ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በመንበረ መንግሥት /ግቢ/ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓመታዊው የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል
በዛሬው ዕለት ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና የመንበረ መንግሥት /ግቢ/ ቅዱስ ገብርኤል ገዳማት የበላይ ጠባቂ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ብ ሳሙኤል ደምሴ፣የአራዳና ጉለሌ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/አሚን ቆሞስ አባ ላ/ማርያም ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ሰ ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ በላይ፣የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣የገዳሙ ካህናትና ዲያቆናት፣የገዳሙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በመንበረ መንግሥት /ግቢ/ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓመታዊው የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በያሬዳዊ ዝማሬና በሥርዓተ ቅዳሴ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
መርሃ ግብሩን የመሩት የገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ሰ ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ በላይ ለዚች ዕለት በምሕረቱና በቸርነቱ ያደረሰንን እግዚአብሔርን አመስግነው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የዕለቱን ትምህርት የሰጡት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሲሆኑ ” የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” (መዝሙረ ዳዊት 34:7) በሚል ርዕስ ተነስተው ለምእመናኑ ክብረ በዓሉን የተመለከተ ትምህርት አብራርተውና አመሣጥረው አስተምረዋል፤ በትምህርታቸውም፦ የሲድራቅ፣የሚሳቅና የአብደናጎምን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን የእምነት ጽናትና የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት ያለውን ፈጣን ተራዳኢነት አብራርተዋል፤ መላእክት ሥራቸው እግዚአብሔርን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ በማለት ማመስገንና የሰው ልጆችን ማገዝና መርዳት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት በአማላካቸው የታመኑትን ሦስቱን ወጣቶች በሚነደው እሳት እንዳይቃጠሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ታድጓቸዋል፤እግዚአብሔር እውነተኛና የታመነ አምላክ ስለሆነ በእርሱ የሚታመኑትን ዘወትር ከክፉ ነገር ይጠብቃቸዋል፤ በሲድራቅ፣በሚሳቅና በአብደናጎም ሕይወትም የተመለከትነው ይህንኑ እውነት ነው፤ሦስቱ ወጣቶች በወጣትነት ዘመናቸው የውስጥና የውጭ ፈተናን በመቋቋም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት አስመስክረዋል፤ በሕይወታቸውና በልባቸው ውስጥ ሰማያዊውን ንጉሥ ስላነገሡ ምድራዊው ንጉሥ ያቀጣጠለውን እሳት አልፈሩም፤ ላቆመውም ግዑዝ ጣዖት አልሰገዱም በማለት አስተምረዋል፤ መላእክት ከእግዚአብሔር ታዘው ወደ እኛ በመምጣት ከተለያየ መቅሰፍትና መከራ ይጠብቁናል ሲሉ በፁዕነታቸው አብራርተዋል።
አያይዘውም ለወጣቱና ለምእመናኑ እንደ ሲድራቅ፣ሚሳቅና አብደናጎም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በእምነት በመጽናት፣ነውር የሆነውን ነገር በመጸየፍ፣በሕይወታችን ላይ ግዑዝ የሆነውን ነገር ሳይሆን ሕያው የሆነውን እግዚአብሔርን በማንገሥ፣ እርሱን እግዚአብሔርን በማምለክና ለእርሱ በመስገድ ፣ለፈጣሪያችን በመታመን፣ በጽድቅና በቅድስና ሕይወት በመኖርና የተፈጠርንበትን ዓላማ በማሳካት እግዚአብሔርን ልናስደስተው ይገባል ብለዋል፤እንደ ሦስቱ ወጣቶች መከራንና ፈተናን በመታገስና በጽናት በማለፍ የእምነት አርበኞች ልንሆን ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም በተለያዩ ቦታዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ምእመናን ጸሎተ ምህላ ተደርጎ፤ በብፁዕ አቡነ ሰላማ ለሕዝበ ምእመናኑ ቡራኬና ቃለምዳን ተሰጥቶ ወደ ሥርዓተ ቅዳሴ ተገብቷል።
ዘጋቢ፦ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ዌብማስተር ፦ መ/ር ዘሩ ብርሃኔ
ፎቶ ፦መ/ር ዋሲሁን ተሾመ