ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ደቀመዛሙርትን፣ መነኮሳትንና የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን በመጎብኘት የልደት በዓልን አከበሩ!

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ደቀመዛሙርትን፣ መነኮሳትንና የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን በመጎብኘት አከበሩ።

ብፁዕነታቸው በወልቂጤ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ግቢ በመገኘት በዚያው ከሚኖሩት አበው መነኮሳት፣ የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት ጋር በመሆን በዓለ ልደትን አክብረዋል።

ደቀ መዛሙርቱ የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትን በተመለከተ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል “(ት.ኢሳ 9:6) በሚል ርዕስ መነሻነት የክርስቶስን ልደት አስተምረዋል።

ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞትንም ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን መነሣቱንና በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሰላምን የሚሰጥ በመሆኑ ምክንያት “የሰላም አለቃ” ተብሎ መጠራቱንም ጠቅሰዋል።

በደቀ መዛሙርቱ የመመገቢያ አዳራሽ የተዘጋጀውን የምሳ ማዕድ በጸሎት ከባረኩ በኋላ ከደቀመዛሙርቱ፣ ከመምህራኑና ከመነኮሳቱ ጋር የፍቅር ማዕድ (አጋፔ) መርሐግብር አካሂደዋል።

በተያያዘም ብፁዕነታቸው በእዣ ወረዳ በአገና ከተማ ወደሚገኘው ደ/መ የገጨ አቡነ ሳሙኤል ገዳም በማቅናት በገዳሙ የሚኖሩትን መናንያን አባቶችና እናቶች፣ የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርትን ጎብኝተዋል።

” ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና “(ሉቃ 2፥11) የሚለውን መለኮታዊ ቃል መነሻ በማድረግ ልደቱን በተመለከተ ትምህርተ ወንጌል አስተላልፈዋል።

ዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ መድኃኒት ሆኖ የተሰጠበት እንደሆነም አብራርተዋል።

መልአኩ እንደተናገረው ክርስቶስ “ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ” (ሉቃ 2፥10) መሆኑንም አብራርተዋል።

ብፁዕነታቸው ከገዳሙ ሲመለሱ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በኤዋን ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ልዩ የልደት መርሐ ግብር አካሂደው ጨርሰው ወደ ዩኒቨርስቲያቸው አስፋልቱን ሞልተው እየዘመሩ ሲመለሱ አግኝተዋቸው ከመኪናቸው ወርደው ተማሪዎቹን ባርከዋል።

አብረውም የልደት መዝሙርን ደስ በሚል መልኩ ዘምረዋል።

ተማሪዎቹም በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ሆነ በአካዳሚክ ትምህርታቸው ጠንካራና ብርቱ እንዲሆኑ መክረዋቸዋል።

በመጨረሻም የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ መልእክት አስተላልፈው ጸሎት አድርገውላቸዋል።

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ