ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የደብረ እንቁ ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን የልማት ሥራዎችን ጎበኙ!!!

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደብረ ዕንቁ ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን እየተሰራ ያለውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እና 64 ሜትር የሚረዝመውን የመስቀል ፕሮጀክት ግንባታን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ለብፁዕነታቸው ከሕንፃ አሰሪ ኮሚቴ እና ከአካባቢው  ምዕመናን ስለገጠማቸው አጠቃላይ ተግዳሮት አስረድተዋል።

ብፁዕነታቸው በበኩላቸው ወቅቱ ዓብይ ጾም በመሆኑ ምዕመናን ጾሙን በተረጋጋ መንፈስ መጾም እንዳለባቸው እና እንዲህ ዓይነት ተግዳሮት ሲገጥም በደብዳቤ የሚፈታ ስለሆነ ችግሩን ዘርዝራችሁ አቅርቡልኝ ሲሉ መምሪያ ሰጥተዋል።

ከጥርጣሬ በፀዳ መልኩ በህግ የተደገፈ ቅሬታ ካለ ቤተ ክርስቲያን ታሸንፋለች ብለዋል።

በደብረ እንቁ ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እየተገነቡ ያሉ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ናቸው ከሚለው ጥርጣሬ ባለፈ ተጨባጭ ነገር ከመጣ እሰከሚሄድበት ድረስ ሄደን  የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም እናስጠብቃለን ሲሉ ብፁዕነታቸው በአጽንኦት ተናግረዋል።

የደብረ እንቁ ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በማስረጃ ተደግፎ ከቀረበ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ልማቷን የሚያደናቅፍ ከሆነ እንደመስቀል አደባባይ እና እንደጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት እኩል እናየዋለን ብለዋል።

መስቀል ለክርስቲያኖች ቤዛችን መሆኑ እንዳለ ሆኖ የመስቀል ፕሮጀክቱም  ለዓይን ማራኪ ለከተማም ውበት የሆነ  የመስቀል  ልማት መሆኑን ብፁዕነታቸው አድንቀው አበረታታዋል።

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ያሉ ይዞታዎችን በህገ ወጥ መንገድ የማጠርና አገልጋዮችን የማዋከብ ተግባር እንዲቆምልን ሲሉ ለብፁዕነታቸው ጠይቀዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርትና ሥልጠና ክፍል ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ምህረት በቃሉ ወርቅነህ እና ዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ምህረት አምሃ መኳንንት እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

    በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ
   ፎቶ በዋሲሁን ተሾመ