ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በአ/ሀ/ስ/የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሀገረ ስብከቱ የሥራ እንቅስቃሴን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ አመራር አደረጃጀትን እና ቀደም ሲል ከሥራና ከደመወዝ የተፈናቀሉ ሠራተኞችን ጉዳይ አስመልክተው ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም  ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምስቱ አርዮንታል አብያተ ክርስቲያናት አንዷና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ ከጌታችን፣ ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ  ትምህርት፣ ከሐዋርያት፣ ከሐዋርያን አበው፣ በየደረጃው ስለስቱ ምዕትም እንዲሁ በመጀመሪያ በ325 ከዚያ 381 እና በ431 ዓ.ም እነዚህን ዐቢይት ጉባኤያትን ተቀብላ፣ የሐዋርያት ትውፊትን ጠብቃ፣ ትውፊቷም በሌሎች ያልተጣሰ፣ ያልተደፈረ ሲሆን በዓለማዋ ፀንታ የኖረች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

ያ ሥርዓት ሳይፋለስ ተጠብቆ አሁን እስከ አለንበት ዘመን ደርሶ ቤተ ክርስቲያንዋ ሕዝቧቿን የምትመራበት፣ የምታስተምርበት፣ የምታስተዳደርበት የምዕመናን ወኪል ያሉበት ፣ ወጣቶች የሚወከሉበት፣ ካህናት የሚወከሉበት፣ ሁሉም በየዘርፉ በጾታው ሰብጥር ያሉበት የሰበካ ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ አውጥታ በዚያ እየተመራች ትገኛለች፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ

የሰበካ ጉባኤ ዓላማ

  1. ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ማድረግ፤
  2. የቤ ተክርስቲያንን አገልጋዮች በሐዋርያነት ተግባር ማደራጀት፣ ችሎታቸውንና እና ኑሮአቸውን ማሻሻል፣
  3. ምዕመናን በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልምሰው፣ በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው፣ በክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ፣
  4. የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ማጠናከር፣ እንዲሁም በገቢ ራሷን ማስቻል ናቸው፡፡

እነዚህ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሁልጊዜ የምትመራባቸው ዓላማዋ ናቸው፡፡

ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከመጣሁ ከአንድ ወር በላይ ሆኖኛል፡፡ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተሠሩ ዐበይት ሥራዎች አሉ፤ የገጠሙም ተግዳሮቶች አሉ፡፡

የተሠሩ ሥራዎችን በሚመለከት ሀገረ ስብከቱን በአዲስ አመራሮች መተካት ነው፤ ሙሉ ለሙሉ 14ቱም አመራሮች ተነሥተው በምትካቸው በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በጠባያቸውና በሥራ አፈጻጸማቸው ይመጥናሉ የተባሉ አገልጋዮችን በቦታው መተካት ነው፤ የመጀመሪያው ሥራ ይህ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ ደረጃ አንድ አንድ የአስተዳደር ጉድለቶች በመኖራቸው ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም  ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በቀረበው ሮሮ እና ጩኸት ምክንያት መልካም አስተዳደርን ለመስፈን፣ መጀመሪያ ጉዳዮቹ መጣራት ስላለባቸው ከሰብአዊ መብት ተወካይ፣ ከፌደራል ጉዳዮች ተወካይ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዕውቅ ሰዎች ባንድ ላይ ሆነው በሀገረ ስብከቱ ላይ ደረሰ የተባለውን የአስተዳደር በደል እንዲያዩ፤ እንዲመምሩ፣ አጥንተውም እንዲያቀርቡ ቅዱስነታቸው በቋሚ ሲኖዶስ አስወስነው፣ የማጣራቱ ሂደት በሚገባ ተከናውኖ፣ ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ፣ እንደገና ጸድቆ ሠራተኞቹ በሦስት መንገድ በደል የደረሰባቸው በመሆኑ፣

ከሥራ ሙሉ ለሙሉ የታገዱ፣ ከሥራ የተፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን የቅጥር ደብዳቤ ተሰጥቷቸው ነገር ግን ከሁለቱም ሳይኑ ባየር ላይ የቀሩ፣ ከጥቅማቸውም፣ ከደረጃቸውም፣ ዝቅ ተደርገው የተመደቡ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ ቋሚ ሲኖዶስ በጥናቱ መሠረት በወሰነው ቅድሚያ ከሥራ የተፈናቀሉትንና የወር ደመወዝ የሌላቸውን ወደ ሥራቸው መመለስ፣ አመራሩን ሙሉ በሙሉ ከመተካት ባሻገር የመጀመሪያው ሥራችን ከሥራ የተፈናቀሉትን፣ ደወመዝ የሌላቸውን ደመወዝ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡

እርሱም ከመቶ ዘጠና አምስቱ ፕርሰንት ተሳክቷል፡፡ ሠራተኞች በሥራቸው ተመድበዋል፤ በአስተዳዳሪነት ደረጃ ያሉትን ወደነበሩበት ለመመለስ ጊዜ ስለሚያስፈለግ ቀደም ሲል ነበሩበት ቦታ በሌሎች በመያዙና እነርሱን እንደገና ማፈናቀል ስህተትን መደገም ስለሚሆን ነገሮችን አመቻችተን በቅርቡ መፍትሔ እንሰጣለን፡፡ ለሌሎች ግን መፍትሔ ሰጥተናል፤ በተለይ ደመወዝ ለሌላቸው፤ ሌላው ደግሞ ለአንድ ዓመትም ይሁን ለሁለት ዓመታት ደመወዝ ሳይኖራቸው በሰዎች እየተረዱ የቆዩት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ውዝፍ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው ጥናቱ አልቋል፤ ሌላውም በየደረጃው መፍትሔ ያገኛል፤ የመጀመሪያው ደረጃ ደመወዝ የሌላቸው ቤተሰቦቻቸው በረሃብ እንዳይቀጡ፤ በአዲሱ ዓመትም መልካም ምኞትና ተስፋ እንዲኖራቸው የእነርሱን ችግር መፍታት ነው፤ ውዝፍ ደመወዛቸውንም እንዲያገኙ የታዘዘ ስለሆነ አፈጻጸሙን እየተከታተልን ነው፤

ቀጥሎ በአየር ላይ ያሉትን ደግሞ ለእሱም ቦታ መስጠት ነው፤ ሦስተኛውና የመጨረሻው ከደረጃቸው ዝቅ ብለው፣ ከጥቅማቸውም አንሰው ወደ ሌላ ቦታ የተቀየሩና ተቃውሞ ያቀረቡ፣ በዝውውሩ ተበድለናል ያሉ ሰዎችም አጣሪ ኮሚቴው ባቀረበውና በሰጠው አስተያየት መሠረት ለእነሱ መፍትሔ እንሰጣለን፤ የተበዳዩ ቁጥር እስከ 300 ይደርሳል ይህ በአጣሪው ሂደት በተጨባጭ የተገኘ የጽሑፍ መረጃ ነው፤ አጣሪ ኮሚቴው ያላያቸው ችገሮች ደግሞ የትየለሌ ናቸው፡፡

ስለዚህ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፤ ሁሉንም ችግሮ በዚህች አጭር ጊዜ እየፈታን እንገኛለን፤ የገጠሙንን ተግዳሮች በሚመለከት ሥራዎችን ለማፋጠን አመራሮችን በምንቀይርበት ጊዜ የባንክ ዝውውር፣ የንብረት መረካከብ /የቢሮ/ ራሱን ችሎ የተወሰነ ጊዜ ይፈልጋል፤

ስለዚህ አዲሶቹ አመራሮች ሥራውን ተረክበው ወደ ሲስተሙ አስኪገቡ ድረስ የተወሰነ ሁኔታዎችን ማጥናት አለባቸው፤ አብዛኞቹ ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን ወዲያውኑ ወደ ሲስተም መግባት ችለዋል፤ አሠራሩም እንግዳ አልሆነባቸውም፤ ችግሮቹን ለመቅረፍ ቅዳሜም፣ እሁድም ወደ ቢሮ በመግባት ጥረት አድርገዋል፤ በዚህ ጊዜ የገጠሙን ትልቅ ችግሮች በአጥቢያ ላይ ቅጥር የተፈጸመባቸው አብዛኛዎቹ ደብዳቤዎች የመዝገብ ቤት የፕሮቶኮል ቁጥር ያልጨበጡ መሆናቸው ነው፤ ይህም ጉዳዩ በውጭ የተፈጸመ መሆኑን ያሳያል፤ ሥርዓቱን ጠብቆ የተፈጸመ ቅጥር አለመሆኑንም ያሳያል፤ ይኽ በጣም አስቸግሮን ነበር፤ የደመወዙን መጠን ለማወቅ፣ ቀደም ሲል የነበረውን ባግራውንድ ለማወቅ የግዴታ መረጃዎች ያስፈልጋሉ፤

የት እንደተቀጠረ፣ ሙያው ምን እንደሆነ ለማዎቅ መረጃዎች የስፈልጋሉ፤ ይህን ለማግኘት መዝገብ ቤት ፋይል መገኘት ነበረበት፤ ነገር ግን ይህ አልተገኘም፤ መጀመሪያ ፎርም አዘጋጀን፤ ምን አልባት መረጃዎቹ በተለያዩ ቦታዎች ሲገኙ የሐሰት፣ የማጭበርበር ሥራዎች ተሠርተው ከሆነ ራሳቸውን ተጠያቂ ለማድረግ ፎርም እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡ የነበራቸውን የደመወዝ መጠን፣ የቅጥራቸውን ዓመተ ምሕረት፣ የሥራቸውን ሂደት፣ የትምህርታቸውን ደረጃ የሚመላክት ፎርም ተዘጋጀ፤ ጉዳዩ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ስናይ በረሃብ እንዳይጎዱ በዚህ መንገድ ነገሮችን ለማየት ሞከርን፤ ትልቁ ችግር ሙሉ የቅጥር መረጃ በመዝገብ ቤት አለመገኘቱ ነው፡፡

ሀገረ ስብከቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉበት፤ ይህንን ዘረፈ ብዙ ችግር መፍታት የምንችለው ተጠያቂነት ያለበት፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊነት ያለው፣ አካውንተብሊቲ ያለው የመልካም አስተዳደር ሲስተም በመዘርጋት ብቻ ነው፤ ቤተ ክርስቲያንዋ አስተዳደራዊ ሥራዎቿ በሁለት ነው የሚከፈሉት፤

እነርሱም፡-

  1. መንፈሳዊ ዘርፍ
  2. አስተዳደራዊ ዘርፍ ናቸው፡፡

አስተዳደራዊ ዘርፉን ቤተ ክርስቲያንዋ የዘመኑን ትምህርት የተማሩ ፕሮፌሺናል ሰዎች ከቤተ ክርስቲያንዋ ልጆች መካከል ብሎም ሁለቱንም አጣምረው የያዙ ሰዎች ይመራሉ፤ ይኽ የፋይናንሱንም፣ የመልካም አስተዳደሩንም፣ የሕጉንም ዘርፍ የሚከተል ነው፡

  • የሕጉን ዘርፍ በተመለከተ ደግሞ በሁለት ነው የሚከፈለው
  1. ስክረመንታል ሎው የምንለው አለ፤ (መንፈሳዊ ወይም ምሥጢራዊ ሕጎች)

ሌላው ደግሞ

  1. ፍትሕ መንፈሳዊ በዚህ ውስጥ የሚካተት ሆኖ ራሱን ችሎ በመንፈሳዊ ዘርፍ የሚዳኝ ቢሆንም በዓላማዊ የሕግ ሥርዓት የሚዳኙ ደግሞ ዘርፎች አሉ፤ ከሲቢል ሕግ ጋር ሲቢል ሎው ከምንለው ጋር አብረው የሚሄዱ፣ በዚህ ሙያም የሰለጠኑ ባለሙያ ሰዎች ያስፈልጋሉ፤ አሁን ፍርድ ጎደለ፣ ደሃ ተበደለ የሚባለው ብሂል በሚዛን መቀመጥ መቻል አለበት፤ ተበዳዩንም ለማወቅ፣ በዳዩንም ለማዎቅ፣ በግራም በቀኝም ያለውን ሚዛን ማስተዋል ያስፈልጋል፤

ስለዚህ ዳኝነት ሚዛናዊ ነው፤ ግን የሚያደላው ለእውነት ነው፤ በአንዱ አቅጣጫ እውነት ሚዛን ትደፋለች፤ እውነቱን ለማግኘት ግን በግራም በቀኝም ያሉትን ሕጎች እና ከራሳችን ኮንሸንስ (Conscience) ከራሳችን ልቡና እና አእምሮ መንፈሳዊ ቤት እንደመሆኑ በጥምረት ከሕገ ወንጌል ጋር አጣምረን የምናያቸው ነገሮች አሉ፤

መንፈሳዊ ሕጎች ደግሞ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ ናቸው፤ እነዚህ በዓለማውያን ዳኞች አይዳኙም፤ ሌሎችም በዓለማውያን ዳኞች የማይነኩ መንፈሳውያን ሕጎች አሉ፤ ሰክረመንታል ሎው የምንለው ነው፡፡

ይህ ከመንፈሳዊ ዓለም ለየት የሚያደርገው በፍትሕ መንፈሰዊ ሊታይ የሚችል፣ ክብረ ክህነትን፣ ሌሎችን ምሥጢራት የሚመለከቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊው ዓለም ያለውን ዳኝነት ውስብስብ የሚያደርገው በእስፕሪችዋል ዊንግ ያለውና በአስተዳደራዊ ዊንግ ያለውን ወይም ደግሞ በመንፈሳዊ ዘርፍ ያለውን እና በአስተዳደራዊ ዘርፍ ያለውን እና በሥራቸው ያሉትን ቅርንጫፎች ንዑስ ክፍሎችን ሁሉ የሚያካትት ነው፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚሁ ሀገረ ስብከት የሚታዩ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ የዲፕሎማቶች ማዕከል እንደመሆኑ መጠን የሚድያውም ዐይን በቀላሉ ሊያያቸው የሚችለው ቦታዎች በዚሁ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ያሉ በመሆናቸው ለሁሉም ነገሮች የተጋለጠ ነው፤

ስለዚህ በዚህ ያለው ክፍያም ከሌሎቹ የተሻለ በመሆኑ በኑሮም ደረጃ ይሁን ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ፈልሰው የሚመጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ አገልጋይ ካህናት ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ካላቸው ችግር አንጻር ማስታወቂያ እንኳን ባናወጣ ቅጠሩን ብለው ደጅ ይጸናሉ፤ አንደኛ ክፍት ቦታ ሳይኖር ነው፤ ባንድ አጥቢያ ሊኖር የሚገባው  አገልጋይ መጠን ወሰን የለውም፤ እጅግ፣ እጅግ ብዙ ነው፤ ያ ማለት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደ አንድ ሀገረ ስብከት አይደለም የሚቆጠረው፤ አንዱ ካቴድራል ብቻ አንድ ሀገረ ስብከት ማለት ነው፤ በሥሩ የሚያስተዳድራቸው ት/ቤቶች፣ ክሊኒኮች እና የአገልጋይ ካህናት የሊቃውንቱ ስብጥር ብዙ ነው፤

አገልግሎቱም ሰፊ ነው፤ አገልጋዮቹም ብዙ ናቸው፤ ኬዞቹም ሰፊ ናቸው፤ ሰው በርቀት ሆኖ ሲያየውና ገብቶ ሲያየው ይለያያል፤ በልማትም ከፍተኛ እንቅስቃሴ የለበት ነው፤ በፐርሰንትም ደረጃ ሌሎቹ አህጉረ ስብከት ተደምረው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አያህሉም፤

ስለዚህ ሶርስ ኢንካምም ነው፤ (ዋና የገቢ ምንጭ ነው)፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡

አገልግሎቱ ሃያ አራት ሰዓት ነው ምዕመናንም ሃያ አራት ሰአት ይገለገላሉ፡፡  እነዚህ ሁሉ ተደምረው ሀገረ ስብከቱ ሥራዎቹ ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ ሁሉ ተግዳሮቶቹም ዘረፈ ብዙ ናቸው፡፡

ስለዚህ በቀጣዩ አዲስ ዓመት እየተነከባለለ የመጣው ችግር መፍትሔ ካገኘ እርግጠኛ ነኝ ወደ ልማቱ ፊታችንን እናዞራለን፤ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በቅዱስ አባታችን በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ሲስተም ይዘረጋል፤ ከዚያ በኋላ ሥራውን የሚያንቀሳቅሰው ሲስተሙ ይሆናል፡፡  እንዲህ አይነት ችግሮችም አይኖሩም፤ በአዲስ ዓመት በሦስት አንኳር ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ ዕቅድ ይኖረናል፡፡

  1. ሲስተም የሚዘረጋበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው፤ በአስተዳደሩም ይሁን በፋይናንስ ሥርዓት፣ በመንፈሳዊውም አስተዳደር ዙሪያ ይሁን፣ በቅጥር ሠርዓቱም፣ ባጠቃላይ በመልካም አስተዳደርና በዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ዙሪያ ላይ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ሲሰተም መዘርጋት ነው፤
  2. ሀገረ ስብከቱ በየዕለቱ የሚያከናውናቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች በሚድያ በተደገፈ ለሕዝቡ መድረስ መቻል አለበት፤ ይህን ለማድረግ ካሁን በፊት የተጠና እንዳለ ሰምተናል እርሱን ሪቫይዝ አድርገን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ መሠረት ያየር ሰአት በመከራየት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ እቅዱ አለን፤

ሌላው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እስከ አሁን የልማት ሥራ አልተሠራም፤ ስለዚህ ብዙ መሬቶች አሉ፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም፣ ከዚያም እንዲሁ በክፍለ ከተማም ደረጃ፣ በራሱም በሀገረ ስብከቱ የተጣሉ የመሠረት ደንጊያዎች አሉ እነርሱን ማስቀጠል ነው፤

በየአጥቢያው ብዙ ልማቶች አሉ፤ ሀገረ ስብከት ግን የራሱን ልማት ማልማት አለበት፣ የንዋየ ቅድሳትን እንበል ራሱን የቻለ የማምረቻ ተቋማት እንዲኖሩት ማድረግ ነው፡፡

ስለዚህ በአዲሱ ዓመት ትኩረታችንን ወደ ልማት፣ ሲስተም ወደ መዘርጋትና ሚዲያን ለማግኘት ከቤተ ክርስቲያናችን Eotc የአየር ሰአት መከራየት ነው::ለዚህ ደግሞ ሀገረ ስብከቱ አቅሙ አለው፤

በመጨረሻም መጪው ዘመን የስኬት፣ የሰላም፣ የፍቅር እንዲሆንልን፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራትም መጪው ዓመት የልማት፣ የዕድገት የብልጽግና እንዲሆንላቸውና ሕዝቦቻቸውን በሰላም እንዲመሩ፣ ለሀገራችንም ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት እንዲሆን፤ ዘመኑ የሰላም ዘመን እንዲሆን ምኞቴ ነው”