ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰ/ት/ቤት “ራዕየ ቴዎፍሎስ” በሚል ስያሜ ሊያስገነባ ያቀደውን ሕንጻ ሥራውን አስጀመሩ
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመገኘት በሰ/ት/ቤቱ “ራዕየ ቴዎፍሎስ” በሚል ስያሜ ሊገነባ የታቀደውን ሕንጻ ሥራውን አስጀመሩ።
ብፁፅነታቸው ሰንበት ትምህርት ቤት ለቤተክርስቲያን የችግኝ ጣቢያ ነው ሲሉ የሰንበት ትምህርት ቤትን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።
የችግኝ ጣቢያ ችግኝ የሚበቅልበትና ለተለያዩ ቦታዎች ሥርጭት የሚደረግበት እንደሆነ ሁሉ ሰንበት ትምህርት ቤትም ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ ጳጳሳት፣ ለቤ/ክንና ለሀገር የሚጠቅሙ ትውልዶች የሚወጡበት መሆኑን አብራርተዋል።
ትውልድን በመንፈሳዊ እውቀት ለመገንባትና ለማልማት ታስበው የሚሠሩ ሕንጻዎችም እጅጉን ሊበረታቱና ሊደገፉ እንደሚያስፈልግ ብፁዕነታቸው ጠቅሰዋል።
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21፥15-17 ያለውን መለኮታዊ ቃል መነሻ በማድረግ በበጎች፣ በጠቦትና በግልገል የተመሰሉትን አረጋውያንን፣ ወጣቶችንና ሕጻናትን የመጠበቅና የማስተማር የቤተክርስቲያን ድርሻ መሆኑንም አስተምረዋል።
ብፁዕነታቸው በካቴድራሉ የሚገኘውን “ቤተ መዘክር ዘቴዎፍሎስ ፓትርያርክ” ተብሎ የተሰየመውን ቤተ መዘክርም ጎብኝተዋል።
ካቴድራሉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ እንደተመሠረተ ከመድረኩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ሊሠራ የታሰበው ሕንጻ መሠረቱ ከተጣለ በኋላ ለረዥም ጊዜ ሥራው እንዳይጀምር ብዙ መሰናክሎችና እንቅፋቶች እንደነበሩ አውስተዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአመራር ዘመን ያሉት ችግሮች ተፈተው ሥራው መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰዋል።
ሊሠራ የታሰበው ሕንጻ G+3 ሁለገብ ሕንጻ ሆኖ 600 ካሬ ቦታ ላይ ያረፈ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
ሕንጻው ሲጠናቀቅ ትውልድን በመንፈሳዊ እውቀት በመገንባት በኩል ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች የሰ/ት/ቤቱ ሊቀ መንበር ዲ/ን ያዕቆብ ቦጋለ አብራርተዋል።
የሰ/ት/ቤቱ የተልዕኮ ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ዲ/ን ዮናስ ኢሳይያስ ሀገረ ስብከቱ የካቴድራሉን ጥያቄዎች ተቀብሎ ምላሽ በመስጠቱ አመስግነዋል።
በካቴድራሉ 820 ሕጻናትና 450 ወጣቶች በመደበኛ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ስለመሆናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም 400 ገደማ የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች በተልዕኮ የመንፈሳዊ ትምህርት እየተከታተሉ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።
ሰንበት ት/ቤቱ ለብፁዕነታቸው፣ ለክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁና ለካቴድራሉ አስተዳዳሪ ስጦታ አበርክተዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን አባ ገብረ ሥላሴ (ቆሞስ)ና የሰንበት ት/ቤት አባላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ