ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ!

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት አስመልክተው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

በዓሉን ስናከብር “የበዓሉን መንፈሳዊ ጭብጥ መልእክት” ከልብ በመረዳትና በመገንዘብ መሆን እንዳለበት ብፁዕነታቸው አሳስበዋል።

ሐዋርያው የተናገረውን ” …ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፤ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6፥4-5) የሚለውን መለኮታዊ ቃል በውስጣችን በማሰብ ማክበር እንደሚገባን መልእክት አስተላልፈዋል።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን ራሱ ከፈጸመ በኋላ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ በማለት (ማቴ 28፥19-20) ትዕዛዝ ማስተላለፉን ገልጸዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የመጠመቁ ዓላማ ምሥጢረ ሥላሴን ለመግለጥ (ማቴ 3፥16-17)፣ ጽድቅን ሁሉ ሊፈጽም (ማቴ 3፥15) እና አርአያ ሊሆነን እንደሆነ አብራርተዋል።

አክለውም በዓሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ በመሄድና በእርሱ እጅ በመጠመቅ (ማቴ 3፥13-15) ትህትናን በተግባር ፈጽሞ ያሳየበትና ያስተማረበት ዕለት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እግዚአብሔር አብ ” በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ” (ማቴ 3፥17) ብሎ የተናገረውን አብራርተው እኛ ደግሞ ክርስቶስ ሕይወታችን መሆኑን ዘወትር በእምነት እያሰብን ደስ ልንሰኝ ይገባል ብለዋል።

እኛም የክርስቶስን ፈለግ በመከተል የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ወላጅ አልባ ሕጻናትን በመጎብኘትና በመንከባከብ፣በኃዘን ላይ ያሉትን በእግዚአብሔር ቃል በማጽናናት ትህትናን አብዝተን በተግባር ልንፈጽም ይገባል ሲሉ መክረዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሀገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ እና በብዙ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የተለያዩ ዕርዳታዎችን እያደረገች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።

በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በቻልነው አቅም መርዳት የዜግነት፣ የሃይማኖት እና የሰባዊነት ግዴታ መሆኑን ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም ብለዋል።

በዓለ ጥምቀት በአደባባይ የሚከበር በዓል ስለሆነ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምንጣፍ የሚያነጥፉ ወጣቶች እና ምእመናን በየቦታው ለአባቶችና ለመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካላት በትህትና እንዲታዘዙ አሳስበዋል።

የበዓለ ጥምቀቱ አከባበር በሰላም እንዲፈጸም በስሜት ሳይሆን በማስተዋልና በእምነት፣ በራስ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ በመደማመጥና በመናበብ ማክበር እንደሚገባ አባታዊ መመሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በዓሉ የሰላም፣የጤና፣ የአንድነትና የፍቅር እንዲሆን ከልብ ተመኝተዋል።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese