ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በተገኙበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት እየተሰጠ የቆየው ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቀቀ!!
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ሥር ለሚገኙ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች በክፍለ ከተማው የትምህርትና ስልጠና ክፍል አስተባባነት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ ለሁለት ቀናት እየተሰጠ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ መመሪያ ሰጭነት በዛሬው ተጠናቋል፡፡
በዕለቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ም/ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና ከመንፈሳዊ የእረኛነት ጽንሰ ሐሳብ ምንነት ጀምሮ፡የእረኝነት ሥራ በሁለቱ የኪዳን ዘመናት ምን ይመስል እንደነበርና ዛሬ ባለንበት ዘመን በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስላለውና ሊኖር ስለሚገባው የእረኝነት አገልግሎት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡ከተሳታፊዎች ለተነሡ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የዕለቱን መርሐግብር የመሩት የክፍለከተማው የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ መ.ር ልሳነወርቅ
አሸናፊ በክፍለ ከተማው ልዩ ልዩ ክፍሎች አስተባባሪነት የተጀመረው እንቅስቃሴ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው በቅርብ ጊዜም በግጭት አፈታትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ በሰው ኃይል አስተዳደርና በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍልየጋራ ትብብር የሚሰጥ ስልጠና እንደሚኖርም አሳውቀዋል፡፡
የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎችም በሁለቱም ቀናት የተሰጡት ስልጠናዎች እጅግ ጠቃሚና አነቃቂ መሆናቸውን አውስተው፡በሚቀጥሉት ስልጠናዎች ግን የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚገዳደሩ አንገብጋቢ ችግሮች እና አፋጣኝ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡
በመጨረሻም የጉራጌና አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ችግሮችን ለመፍታትና የአገልጋዮችን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ያደረገውን ጥረት ከልብ እናመሠግናለን እናደንቃለንም፡ ወደፊት ግን በማዕከላዊነት የተደራጀ ሆኖ በሀገረ ስብከቱ የትምህርትና ስልጠና በበላይነት የሚመራ መሆን እንዳለበት አሳውቀዋል፡ እንደዚህ ዓይነት ጉባኤ ሲኖር የጉባኤ ተሳታፊዎች የቤተ መልክ ያለው አለባበስ ለብሰው እንዲመጡም መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል አስተባባሪነት በደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል
ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ
“ኦርቶዶክሳውያን ከየት ወደየት ከባቢያችንስ”
በሚል ርእስ የገዳማትና አድባራት ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች እና የሰ/ት/ቤት አመራሮች
በተገኙበት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና መሰጠቱ
የሚታወስ ነው፡፡
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ:-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ