ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዕድሳት የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዕድሳት ማስፈጸሚያ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
በዕድሳት ላይ የሚገኘው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከፍጻሜ ለማድረስ መላው ኦርቶዶክሳዊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።
የዕድሳቱን ሂደት በተመለከተ ከፍተኛ ክትትል እያደረጉ የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለዕድሳቱ ማስፈጸሚያ በግላቸው የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ በተካሄደው የርክክብ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ በግላቸው 120 ሺ ብር መስጠታቸውን ጠቁመው ቅዱስነታቸው ያደረጉት ተግባር ሌሎቻችንን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣን ቆሞስ አባ ሲራክ ቅዱስ አባታችን የካቴድራሉን ዕድሳት በተመለከተ ጥብቅ ክትትል ከማድረጋቸው ባሻገር በግል ገንዘባቸው ላደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
©eotc tv