሳሰሉት ሁሉ በአንዳንድ ምክንያቶች እንዳይሸራረፉ ሁሉም ሰው ነቅቶ መጠበቅና ማዳበር እንዲሁም ለልጆቹ ማስተማር ይገባል ካሉ በኋላ እግዚብሔር በሁሉም ሀገራችን ዝናመ ምሕረቱን አውርዶ የተዘራውን አብቅሎ ለፍሬ እንዲያደርስልን፣ ወርሐ ክረምቱንም እንዲባርክልን በሁሉም አህጉረ ስብከት ዘንድ የአንድ ሱባኤ ጊዜ ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
ጸሎተ ምህላው እዚያው ቁልቢ ገብርኤል ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንዲሁም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሊቃውንትና ምዕመናን ባሉበት ቅዱስ ፓትርያርኩ አስጀምረው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት በዓሉ በጸሎት ተዘግቷል፡፡
ምንጭ:- መምህር ሙሴ ኃይሉ (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/መ/ፓ/ልዩ ጽ/ቤት ድረ-ገፅ)
{flike}{plusone}