ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በግንባታ ላይ የሚገኘውን ግዙፉን የጀሞ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ሕንጻ ቤ/ክ ጎበኙ

በዛሬው ዕለት የካቲት 2/2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን እየተገነባ የሚገኘውን ግዙፉን የጀሞ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ሕንጻ ቤተክርስቲያን ጎብኝተዋል።
ብፁዕነታቸው እየተገነባ ያለውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ያደነቁ ሲሆን ግዙፉ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሲጠናቀቅ ለአገልግሎት ምቹ ከመሆኑም ባሻገር ብዙ ምእመናን በአንድ ጊዜ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
አያይዘውም ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንዲህ ተውቦና አምሮ በመገንባት ላይ የመገኘቱ ምሥጢር የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣የአስተዳደር ሠራተኞች፣ ማኅበረ ካህናቱና የአከባቢው ምእመናን በመናበብና በመቀናጀት አብሮ በጋራ በፍቅር መሥራት እንደሆነ አብራርተው ሌሎችም አድባራትና ገዳማትም ከዚህ ደብር ብዙ ልምድ ሊማሩና ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
በመቀጠልም ብፁዕነታቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽህፈት ቤት በመገኘት የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ዘካሪያስ አዲስ የጽህፈት ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴ ለብጹዕነታቸው አስረድተው ክፍለከተማው የተለያዩ መሰናክሎችን ተቋቁሞ ጠንክሮ እንደሚሠራም አብራርተውላቸዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ