ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2011 ዓ.ም የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

ሙሉ የቅዱስነታቸው መልእክት እንደሚከተለው ይቀርባል

ቃለ በረከት

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዐለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ በዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወአሐዱ ዓመተ ምሕረት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ዲያብሎስን ኃጢአትንና ሞትን ድል እንድንነሣ ያደረገን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

“ወለእግዚአብሔር አኰቴት ዘወሀበነ ንማዕ በእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” (1ቆሮ. 15፡57)፡፡

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የእግዚአብሔር ዓላማ በፍጡር ሤራ ሊቀለበስ አይችልም፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍጹም መልካም ስለሆነ በእርሱ የተፈጠሩ ፍጡራንም እንደዚሁ መልካም ናቸው፤ ዛሬ ርኩሳን መናፍስት ብለን የምንጠራቸው ፍጡራንም ቢሆኑ፣ ፈጣሪ የሰጣቸውን ነጻ አእምሮ በተሳሳተ መንገድ ተጠቅመው ከመውደቃቸው የተነሣ ከመልካምነት ወደርኩስነት ተቀየሩ እንጂ ጥንት ሲፈጠሩ እንደሌላው ሁሉ መልካም ነበሩ፤

እግዚአብሔር ፍጥረታትን በአጠቃላይ መልካም አድርጎ ሲፈጥር፣ ሰውን ግን በተለየ ሁኔታ በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮ፣ በአፉ እስትንፋስ አክብሮና የማይሞት ሕያው አድርጎ፣ ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች የሚገኝ ማእከላዊ ፍጡር አድርጎ ፈጥሮታል፡፡

የርኩሳን መናፍስት አለቃ የሆነው ዲያብሎስ በሰው ላይ በቅንዐት የተነሣበት ዋና ምክንያትም፣ ሰው ከፍጡራን ሁሉ በላይ ክቡር ሆኖ በመፈጠሩ ነው፤ በመሆኑም ዲያብሎስ በዚህ ቀንቶና ተመቅኝቶ ሰውን በማሳሳት፣ እግዚአብሔርን ከመምሰል ጸጋው ፈንግሎ ጣለው፤ ዲያብሎስ ሰውን አሸንፎ በመጣሉ፣ ለጊዜውም ቢሆን የማይቀለበሰውን የእግዚአብሔርን ዓላማ ያሰነካከለ መስሎ ታይቶአል፡፡

ከነገሩ ሁኔታ በግልጽ እንደሚታየው፣ ይህ ፍልሚያ በዲያብሎስና በሰው ልጅ መካከል የተካሄደ ነው፤ የውጊያው መሣሪያም ቁሳዊ ነገር ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ሞራል የማሸነፍና የመሸነፍ ጉዳይ ነው፤ ከዚህ አኳያ “መልካሙንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍእንዳትበሉ ከበላችሁ ትሞታላችሁ”  የሚል ከእግዚአብሔር ለሰው የተሰጠ ትእዛዝ በአንድ ወገን፣ የለም “ሞትንስ አትሞቱም፤ ነገር ግን ከእሱ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ ይከፈታሉ፤ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን ታውቃላችሁ” የሚል የዲያብሎስ አታላይ ምክር በሌላ ወገን፣ ለሰው ልጅ ቀርቦለታል፡፡

እነዚህ ሁለቱ እርስ በእርስ የሚቃረኑ ነገሮች፣ በሰው አእምሮ ውስጥ መፋለማቸውን ቀጥለው፣ በመጨረሻ “ብትበሉ አትሞቱም” የሚለው የዲያብሎስ ሐሳብ በሰው ዘንድ ተቀባይነትን ስላገኘ፣ መብላት አሸነፈ፤ አለመብላት ተሸነፈ፤ በውጤቱም የሽንፈቱ ኃሣር በሰው ላይ ወደቀና፣ የሰው ልጅ ክብሩን ሁሉ አጥቶ፣ በፈጸመው ጥፋት በሞት ተቀጣ፤ ይህ ሤራ በፍጡሩ በዲያብሎስ ጥበብ ተደረገ፤ ነገር ግን ከፍጡር ጥበብ ይልቅ የፈጣሪ ጥበብ ይበልጣልና፣ ለወደፊቱ ሰው ዲያብሎስን የሚያሸንፍበት ሁኔታ እንደሚመጣ፣ እግዚአብሔር ወዲያውኑ የተስፋ ፍንጭ ሰጠ፤ ተስፋው የተነገረው በራሱ በእግዚአብሔር ሲሆን፣ ጊዜውም በሰው ላይ የሞት ፍርድን ባስተላለፈበት ቅፅበት ነው፤ የተስፋው ይዘትም እንዲህ የሚል ነበር፡-

 “የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ ይቀጠቅጣል “ የሚል ነበር፤ ይህ ተስፋ በየጊዜው እየተደጋገመ ለሰው ልጅ ይገለፅ ነበር፤ ለምሳሌ “ዘርህ የጠላትን ደጅ ይወርሳል” ተብሎ ለአብርሃም፣ “አንተ የዘንዶውን ራስ ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠኻቸው” ተብሎ ለኢትዮጵያውያን ተነግሮአል፤ ይህ ዓይነት የድልና የአሸናፊነት ተስፋ በተለያየ አገላለጽና አነጋገር፣ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት ያህል ለሰው ልጅ ሲነገር ቆየ፤ ከዚህ በኋላ ጊዜው ሲደርስ፣ እንደተስፋው ቃል ሲጠበቅ የቆየው፣ የእባብ ዲያብሎስን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘር ከሴት ተወለደ፤ ይህ ዘር እንደመጀመሪያው አዳም ተራ ሰው አልነበረምና በተለመደው የዲያብሎስ ተንኮል ተሳስቶ የሚወድቅ አልሆነም፤ ምክንያቱም ከሴት የተወለደው ዘር (ዳግማዊ አዳም) ሰው ብቻ ሳይሆን፣ ሰውም አምላክም ነውና፣ ድሉ የዲያብሎስ ሳይሆን የሰው እንደሚሆን ሁኔታው ራሱ በግልጽ አመላከተ፡፡ በሰውነቱ የሴቲቱ ዘር፣ የአብርሃም ዘር፣ የዳዊት ዘር እየተባለ፣ በአምላክነቱ ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር እየተባለ በትንቢተ ነቢያትና በአፈ መላእክት የተነገረለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ድል አድራጊነቱን ያረጋገጠው ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በጾመበት በረሀ ላይ ነበረ፡፡

 ዲያብሎስ በተለመደው ተንኮሉ በመብል፣ በፍቅረ ንዋይና፣ በትዕቢት አስጐምጅቶ ለመጣል ባደረገው ፍልሚያ፣ ዳግማዊው አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊ ኃይል ድባቅ እየመታ መሣሪያዎቹን ሁሉ ዶግ አመድ ስላደረገበት፣ ሽንፈትን ተከናንቦ እንደተመለሰ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤

ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱም በተመሳሳይ መንገድ የዲያብሎስ ተላላኪ የሆኑ ርኩሳን መናፍስትን ድል አድራጊ በሆነው ቃሉ፣ “ አንተ ርኩስ መንፈስ እልሃለሁ ከእርሱ ውጣ” ሲላቸው፣ እነርሱም በበኩላቸው “አንተ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ያለጊዜው ልታጠፋን መጣህን?” እያሉ ሲመልሱ እናያለን፤ በዚህ አባባላቸው ርኩሳን መናፍስቱ የመጥፊያ ጊዜያቸው መቃረቡን ከማወቃቸውም በላይ፣ እሱ የሚያሸንፋቸውና የሚያጠፋቸው እንጂ፣ የሚመክቱትና የሚችሉት አለመሆኑን በአንደበታቸው ሲያረጋግጡ እናያቸዋለን፤ ይህም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን ርኩሳን መናፍስቱን ካደሩባቸው የእርያ መንጋዎች ጋር፣ አንድ ላይ በጌርጌሴኖን ባህር አሰጥሞአቸዋል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከዚህ በላይ እንደተገነዘብነው የዲያብሎስ የውጊያ መሣሪዎች ሕግ፣ ኃጢአትና ሞት ናቸው፤ ዲያብሎስ በመጀመሪያ አትብላ የሚል ሕግ መነገሩን ሲያውቅ፣ ሰው ሕግን እንዲጥስ አደረገ፤ እግዚአብሔርም በበኩሉ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ ፈጻሚ ነውና፣ ሕግ መጣሱን አረጋግጦ በሰው ላይ ፈረደ፤ ኃጢአት ማለት አንድን ነገር ማጣት ማለት ነውና፣ ሰው ሕግን በመጣሱ ምክንያት ታላቁ አባትና ጌታ እግዚአብሔርን አጣ፤ ማለትም ከእግዚአብሔር ተለየ፣ ቀጥሎም በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተፈረደበት፤ ዲያብሎስ ሰውን ሲወጋና ሲጥል የሚኖር በዚህ ስልት ነው፤ ማለትም በመጀመሪያ ሰው ሕግን እንዲጥስ፣ ቀጥሎም በሕግ ጥሰት እንዲፈረድበት ያደርጋል ማለት ነው፤ ዲያብሎስ ይህንን ተንኮሉ የሚያከናውነው በሰው ጭንቅላት ገብቶ የሆነ ነገርን በማስጐምጀት፣ በማነሣሣትና በመገፋፋት እንደሆነ ሁላችንም መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ታድያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን ራስ ቀጠቀጠ ሲባል፣ የቀጠቀጠው አካሉን ሳይሆን፣ የሰውን ጭንቅላት እየመረዘ ሰውን የሚጥልባቸውና የጭንቅላቱ ውጤት የሆኑት መሣሪያዎቹን ነው፤ እነሱም ሕግ ጥሰት፣ ግብረ ኃጢአትና ፍዳ ሞት  ሲሆኑ፣ እነዚህ የሚያመጡትን ከባድ ቅጣት በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት አስወገደ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራልን እንዲህ ይላል “ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?  የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው ይላል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ያለበት ምክንያት ሕግ ካልተጠበቀ፣ ለኃጢአት ኃይል እንደሚሆን፣ ኃጢአትም ሰውን ወግቶ ለሞት የሚዳርግ ጦር እንደሚሆን ለማስረዳት ነው፤ ይሁንና እነዚህ ሁሉ በጌታችን መስቀል ከአበጋዛቸው ከዲያብሎስ ጋር ድል መሆናቸውን ሲያበስር፣ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ብሎ ሲጠይቅ እናያለን፤ ምክንያቱም ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ፣ ሕግ የሚጠይቀውን የቅጣት ዋጋ ሁሉ፣ እሱ በፈጸመው የቤዛነት መሥዋዕት ሙሉ  በሙሉ የተነሣ መሆኑን ሲያስገነዝብ፣ “ሁሉም ተፈጸመ” ብሎ ራሱ ነግሮናልና ነው፡፡

በዘመነ ስብከቱም “ኃጢአትህ ተሠርዮልሃል፤ ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል “ እያለ ከማስተማሩም ሌላ፣ በመስቀል ላይ ሆኖ የኃጢአተኛው ወንበዴ ኃጢአትን በመሠረዝ፣ “ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ “ ብሎ በምሕረት ተቀብሎታል፤ በዚህም በእሱ መሰቀል የኃጢአት ዕዳና ቅጣት ተሠርዞ፣ ከእሱ ጋር በገነት መኖር እንደተጀመረ አብስሮናል፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ዐራት ሙታንን፣  በስቅለቱ ዕለት አምስት መቶ ሙታንን ከመቃብር በማስነሣት፣ የሞት ድል መሆንን በተግባር ከማሳየቱም ሌላ፣ “ አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት የነፍሳችን መንገድ ወደ እግዚአብሔር እንጂ፣ እንደድሮው ወደ ዲያብሎስ አለመሆኑን አሳይቶናል፤ ምክንያቱም ሞተ ነፍስ ማለት ከእግዚአብሔር መለየት፣ ድኅነተ ነፍስ ማለት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ማለት ነውና፡፡

ታድያ ይህ ሁሉ ሲሆን አሸናፊው ማን ነው? ተሸናፊውስ ማን ነው? የሚለውን በሚገባ ማወቁ ከእኛ አይጠበቅምን? ከተፈጸመው ድርጊት አኳያስ የመጨረሻው አሸናፊ የሴቲቱ ዘር የተባለውና የእባቡን ራስ የቀጠቀጠው ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? የመጨረሻው ተሸናፊስ ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ፣ እርሱም የቀደመው እባብ አይደለምን? ይህንን ድል ያቀዳጀንስ ያለመለያየትና ያለመቀላቀል፣ ያለመለዋወጥና ያለመጠፋፋት፣ ያለቡዓዴና ያለ ድማሬ፣ በአንድ አካልና በአንድ ባሕርይ ተዋሕዶ፣ የሰው ልጅ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ የሆነው አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? እንኪያስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ቤዛነት ይህንን ድል ላጐናጸፈን ለእግዚአብሔር ከፍ ያለ ምስጋና፣ ክብርና አምልኮ ልናቀርብለት ይገባል፡፡

ይህ በአምላካዊ ጥበብ የተከናወነው ድል፣ በሰው ልጅ ታሪክ ታላቁና ዋነኛው፣ ተወዳዳሪም የማይገኝለት፣ ከድል ሁሉ የበለጠ ድል ስለሆነ፣ በሃይማኖት መሣሪያነት የድሉ ባለቤትና ተጠቃሚዎች መሆን ከኛ ይጠበቃል፡፡

ዲያብሎስ በተንኮሉ የሸረበው ሤራ፣ በጌታችን የቤዛነት ኃይል ተበጣጥሶ፣ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የመኖር ጸጋው እንደገና እጅ አድርጎአል፤ የእግዚአብሔር ዓላማም በዲያብሎስ ተንኮል ሳይደናቀፍ፣ ሰው እንደገና ታድሶ በተቀመጠለት እግዚአብሔርን የመምሰል አቅጣጫ ቀጥሎአል፤ እግዚአብሔር ለሰው ያለው ብቸኛ ዓላማ ይህ ነው፤ ይህ ዓላማ በጌታችን ዳግም ምጽአት ለሁሉም ምእመናን በይፋ እውን ይሆናል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

የጌታችን በዓለ ስቅለትና በዓለ ትንሣኤ የሚያስተምረን ዓቢይ ትምህርት፣ በመንፈሳዊ ኃይል ማለትም በመንፈሳዊ ሕግ ሁሉንም ድል ማድረግ እንደሚቻል ነው፤ የሰው መደበኛ ጠላት ሕግን መጣስ ነው፤ ሕግ ከተጣሰ ኃጢአት ይመጣል፤ ኃጢአት ከመጣ ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየት ይመጣል፤ ትልቁና አደገኛው ሞት ይህ ነው፤ ትልቁ ሽንፈትም ይህ ነው፤ ታድያ እኛ የምንሸነፈው መቼ ነው? ያልን እንደሆነ መንፈሳዊ ሞራላችንና ኅሊናችን በክፉ መንፈስ ተሸንፎ ሕግን ስንጥስ ነው፤ ሰው ሕግን ካልጣሰ ኃጢአተኛ አይሆንም፤ ኃጢአተኛ ካልሆነም ከእግዚአብሔር አይለይም፤ ከእግዚአብሔር ካልተለየ ደግሞ በሥጋ ቢሞትም በነፍስ አይቀጣም፤ በዚህ ኩነት ስንገኝ ማለትም ሕግን ካልጣስን አሸናፊዎች መሆናችን እርግጠኞች እንሁን፡፡

በአሁኑ ጊዜ ዓለማችን በአጠቃላይ፣ እንደዚሁም ሀገራችን፣ በልዩ ልዩ ፈተና ሲደነባበሩ የሚታዩት፣ ከመንፈሳዊው ሕግ አፈንግጠው በሥጋዊ ፍልስፍና ብቻ ለመጓዝ በሚያደርጉት ከንቱ ሙከራ እንደሆነ፣ ከቶ ልንስተው አይገባም፤ እንደዚህ ዓይነቱ ርእዮት ለጊዜው ይመስል እንደሆነ እንጂ፣ በተጨባጭ እንደታየው የሚያዛልቅ ሆኖ አይገኝም፤ ለወደፊቱም ቢሆን ከማተረማመስ በቀር ሊሆን አይችልም፤ ቅዱስ መጽሐፍም፣ ተጨባጩ የዓለም ታሪክም ይህንን አያሳዩም፣ የሚያዋጣው ብቸኛው ርእዮት ፈሪሀ እግዚአብሔርን ማእከል ያደረገ ጥበብ ነው፣ ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ፣ ከዚህ ውጭ የሆነው አማራጭ እንደማያዋጣ እናስተውል ፡፡

ስለሆነም ከበዓለ ስቅለትና ከበዓለ ትንሣኤ ትልቅ ትምህርት ወስደን፣ ሰብአዊና መንፈሳዊ ሞራላችንን በሕግ፣ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በሰላምና በእምነት እየገነባን፣ በአእምሮ እየታደስን፣ ትንሣኤ አእምሮን፣ ትንሣኤ ኅሊናን፣ ትንሣኤ ልቡናን ለመነሣት መፍጠን አለብን፤ ይህ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እውነተኛና ዘላቂ ድል ነውና፡፡ ቀድሞም ሆነ ዛሬ የሁሉም መሣሪያ ጭንቅላት ነው፤ ጭንቅላታችን ሁሉንም ነገር በመልካም አስተሳሰብ ለማሸነፍ ቊርጠኝነት ካጠረው፣ ምንጊዜም ተሸናፊ መሆናችን አይቀርም፤ በአንጻሩ ደግሞ ጭንቅላታችን ሁሉን ነገር በቅንነትና በበጎ ሐሳብ ብቻ ለማሸነፍ ከተነሣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ የኋላ ኋላ አሸናፊነታችን የማይቀር ነው፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር በፈሪሀ እግዚአብሔር ሲታጀብ ነው፡፡ ዛሬ የሀገራችን ወቅታዊና አንገብጋቢ ነገሮች ሆነው የሚታዩት፣ የሰላም፣ የአንድነትና ከድህነት የመላቀቅ ጥያቄዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ልንመልሳቸው የምንችለው፣ በጭንቅላታችን ውስጥ መሽገው የተቀመጡትን፣ ጭፍን ጥላቻን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ለኔ ብቻ ይድላኝ ባይነትን፣ በጥርጥር ዓይን መተያየትን፣ አለመተማመንን፣ መጨካከንን መለያየትን አንዱ ለሌላው ሥጋት መሆንን፣ ሙሉ በሙሉ ከጭንቅላታችን ማስወጣት ስንችል ብቻ ነው፡፡

 ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ፣ ሽንፈትን ከሚያከናንቡን በቀር፣ ምንም ዓይነት ዕርባና ሊሰጡን አይችሉምና ነው፣ ነገር ግን ንጹሑን ጭንቅላታችን ተጠቅመን፣ በፍቅር፣ በወንድማማችነት፣ በኅብረት፣ በስምምነት፣ በአንድነት፣ በመከባበር፣ በመተማመን፣ በይቅር ባይነት፣ በመደጋገፍና በመተዛዘን መንፈስ ሁላችንም አጥብቀን ከሠራን፣ በሁሉም ዘርፍ በእርግጠኝነት አሸናፊዎች እንሆናለን፡፡

በ መ ጨ ረ ሻ ም

ለመላው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በሙሉ የምናስተላልፈው መልእክት፣ በየዓመቱ የምናከብረው በዓለ ትንሣኤ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ለማክበር ብቻ ሳይሆን፣ የኛንም ትንሣኤ በተግባር ለማረጋገጥና የኅሊና ዝግጅት ለማድረግም ጭምር መሆኑን አውቀን፣ በድህነትና በሰላም እጦት፣ እየተፈተነች የምትገኝ ሀገራችን ኢትዮጵያን፣ ለመታደግ በትንሣኤ አእምሮ፣ በትንሣኤ ኅሊና እና በትንሣኤ ልቡና ታድሰን፣ ፍጹም በሆነ የይቅርታ መንፈስ፣ ለሀገር አንድነት፣ ለዜጎች ክብርና ደኅንነት፣ ለዘላቂ ልማትና ዕድገት፣ ለፍጹም ወንድማዊ ፍቅርና ስምምነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ፣ በጥንቃቄና በማስተዋል፣ ባለመሰልቸት አጥብቀን እንድንሠራ፤ ከዚህ በተጨማሪ ለክርስቲያኖች ሁሉ በጥብቅ ልናሳስብ የምንፈልገው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በዐለ ትንሣኤ ልናደርገው የሚገባን መንፈሳዊና ሰብአዊ ግዴታችንን እንዳንዘነጋ ነው፤ ይኸውም የተራቡና የተጠሙ ወገኖቻችንን ካለን በማካፈል አብረውን እንዲገድፉና በልተው ጠጥተው ተደስተው እንዲውሉ እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዐለ ትንሣኤ ያድርግልን

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ ይቀድስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ