ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በተዘጋጀው ዐውደ ወንጌል ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጉባኤ ተገኝተው ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ምዕዳን ሰጡ

የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በተዘጋጀው ዐውደ ወንጌል ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጉባኤ ተገኝተው ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።
በጉባኤው ክቡር መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፥ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ የሀገረ ሰብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፥ ሊቀ ሥልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋየ (ቆሞስ) የደብሩ አስተዳዳሪ፥ የደብሩ ካህናት አገልጋዮች፥ ዘማርያን፥ ሰባክያነ ወንጌል፥ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርከት ያሉ ምእመናን ተገኝተዋል።
ጉባኤው በካቴድራሉ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየ ዐውደ ወንጌል ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሆኑን ተገልጿል።
በዕለቱ በተለያዩ ሰባክያነ ወንጌል ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል፥ በሊቃውንት ያሬዳዊ ዝማሬና በዘማሪት ምርትነሽ መዝሙር ቀርቧል።
የዕለቱ መርሐ ግብር በካቴድራሉ ዋና ጸኃፊ መጋቤ ሥርዓት ልዑል ሰገድ የተመራ ሲሆን የመጀመሪያው ተጋባዥ ሰባኪ አባ አትናቴዎስ ወልደጎርጎሬዎስ የሐመረ ብርሃን ዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ርእሰ መምህር ” እግዚኦ መኑ የሐድር ውስተ ቤትከ፤ አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?” (መዝ 15:1) በሚል የመዘምሩ ቃል መነሻነት ዕለቱን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል።
በእግዚአብሔር ቤት እሱ ራሱ ባለቤቱ ቅዱስ እግዚአብሔር፥ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምና ቅዱሳን መላእክትን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳኑ ይገኙበታል ካሉ በኋላ፡ እኛም እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሠረት በቃሉ ጸንተን በቅድስና በቤቱ ልንኖር ይገባል ብለዋል።
በመቀጠልም ልሣነ ክርስቶስ ጳውሎስ መልክዓ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ የቦሌ ደብረ ሳሌም የስብከተ ወንጌል ኃላፊ “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ።” (ዮሐ 2:16) በሚል መነሻነት 3ኛ ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፆም (ምኩራብ) በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት አስተምረዋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብቶ ቤቱ እንዳጸዳ ሁሉ ወደ አምላክ እየጸለይን ቤተ መቅደሳችን እናጽዳ። ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር የሚገኝበት፥ ድኅነተ ሥጋና ድኅነተ ነፍስ የምናገኝበት፥ ከእግዚአብሔር የምንገናኝበት የቅድስና ቤት ነውና በቅድስና እየኖርን ቤተ መቅደሳችን ከክፋት፥ ተንኮል፥ ዘረኝነት፥ ቂምና በቀል በማጽዳት፥ ውስጣችን አንጽተን በንሥሓ ተመልሰን በቅድስና እንኑር ብለዋል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋየ በበኩላቸው ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና ዋና ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ በጉባኤው ተገኝተው ላስተማሩና ለዘመሩ እንዲሁም ለጉባኤው ስኬት ለተሳተፉት አካላት ሁሉ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማም የካቴድራሉ አመሠራረትና ዕድገት በማውሳት እሳቸውም በካቴድራሉ ሲያገለግሉ እንደነበሩና አሁንም በይበልጥ ካቴድራሉን እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል።
በጉባኤው የተገኙት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መርሐ ግብሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ጉባኤው መቀጠል እንዳለበት ተናገረዋል ።
የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት ምግብና የሕይወት ውሃ ስለ ሆነ ነፍሳችን ዘወትር የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል።
ለክርስቶስ ወንጌል እንደ ሚገባ ኑሩ አንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል ሰምተን በቃሉ መሠረት እየኖር ለእግዚአብሔር መንግሥት ተዘጋጅተን መኖር አለብን ብለዋል።
የቤተ ክርስቲያን ዋና ዓላማ ወንጌልን ማስተማር ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ቅዱስ ጳውሎስ በጊዘውና ያለጊዜው ቃሉን ስበክ እንዳለው እኛም ዘወትር ቃሉን መስበክ አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ምእመናኑን በመባረክና አባታዊ መመሪያን በማስተላለፍ ጉባኤው በጸሎትና በቡራኬ ተዘግቷል።
ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ወሲሁን ተሾመ