ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ወደ እናት አገራቸው ተመለሱ
አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትጋር ወደ ኢትዮጵያ በሰላም ገብተዋል ። ሲገቡም ደማቅ አቀባበል ተደረጎላቸዋል፡፡ ከ26 ዓመታት ያላነሰ ዕድሜ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ የጥል ግንብ(ክፍፍል) በእግዚአብሔር ቸርነት፤ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዶክተር ዐቢይ አህመድ ያላሰለሰ ጥረትና በሁለቱም ሲኖዶሳዊ ቅዱሳንና ብፁዓን አባቶች ቀና በሆነ አመለካከትና የዕርቀ ሰላም ፍላጎት መሠረት የጥሉ ግንብ ተደረማምሶ የዕርቀ ሰላሙ ድልድይ ተገንብቷል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም ወደቀደመ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል፡፡
ቅዱስነታቸው እና ተከታዮቻቸው ብፁዓን አባቶች በጠቅላይ ሚኒስተሩ VIP አውሮፕላን ሐምሌ 25ቀን 2010ዓ/ም ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ 6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፣ብፁዓን አባቶች ፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ መምህር ይቅርባይ እንዳለ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች ፣የኢዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ ሓላፊዎች ፣የሰንበት ት/ቤቶች መዘምራን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ጀምረው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በቀጥታ ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያመሩ ሲሆኑ እዛውም በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችና ምዕመናን በደማቅ አቀባበል ተቀብሏቸዋል፡፡
በመቀጠልም በፕሮግራሙ መርሐ ግብር መሠረት የዕርቁን ሂደት ሲከታተል የነበረው የብፁዓን አባቶችና የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የኮሚቴ አባላት በመወከል ብፁዕ አቡነ አብርሃም ስለ ነበረው የዕርቁ ሂደት ሲያብራሩ ምንም አይነት አከራካሪ ጉዳይ አለመፈጠሩን ፣ሌላም ሦስተኛ ወገን አሸማጋይ አለመኖሩን ፣የሁለቱ ሲኖዶሶች ወኪሎች ዝግ ስብሰባ አድርገው የጋራ ውሳኔ ላይ የደረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፣በዚህም በርካታ የእምነታችን ተከታዮች መደሰታቸውን አብራርተዋል። በመጨረሻም የኢፊዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተዘጋጀው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ ተገኝተው ኦርቶዶክስ ሀገር ናት ፣ዛሬ የጥል ግንቡ ፈርሷል፣ድልድዩ ተገብቷል፣በማለት ታላቋን ቤተ ክርስቲያናችንን በዓለም አቀፉ መድረክ አወድሰዋል በማለት ሪፓርታቸውን አጠቃለዋል፡፡
ከዚያም በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወክለው ስለነበረው ዕርቀ ሰላሙ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፤ ዕርቀ ሰላሙ የእግዚአብሔር ምሥጢር አለበት ፣ለመምጣት ያቀድነው በሌላ ቀን ነበር ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እኛ ባላሰብነው ሐምሌ25ቀን2010ዓ/ም ለመምጣት ችለናል ካሉ በኋላ ፥ ዕለቱ የሰማዕቱ የመርቆሬዎስ ዕለት መሆኑ ከፓትርያርኩ ስም ጋር ይዛመዳል ፥ ይህም የእግዚአብሔር ምሥጢር ነው ፤ይኸውም ከእግዚአብሔር የተላኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አንድ አደረጉን ፥የእኛ ሓሳብ ብፁዕ ወቅዲስ አቡነ መርቆሬዎስ በሞተ ሥጋ ቢለዩንም ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ዝግጁ ነበርን ፥ይህ ማለት ደግሞ ቤተ ክርስቲያንዋ ለሁለት ተከፍላ ትኖራለች ማለት ነው፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተላኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ደርሰውላታል ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፣ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት መልእክት” ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልው አሀው ኅቡረ ” የወንድሞች አንድ መሆን ያማረ ነው በሚል የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ተነሥተው ከቅዱስነታቸው ጋር ሢመተ በዓላቸው አንድ ቀን እንደነበረ፣ በአንድ ፓትርያርክ በአቡነ ተክለሃይማኖት አንብሮተ እድ እንደተሾሙ ታሪካዊ ዳራቸውን በማውሳት ሰለተደረገው ዕርቅ ደስታቸው ገደብ እንደሌለው ገልጸዋል። በቀጣዩም ቤተክርስቲያንዋን በመመካከርና በመደጋገፍ አብረው በጋራ ለመምራት ዝግጁ መሆናቸውን በደስታ በመግለጽ ስለ ተደረገው ዕርቀ ሰላም እግዚብሔርን በማመስገን መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡