ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ካቴድራል ሊያሠራው ያሰበውን ባለ 8 ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ!!!
የአዲስ አበባ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ካቴድራል ሊያሠራው ያሰበውን ባለ 8 ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሊኖሩ ከተገቡ ተቋማት መካከል አንዱ የትምህርት ተቋም በመሆኑ ይህንን ተቋም ለመገንባት አስባችሁ ወደ ተግባር ስለገባችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከቀድሞ ጀምሮ ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣ ፊደል በመቅረጽ ትውልዱን በሞራል፣ በሥነ ምግባርና በልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፍ ያስተማረች ትልቅ የሀገር ባለውለታ ነች ሲሉ ተደምጠዋል።
አክለውም ሥራ ፈቶ የቆየውን ቦታ በማጥናት ለራስ አገዝ ገቢ ለመጠቀም መንቀሳቀስ መልካም ነው፣ በአጭር ጊዜ ትምህርት ቤቱ ተሰርቶ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካና ልጆቻችሁ እዚሁ እንዲማሩ ካህናት የንስሐ ልጆቻችሁን በማስተባበር፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች በዕውቀትና በጉልበታችሁ በማገዝ ጅማሬውን እውን አድርጉ ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትና ልማት ኮሚቴ በጥምረት በቀረበው ሪፖርት እንደተገለጸው የልማት ኮሚቴው የካቴድራሉንና የልማት ቦታውን የመሬት አጠቃቀም/Master plan/ በማስቀደምና የካቴድራሉን ይዞታ 2 ሚሊየን በሚሆን ወጭ አጥር በመከለል፣ የካቴድራሉን የውጭ በሮች በመገንባትና የመቃብር ቦታውን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማስተካከል ከፍተኛ ሥራ መሥራቱ አብራርቷል።
የቤተ ክርስቲያንን ክብር በሚመጥን መልኩ ቀጣዩን ትውልድ ለመቅረፅ በዕለቱ የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠለት ባለ 8 ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ ዘመናዊ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ክፍሎችን የሚያጠቃልል መሆኑ ተገልጿል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ገብረ ሚካኤል በዕለቱ ተገኝተው የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትንና ተጋባዥ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው በካቴድራሉ ልማት ላይ ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ያደረጉትን አካላት አመስግነዋል።
በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” በሚል መነሻ ሐሳብ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አምላኩ የተቀበለውን ዘለዓለማዊ ብርሃን ለትውልድ የሚተርፍ መልካም ሥራ በመሥራት ለሌሎች መግለፅ እንደሆነ አስረድተዋል።
እኛ ያለንበት ዘመን መገፋፋትና ጨካኔ የበዛበት ወቅት ነው:ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ያለፈ ጊዜ የትምህርት አሰጣጥ ውጤት በመሆኑ ካቴድራሉ ሊያሠራ ባቀደው ትምህርት ቤት ትውልዱን በሥነ ምግባርና መንፈሳዊ ትምህርት ሊያቃናው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩም የአዲስ አበባ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ፣የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ገ/ሚካኤል፣ የካቴድራሉ ካህናትና የ/ት/ቤት ወጣቶች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶችና የአካባቢው ምዕመናን ተገኝተዋል።
በመ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ