ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትዐብይ ጾምን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

346

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ  ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን አስመልክቶ የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. መልእክት አስተላለፉ፡፡
ቅዱስነታቸው ያስተላለፉትን ሙሉ መልእክት ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡-
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በአተ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡
በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በመላ ዓለም የምትገኙ፣
በሃይማኖት ጸንታችሁ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንዲፈጽምላችሁ በናፍቆት የምትጠባበቁ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ምእመናንና ምእመናት፣
ኃጢአትን በምግባረ ጽድቅ ለምንደመስስበት፣ ዲያብሎስን በእግዚአብሔር ቃል ድል ለምናደርግበት ለታላቁ ጾማችን ለጾመ ኢየሱስ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ፡፡
‹‹እስመ አኮ ክመ በኅብስት ባህቲቱ ዘየሐዩ ሰብእ አላ በኵሉ ቃል ዘይወጽእ እምአፉሁ ለእግዚአብሔር፤ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› (ማቴ 4÷4)
    ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ወደ ምድረ በዳ ሄዶ ጾምን መጾም ጀመረ ፡፡
    ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት ሲጾም ከዓራዊት በቀር ከእርሱ ጋር ማንም አልነበረም፤ መዋዕለ ጾሙን ከፈጸመ በኋላ ዲያብሎስ አዳምን ባሳተበት መብል እርሱንም ለማሳሳት ከጀለ፤ ሆኖም ጌታችን ‹‹ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› በማለት የማሳሳቻ ግንቡን ናደበት፤
ቀጥሎም ዲያብሎስ ‹‹መላእክቱን ስላንተ ያዝልሃል፣ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል›› ብሎ መጽሐፉን በትዕቢት መንፈስ በመጥቀስ ጌታችን ከመቅደሱ አናት ራሱን እንዲወረውር በስሑት ጥቅሱ ወተወተ፤ ይሁንና አሁንም ጌታችን ‹‹አምላክህን እግዚአብሔርን አትፈታተነው›› ተብሎ ተጽፎአል በማለት በድጋሚ የጥፋት መረቡን በጠሰበት፡፡ (መዝ.90›÷11፤ ዘዳ. 6÷16)
    ዲያብሎስ ለሦስተኛ ጊዜ  የዓለምን ክብርና ብልጽግና በማሳየት ጌታችንን ለእኔ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ ብሎ በፍቅረ ንዋይ አማካኝነት በአምልኮ ባዕድ ሊያጠምደው ሞከረ፤ ያን ጊዜ ጌታችን ሂድ፣ አንተ ሰይጣን ‹‹ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ›› (ዘዳ.6÷13) ተብሎ ተጽፎአል ብሎ ዲያብሎስን ተስፋ ቆርጦና ተሸንፎ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት ፡-
ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር ሲሹ ከእህልና ከውሀ ተከልክለው፣ በጾም ተወስነው፣ ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን ሲለምኑ ተቀባይነትን ያገኙ እንደነበረ በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ ተጽፎአል፤ በዚህም ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራ፣ እንደዚሁም ሙሴና ኤልያስ፣ አስቴርና ወንድሟ መርዶክዮስ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው ፤ ከሀገር አንጻር ደግሞ የነነዌ ከተማን ብንመለከት ስለጾም ጠቃሚነት በቂ ትምህርት እናገኛለን፣ (አስ. 4፡1-4፣ ዮና. 3፡1-10)
አበው ነቢያት በጾምና በጸሎት ሆነው ያቀረቡትን ተማኅፅኖና ልመና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ የሚሹትን እንዳገኙ ቅዱሳት መጻሕፍት መስክረዋል ፡፡
    ጌታችን፣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የተጓደለውን ለማሟላት፣ የረቀቀውን ለማጕላትና የተዛባውን ለማስተካከል የመጣ እንደመሆኑ መጠን ‹‹ኦሪትንና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም›› በማለት አስተምሮአል ፤ (ማቴ 5÷17)
    በመሆኑም ሙሴና ኤልያስ እንዳደረጉት እርሱም ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት በመጾም ሰይጣንን ድል አድርጎአል፤ ከድርጊቱ ሂደት እንደምንገነዘበው ሰይጣን ሰውን ለመጣል የሚጠቀምባቸው ዋና ዋና መሣሪያዎች መብል፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ መሆናቸውን በዚህ እናስተውላለን ፤ ዲያብሎስ እናታችን ሔዋንን በዛፉ ፍሬ እንድትጎመጅ፤ እንደእግዚአብሔር ትሆናላችሁ በሚለው ቅስቀሳ ሁሉን በእጇ እንድትጨብጥ በሚያስመስል የሐሰት ምክር እንድትወድቅ አድርጎአል፤ (ዘፍ. 3÷4-8)
    ዲያብሎስ፣ ጌታችንን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጾ በአዳማዊ ቁመና ሲመለከተው በቀዳማዊ አዳም የተጠቀመውን ስልት ተጠቅሞ ዳግማዊ አዳምን ለመጣል ብዙ ተጠብቦአል፤ ይሁን እንጂ ‹‹ተልባ መስሎሽ ሰናፍጭ ትቀምሽ›› እንደሚባለው በቀዳማዊ አዳም ያስለመደው ዘዴ ዳግማዊ አዳም በተባለ በጌታችን ላይ ሊሠራለት አልቻለም ፡፡
    ጌታችን፣ ዲያብሎስን ድል የነሣው በሦስት ነገሮች እንደሆነ እናያለን ይኸውም፡-
–    በጾም፣
–    በጸሎትና
–    በእግዚአብሔር ቃል ነው (ሉቃ. 4፡1-13)
ጌታችን በዲያብሎስ በኩል ይቀርቡ የነበሩ ፈተናዎች በሙሉ ያከሸፋቸው የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ነው፤ ዲያብሎስም በዚያው ልዋጋ ብሎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስን ተጠቅሞአል ይሁንና ጥቅሶቹ በተቀመጠላቸው እውነተኛ ትርጉምና መንፈሳዊ ይዘት ሳይሆን ለራሱ ክፉ ዓላማ በሚያመች አኳኋን ለትዕቢትና ለፍቅረ ንዋይ ስለተጠቀመባቸው ሚዛን ሊደፉለት አልቻሉምና በመጨረሻ ሽንፈቱን ሊከናነብ ግድ ሆኖበታል ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፡፡
ጾም ዲያብሎስንና አሳሳች መሣሪያዎቹን ሰባብረን የምንጥልበት መንፈሳዊና ኃያል መሣሪያችን ነው፤
–    በጾምና በጸሎት አጋንንት ይሸነፋሉ፣
–    በጾምና በጸሎት ኃጢአት ይደመሰሳል፣
–    በጾምና በጸሎት መልካም የሆነ የሥራ ዕቅድ ይሠምራል፤
–    በጾምና በጸሎት ነፍስ ከቁስለ ኃጢአት ትፈወሳለች፤
–    በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ይቻላል፤ በአጠቃላይ ጾምና ጸሎት የሥጋ ፍላጎትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ነፍስ ኃያልና አሸናፊ ሆና የበላይነትን እንድትቀዳጅ ያደርጋሉ፡፡
    እንግዲህ ጾምን እንድንጾም የምንገደድባቸው ዓበይት ምክንያቶች እነዚህ ሲሆኑ ብዙ ተከታይ ሠራዊት እንዳላቸውም መዘንጋት የለብንም በጾም ወቅት፡-
–    እጆቻችን ለጸሎት፣ ድሆችን ለመርዳትና ለልማታዊ ሥራ የሚዘረጉ፤
–    አንደበታችን ሃይማኖትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን የሚሰብክ፣
–    ጆሮአችን ቃለ እግዚአብሔርን፣ መልካሙንና ሐቁን ነገር ብቻ የሚሰማ፣
–    ዓይናችንም ወደጽድቅ ሥራ ብቻ አነጣጥሮ የሚመለከት
–    እግሮቻችንም ወደ ቤተ እግዚአብሔርና ወደልማታዊ ተግባር የሚገሠግሡ መሆን አለባቸው፣ በዚህ መንፈስና ግንዛቤ ጾሙን ከጾምን ዲያብሎስን ማሸነፋችን፣ እግዚአብሔርንም መምሰላችን የሚያጠራጥር አይሆንም ፡፡

በመጨረሻም
    የጾም ወራት ከምንም ጊዜ የበለጠ ሥራ የሚሠራበት እንጂ እጅና እግር አጣጥፈው የሚውሉበት ባለመሆኑ መንፈሳዊውንና ልማታዊውን ሥራችንን አቀናጅተን በመሥራት ሀገራችንን በአረንጓዴ ልማት ያጌጠች፣ ውብ፣ ለኑሮ ምቹና የተፈጥሮ ጸጋዋ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚደረገው የአፈርና የውሀ ጥበቃ ሥራ፣ በወርኃ ጾሙም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምድርን ውብና ለም አድርጎ በፈጠረ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወርኃ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

{flike}{plusone}