ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ!
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
መልአኩ የተናገረውን ” …ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” (ሉቃ 2፥10-11) የሚለውን መለኮታዊ ቃል በውስጣችን በማሰብ ማክበር እንደሚገባን አሳስበዋል።
ክብረ በዓላትን ስናከብር በአንዳንዶች ዘንድ እንደተለመደው የሚበላና የሚጠጣ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ተቆጥበን፤ይልቁንም ከምንም በላይ መንፈሳዊ መልእክቱና ይዘቱ ላይ ትኩረት በማድረግ ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዕለቱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የተሰጠበት መሆኑን በማስታወስ፣ ወደ ዓለምም የመጣበት ዓላማ ” … እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴ 1፥21)ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው ከኃጢአታችን ሊያድነን መሆኑን አብራርተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁላችንም ብሎ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ እንዳዳነን፤ ሞትንም ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን በመነሣት በትንሣኤው ሕያዋን እንዳደረገን ከልባችን በማመንና በማሰብ ልደቱን ማክበር አለብን ብለዋል።
አያይዘውም እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ለእኛ መስጠቱን በማሰብ የተቸገሩትን ልንረዳ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምግብ ላጡት ምግብ በመስጠት፣ አልባሳት ለሌላቸው አልባሳት በመስጠት፣የታሰሩትን በመጠየቅ፣ወላጅ የሌላቸውን ልጆች በመንከባከብ፣በብቸኝነትና በኃዘን ላይ ያሉትን በመምከርና በማጽናናት በዓሉን ስናከብር “በፍቅሬ ኑሩ” ብሎ ያዘዘንን ትዕዛዝ እንፈጽማለን ሲሉ ተደምጠዋል።
በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ ሰላምን ላጡት፣ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና በማረሚያ ቤት ለሚገኙት ወገኖቻችን ጸሎትን በማድረግ መንፈሳዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባልም ብለዋል።
በመጨረሻም በዓሉን በጭፈራ ሳይሆን “አቤቱ ይቅር በለን፣ማረን” በማለት ንስሐ እየገባን እድናከብር አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ