ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች በቪድዮ ኮንፈረንስ የታገዘ የቴክኖሎጂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ!!

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ የሀገረ ስብከቱና የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ቴክኖሎጅ ተኮር ግንዛቤ ማስጠበጫ በቪድዮ ኮንፈረንስ (video conference) በመታገዝ ተሰጥቷል፡፡
የቪድዮ ኮንፈረንስ ሥልጠናውን የሰጡት በኖርዌይ ሀገር የሚገኘው የተክሌ ኮንሰልቲግ ባለቤት ኢ/ር ኪዳኔ መብራቱ እና በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆነው ዲ/ን ተመስገን ቅጣው ሲሆኑ የሥልጠናውም ዓላማ በጽ/ቤቱ እየተዘረጋ የሚገኘው ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር በተሻለ መልኩ ለማደራጀትና ለማስቀጠል መሆኑም ተገልጿል፡፡
በሥልጠና መርሐ ግብሩ ላይ ከቴክኖሎጅ ጽንሰ ሐሳብ ምንነት ጀምሮ፣ በዓለማችን፣ በሀገራችን እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ስላለውና ሊኖር ስለሚገባው የቴክኖሎጅ ትግበራ፣ እንዲሁም ስለ ቴክኖሎጂ ዋና ክፍል አደረጃጀትና እና ስለ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ቀረጻ ሂደት ሁለቱ ባለሙያዎች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
አያይዘውም በሀገረስብከቱ ደረጃ የተጀመረው የቴክኖሎጅ ጅማሬ ተስፋ የሚጣልበት ቢሆንም ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቴክኖሎጂ ረገድ የተከተለችው መርህ ግን እምብዛም አጥጋቢ አለመሆኑን ገልጸው ወደፊት ለሚደረገው የቴክኖሎጂ ትግበራና የፕሮጀክት ቀረጻ ለእናት ቤተ ክርስቲያናቸው በትሩፋት ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ቃል ገብተዋል፡፡
በሥልጠናው የተሳተፉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ስልጠናው ሀገረ ስብከቱ ለጀመረው ቴክኖሎጂ ተኮር ዘመናዊ አሠራር ከመሆኑም በላይ አሁን ላለንበት ዘመን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡ ከሚተገበሩ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች አንዱ የሆነው ዘመናዊ የባለጉዳይ መከታተያ አሁን እየታየ ያለውን ሰፊ የሥራ ጫና እንደሚያቀል ገልጸዋል። ለአቅራቢዎቹም በሚተገበረው የቴክኖሎጂ በበጎ ፈቃደኝነት ሥልጠናውን ለሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎችም ከፍ ያለ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ወደፊትም እንደዚህ ዓይነቱ ሥልጠና እንዲቀጥልና ሀገረ ስብከቱን በዘመናዊ አሠራር ለማደራጀት በሚደረገው ጥረት ባለሙያዎቹ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው