ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤልና ቅ/አርሴማ ቤ/ክ ዓመታዊው የቅድስት አርሴማ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብረ
በዛሬው እለት በቀን 6/2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ሰናይ ባያብል፣የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣የደብሩ ካህናትና ዲያቆናት፣የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤልና ቅ/አርሴማ ቤ/ክ ዓመታዊው የቅድስት አርሴማ ክብር በዓል በያሬዳዊ ዝማሬና በሥርዓተ ቅዳሴ በድምቀት ሲከበር ውሏል።
በክብረ በዓሉ ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ሰናይ ባያብል ለብፁዕነታቸው “የእንኳን ደህና መጡልን” መልእክት አስተላልፈዋል።
መጋቤ ሐዲስ አባ ጸጋ ዘአብ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመጽሐፍ መምህር የሆኑት በብፁዕነታቸው መልካም ፍቃድ የእለቱን ትምህርት “በወልድ ውሉዳውያን በክርስቶስ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን የተሰኙ ፍጹማን ናቸው” በሚል ርእስ ተነስተው ለምእመናኑ በዓሉን የሚገልጽ ትምህርት አስተላልፈዋል። አያይዘውም እኛም እንደ ቅዱሳን መከራንና ፈተናን በመታገስና በጽናት በማለፍ ክርስትናችንን በጽናት ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” ራእ. ምዕ 2 ቁጥር 10 ላይ የሚኘውን ሕያው የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል አንስተው እለቱን በተመለከተ አብራርተውና አመሳጥረው ያስተማሩ ሲሆን፤ በዛሬው እለት የመሰብሰቢያችን ምክንያት ቅድስት አርሴማ ናት ፣ቅድስት አርሴማ በወጣትነት ዘመኗ የውስጥና የውጭ ፈተናን በመቋቋም ሰማዕትነቷን አስመስክራለች፣በልቧ ሰማያዊውን ንጉስ ስላነገሰች ለምድራዊው ንጉስ መከራ አልተሸነፈችም ብለዋል።
አያይዘውም ለወጣቱ እንደ ቅድስት አርሴማ በእምነት በመጽናት፣በጽድቅና በቅድስና በመኖር እግዚአብሔርን ልናስደስት ይገባል፣ዐይኖቻችን ክፋትን ከማየት፣ ጆሮዎቻችንም መጥፎውን ከመስማት፣አንደበታችንም ከሀሜት፣እግሮቻችንም ወደ ክፉ መንገድ ከመሄድ መራቅ አለባቸው በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው ለሕዝበ ምእመናኑ ቡራኬና ቃለምዳን ሰጥተው ወደ ሥርዓተ ቅዳሴ ተገብቷል።
ከቅዳሴ መርሃ ግብር በኋላ ብፁዕነታቸው ከክፍለ ከተማው ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና ከልዑካን ጋር በመሆን አዲስ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቴ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ