ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወአሐዱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
- በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
- ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
- የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
- በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
- እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
ምድራችንን በልምላሜ፣ በአበባ፣ በእሸት በአጠቃላይ በፍጹም በረከት እያደሰ ዘመንን በዘመን እየተካ ጸጋውን ያበዛልን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ ወደ ሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ፤የልቡናችሁን ዕውቀት አድሱ፤እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት በእውነት በቅንነትና በንጽሕና ልበሱት፤ ሐሰትን ተውአት፣ ሁላችሁም ከወንድሞቻችሁ ጋር እውነትን ተናገሩ፤ እኛ አንድ አካል ነንና” (ኤፌ4፤23)፡፡
እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ከለገሳቸው ስጦታዎች አንዱና ዋነኛው የመታደስ ጸጋ ነው፤ እግዚአብሔር፣ እያረጀ እንደገናም እየታደሰ የሚኖር የግዙፋን ፍጥረታት ዓለምና እርጅና የማይነካው የመንፈሳውያን ፍጥረታት ዓለም በድምሩ ሁለት ዓይነት ዓለም እንደፈጠረ ይታወቃል፡፡
የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከግዙፋኑ ወገን ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ በግዙፉ ዓለም ከቆየ በኋላ ታድሶ ወደ ረቂቁ መንፈሳዊ ዓለም በመሻገር ያለ እርጅና ለዘላለም ጸንቶ ለሚኖር ሕይወት የታደለ ፍጡር እንደነበረ በመጽሐፍም በተግባርም የተረጋገጠ ነው፤ ይህ ዓይነቱ የሰው ዕድል በኃጢአት ምክንያት ለጊዜው ቢደናቀፍም የተዘጋጀልንን ጸጋ በውል እንድናውቅ እነ ሄኖክና እነ ኤልያስ የመሳሰሉትን ሞትና ዕርጅና ወደ ሌለበት ዓለም በመውሰድ በተግባር አሳይቶናል፡፡
የሰው ልጅ የመታደስ ጸጋ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንደገና እንደሚቀጥል በነቢያቱ በኩል ተስፋው ሲገለፅ ከቆየ በኋላ፣በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ዳግመኛ ዕድሉ ተሰጥቶን እነሆ ሙሉ በሙሉ ታድሰን ወደማያረጀው መንፈሳዊ ዓለም ለመሸጋገር የጌታ ቀንን እየጠበቅን እንገኛለን፡፡
የሰው ልጅ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ታሪክ ሁለት ታላላቅ ነገሮች አጋጥመውታል፤ እነሱም ብልየትና ሕዳሴ ወይም ማርጀትና መታደስ ናቸው፤ እነዚህ ሁለቱ በዘመን ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ዘመነ ብሉይ፣ ዘመነ ሐዲስ ተብለው ይታወቃሉ፤ ዘመነ ብሉይ የሚባለው ከአዳም ውድቀት ጀምሮ እስከ ልደተ ክርስቶስ ያለው ሲሆን፣ ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ያለው ደግሞ ዘመነ ሐዲስ ይባላል፤ ይህ ዘመን መጨረሻ የሌለው ሐዲስ ሕይወት የተገኘበት ስለሆነ እስከ የለውም፤ከዚህ አንጻር ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ባለው ዘመን የምንኖር ሁላችን በመታደስ ዘመን ውስጥ የምንገኝ ስለሆን ጽዉዓን ኅሩያን ማለትም የተጠሩ የተመረጡ እንባላለን፤ ዘመኑም ዓመተ ምሕረት ይባላል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
በፀሐይ አቈጣጠር መስከረም አንድ ቀን በየዓመቱ የምናከብረው የርእሰ ዐውደ ዓመት ወይም የዓመት ዙር መነሻ ራስ በዓል በውስጡ የተፈጥሮ፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት ምሥጢርን አምቆ የያዘ ነው፡፡
ከጥንተ ተፈጥሮ አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ የቀደሙ አበው እነ አዳም፣ እነ ኖኅ ከዚያም ጥንታውያን የምሥራቅ አገሮች በተለይም ከለዳውያን፣ ግብጻውያንና አይሁዳውያን ጭምር ይከተሉት የነበረ ነው፤የኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት፣ በጨረቃ አቈጣጠር ከመሆኑ በቀር ዛሬ ድረስ በእሥራኤላውያን ተጠብቆ የሚኖር ከሁሉም የዘመን መለወጫ ይልቅ የዕድሜ ባለ ጸጋ የሆነ ርእሰ ዐውደ ዓመት መሆኑ ለጥንታዊነቱ በቂ ማስረጃ ነው ፤ ከዚህም ጋር ፀሐይና ጨረቃ በየዐሥራ ዘጠኙ ዓመት ዑደታቸውን ጳጕሜን አምስት ቀን እያጠናቀቁ መስከረም አንድ ቀን ሁለቱም ማለትም ፀሐይና ጨረቃ በአንድ ቀን ከአንድ የጊዜ መነሻ ነጥብ አንድ ላይ መነሣታቸው ይህ ቀን እነሱ የተፈጠሩበት ቀን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነው፤ የቤተ ክርስቲያናችን የቊጥር መጽሐፍም ዐሥራ ዘጠነኛው ዐውደ አበቅቴ፣ ፀሐይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩበት ኆኅት ተራክቦ ያደርጉበታል በማለት ይህንን መሠረተ ሐሳብ ያጠናክራል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ መስከረም አንድ ቀን ላይ እንዲሆን መደረጉ ከቀደምት አበው ትውፊትና የመስከረም አንድ ቀን ዐውደ አበቅቴ የፀሐይና የጨረቃ መነሻና መድረሻ ሆኖ ከመገኘት አንጻር የዘመን መነሻ ቊጥር የተጀመረው መስከረም አንድ ቀን ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ስለተያዘበት እንደሆነ በዚህ እናስተውላለን፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የዘመነ ብሉይ ማብቃት የዘመነ ሐዲስ መግባት ያበሰረ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በመሆኑ፣ ከመስከረም አንድ ቀን በፊት የተጠናቀቀው አሮጌው ዘመን እንደ ዘመነ ብሉይ፣ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ የምንቀበለው አዲሱ ዓመት እንደ ዘመነ ሐዲስ በአንድ ወገን፣የአሮጌውን ዘመንና የሐዲሱን ዘመን መለያ ርእሰ ዐውደ ዓመትና የዘመነ ብሉይና የዘመነ ሐዲስ መለያ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሌላ ወገን በምሥጢራዊ ንጽጽር ተመሥጥሮ ርእሰ ዐውደ ዓመትና ቅዱስ ዮሐንስ አንድ ላይ እንዲከበሩ ተደርጎአል፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ይህንን አስመልክቶ ሲናገር “ውስተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተጽሕፈ ተዝካርከ፤ መታሰቢያህ በርእሰ ዐውደ ዓመት ላይ እንዲከበር ተጻፈ” ብሎአል፡፡
ዋናው መልእክት ርእሰ ዐውደ ዓመት የአሮጌውን ዘመን ማብቃት የሐዲሱን ዘመን መግባት በማብሰር አዋጅ ነጋሪ እንደሆነ ሁሉ፣ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም የብሉይ ኪዳንን ማብቃት የሐዲስ ኪዳንን መግባት በማብሰር አዋጅ ነጋሪ እንደሆነ በማነጻጸር በንሥሐ መታደስን ይሰበክበታል ፡፡
እንዲሁም አሮጌው ዘመን ከኅልፈተ ዓለም፣ አዲሱ ዘመን ከአዲሱ የመንግሥተ ሰማያት ዘመን፣ ርእሰ ዐውደ ዓመት ከዕለተ ምጽአት በንጽጽር ተመሥጥሮበት የጌታ ምጽአትና የመንግሥተ ሰማያት አዲስ ዘመን ይታሰብበታል፡፡
ከዚህም ሌላ የሀገራችን ሥነ ተፈጥሮ እንደሚያሳየን ከመስከረም አንድ ቀን በፊት ያለው ወርኃ ክረምት ነጐድጓድ፣ መብረቅ፣ የነፋስና የዝናም ውሽንፍር፣ የደፈረሰ ጐርፍ፣ የጉምና የደመና ጽልመት የሚነግሥበት፣ እህሉ አልቆ ሰው ለምግብ እጥረት የሚጋለጥበት ወቅት ነው፡፡ ከመስከረም አንድ ቀን በኋላ ግን ሁሉም ነገር የሚታደስበትና የሚለወጥበት ነው፤ ማለትም የምግብ እጥረቱ በአዲስ እሸት የሚተካበት፣ ጨለማው ደመናው ጉሙ መብረቁ ነጐድጓዱ ቦታውን የሚለቅበት፣ በምትኩ ደግሞ የፀሐይ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃናት በጠራ ሰማይ ላይ ፍንትው ብለው ደማቅ ብርሃናቸውን የሚያሳዩበት፣ በየዋሻውና በየቋጥኙ ተወሽቀው የነበሩ አእዋፍና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ እንደልባቸው ወዲያ ወዲህ እየበረሩ በደስታ የሚዘምሩበት፣ ድፍርሱ የጐርፍ ውሀ ወለል ብሎ የሚጠራበት በአጠቃላይ የሥነ ፍጥረት ውበት የሚታደስበት ወቅት፣ ከመስከረም አንድ ቀን በኋላ ነው፤ ከዚህ አኳያ በመንፈስ ቅዱስ የተሟሟቁ ፣ በዕውቀት የተራቀቁ ቀደምት ኢትዮጵያውያን አበው የወርኃ ክረምቱን አስጨናቂ ሥነ ተፈጥሮ የዘመነ ብሉይ መከራና ፍዳ ተምሳሌት አድርገው አመሥጥረውታል፣ በሌላ በኩል ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ያለውን የሥነ ፍጥረት መታደስ የዘመነ ሐዲስ ተምሳሌት አድርገው በማመሥጠርና በመቀመር በሥነ ፍጥረት ውበት ላይ የመንፈስ ውበትን አላብሰውታል፤ ይህ እጅግ ውብና ድንቅ የሆነ መንፈሳዊና ተፈጥሮአዊ ሀብተ አበው በሚገባ ጠብቆ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ ከነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት
ኢትዮጵያዊው የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት በዋናነት የሚያስተምረን ትምህርት መታደስን፣ መለወጥን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣትን፣ ከድህነት ወደ ልማት መሸጋገርን፣ ከማጣት ወደ ብልፅግና መራመድን ነው፣ አዲሱ ዓመት ስንፍናን በትጋት፣አለማወቅን በዕውቀት የምንለውጥበትን፣ ካለፈው ዓመት ይልቅ እጥፍ ድርብ የሆነ ሥራ በመሥራት ምርታችንን በከፍተኛ ሁኔታ የምናሳድግበትን አዲስ መንፈስ ሰንቀን ለተሻለ ልማትና ዕድገት የምንነሣበት መሆን ይኖርበታል ፡፡
ታድያ ይህን ሁሉ እውን ማድረግ የምንችለው ከሁሉ በላይ የሆነውን ሀብተ ፍቅር በእያንዳንዳችን የልቡና ኪስ ሲሞላ ነው፡፡ ፍቅር የሁሉም መሠረት ነው፤ ፍቅር ሰላምን ይወልዳል፣ ሰላም አንድነትን ይወልዳል፣ አንድነት ጉልበትን፣ ልማትን፣ ዕድገትን፣ መታፈርን፣ መፈራትን፣ መከበርን፣ መደመጥን ይወልዳል፤ እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ የቀደመውን ደማቅ ገናንነትዋን መልሶ ለማረጋገጥ ሲሉ ውድ ልጆቿ ለለውጥ ሲባክኑ እነሆ ከስድሳ ዓመታት በላይ ተቆጥሮአል፡፡ ነገር ግን ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ሳይደረስ ነገሮች እየተወሳሰቡ ከለውጡ ይልቅ ጥፋት እየቀደመ አሁን ላለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ዋና ምክንያት ሆኖ የሚታየው በሀገሪቱ ውስጥ ለዘመናት በበለፀገ ቅዱስ ባህል የተገነባውን የሕዝቡን መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ርእዮት ተከትሎ እርሱን ማእከል ባደረገ የዕድገትና የለውጥ አስተዳደር ማስፈን ሲቻል በእሱ ፈንታ የውጭ ርእዮትን እንዳለ ተቀብሎ በሕዝቡ ጫንቃ ላይ በግድ ለመጫን የሚደረገው የተሳሳተ አካሄድ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ለውጡ ሲጀመር ይቅር ይቅር በመባባል ወደዋናው የለውጥ ተግባር በመሸጋገር ፈንታ የበቀል እርምጃ ወደ መውሰድ ይዞራል፤ ከዚህም የተነሣ መግባባት ስላልተቻለ የሀገር አንድነትና የዜጎች ደኅንነት ሥጋት ላይ እየወደቀ የሀገሪቱና የዜጎችዋ ዕጣ ፈንታ ዋስትና የለሽ እየሆነ መቀጠል ግድ ሆኖበታል፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ከሦስት ሺሕ ዘመናት በላይ የእግዚአብሔር የመመለኪያ ቤተ መቅደስ የታቦቱና የመስቀሉ ታማኝ መንበር በሆነች ኢትዮጵያ ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩና እግዚአብሔርን እየፈሩ ሕዝቡን መምራት የሚያስችል እምነትና ድፍረት መታጣቱ ነገሩ ሁሉ የኋልዮሽ እንዲመለስና ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
አሁንም ከሁሉ በላይ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጀው እግዚአብሔርንና ሕዝቡን ማእከል አድርጎ መሥራት ነው፤ እግዚአብሔርን ስናደምጥ ይቅርታ እንጂ መለያየት፣ የለም መጠራጠርና አለመተማመን ቦታ አይኖራቸውም ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንደ ካሁን ቀደሞቹ ፈተና እንዳይገጥመው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለፍቅርና ለይቅርታ ሰፊውን ቦታ ይስጥ፣ የኃይለ ቃላት ውርወራን ያቁም፤ ኃይለ ቃልን የምንጠቀም ከሆነ መቃቃርን ያስከትላል፣ መቃቃር ጥላቻን ያሳድጋል፣ ጥላቻ ግጭትን ይወልዳል፤ ስለዚህ የሚወረወሩ ኀይለ ቃላት ወገንን አስከፍተው ዋጋ እንዳያስከፍሉን ከአዲሱ ዘመን መለወጫ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገድለን እንቅበራቸው፤ የቀደመውን ግድፈት ሁሉ ለታሪክ ትተን ለቀጣይዋ ኢትዮጵያ አንድነትና ለዜጎችዋ ደኅነንት መልካም የሆነውን ማሰብ የዘወትር ተግባራችን ይሁን፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ እየሰጣችሁ በሰላምና በሰላም ብቻ መንገድ እየተጓዛችሁ ለሀገር የሚበጀውን በማድረግ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ፣ የጥበብ ባለሙያዎች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን ሁላችሁም የቃላት ውርወራን አቁማችሁ ፍቅርንና ይቅርታን፣ የዜጎች ደኅንነትንና የሀገር አንድነትን እንድትሰብኩ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በ መ ጨ ረ ሻ ም
ባለፈው ዓመት በሀገራችን የታዩ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ የሆኑ ግድፈቶች እንደአሮጌው ዘመን አሳልፈንና ፋይላቸውን ዘግተን በአዲስ ፍቅር፣ በይቅርታ፣ በአንድነት የሕዝቡን መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ነባር ዕሤትን በመጠበቅ እግዚአብሔርን በመፍራትና እሱን የበላይ ዳኛ አድርጎ በመቀበል የሀገር አንድነትንና የዜጎችን ደኅንነት በማስጠበቅ አዲሱን ዘመን በፍጹም መታደስ እንድንቀበለው አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
አዲሱ ዘመን የተባረከና የተቀደሰ የሰላም፣ የፍቅናር የይቅርታ ዘመን ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔርአሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ