ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከንባታ ሐድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስ ሆነው በመመደባቸው ማክሰኞ ህዳር ዘጠኝ ቀን 2007 ዓ/ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሥ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የክፍላተ ከተሞች ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ተወካዮች በተገኙበት የአቀባበል ሥነ ሥርዓት የተፈጸመ ሲሆን መርሐ ግብሩ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከተከፈተ በኋላ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አሲኪያጅ የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን የሹመት ደብዳቤ በንባብ ለጉባኤው አቅርበዋል፡፡ በማያያዝም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሠላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ባስተላለፉት የመክፈቻ ንግግር ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ወደ ጵጵስናቸው ማዕረግ ከመምጣታቸው በፊት በተለያዩ ታላላቅ ገዳማት እና አድባራት በአስተዳዳሪነት ያገለገሉና አሁንም በሊቀ ጵጵስና በተለያዩ አህጉረ ስብከት ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የቅዱስነታቸው ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡ ስለሆነ ሁሉም የሥራ ኃላፊ ብፁዕነታቸውን ሊያግዟቸው ይገባል፡፡ ከተማዋን ልናፀዳት ይገባል፡፡ ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አንችልም አባቶቻችን የገንዘብ ፍቅር ሳያሸንቸው አልፈዋል ስለዚህ ችግሮቻችንን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ከተለያዩ አድባራትና ገዳማት የመጡ የሥራ ኃላፊዎች የብፁዕነታቸውን መመሪያ በመቀበል ተግተው መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሲኪያጅም በበኩላቸው የብፁዕነታቸውን መመሪያ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ለማስፈጸም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አብራርተዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም በበኩላቸው ሥራችን ቤተክርስቲያንን ማስፋፋት ነው ዓላማችንም ፍቅር ነው ሁላችንም የቤተክርስቲያን እንደራሲዎች ነን ሕዋሳቶቻችን ድርሻ አላቸው ይሁን እንጂ ሕዋሳቱ አልታዘዝም ካሉ ችግር ይፈጠራል ተግባብተን ተደማምጠን መሥራት አለብን ሥራ በምንሠራበት ወቅት መሰናክል፣መውደቅና መነሳት፣ይኖራል ከቅዱስ አባታችን መመሪያ እየተቀበልን እንሠራለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ የመዝግያ መልዕክት እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ብሎ እግዚአብሔር ያስተላለፈውን ትምህርት መነሻ በማድረግ ከሁሉ በፊት ቤተክርስቲያንን ልናስቀድም ይገባል ዋናው ሥራችን ቤተክርስቲያን የምታድግበትን ሥራ ተግባብተን መሥራት ነው የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ናት ተብሎ እንደተጻፈ የተቀደሰችውን ምድር ተግተን ልናገለግል ይገባናል፡፡
ከተማችን ዓለም አቀፍ ከተማ ናት ዛሬ የተሰበሰብነውን የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን ተደራቢ ሥራ ለመባረክ ነው ብፁዕነታቸው ጠንቃቃ መነኩሴ መሆናቸውን እናውቃለን ችግሮቻችንም ያፈታሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ሀሜትና ነቀፋ አስፈላጊ አይደለም ለቤተክርስቲያን እና ለሃይማኖታችን የሚበጀውን መሥራት አለብን፡፡
ከሁሉም በላይ ለሰላም መጸለይና መሥራት አለብን ሰላም ካለ አምልኮተ እግዚአብሔር አለ ሁሉም ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖረው ያስፈልጋል በየጊዜው መወያየት አለብን በማለት ሰፋ ያለ አባታዊ መመሪያ ከሰጡ በኋላ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡
{flike}{plusone}