ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም መግባትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ ቃለ በረከትና ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መመሪያ አስተላለፉ
ብፁዕነታቸው ሱባኤው በሥርዓትና መልስ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ መከናወንን እንዳለበት አሳስበዋል።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
በመላው ዓለም የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮች ምእመናንና ምእመናት እንኳን ለ፳፻፲፯ ዓ/ም ጾመ ፍልሰታ ለማርያም በጤና አደረሳችሁ።
“ተመየጡ ኀቤየ ወተሐይዉ በጾም ወበጸሎት ወበርትዕት ሃይማኖት
“በጾም በጸሎት በእውነተኛ ሃይማኖትም ወደ እኔ ተመለሱ ትድናላችሁም” ቅዱስ ያሬድ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት ጸንታ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ናት።
ክርስቶሳዊ የመሆን የመጨረሻው መዳረሻ እርሱን አምኖ በእርሱ ኖሮ ከሞት ባሻገር ባለው በዘለዓለማዊ ሕይውት ታምኖ የመንግስቱ ወራሽ የክብሩ ቀዳሽ መሆን ነው።
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር በተባለው መጽሐፉ የክርስቲያን ናፍቆት ሰማያዊ፣ መውጣት መግባቱና ውሎ ማደሩም ክርስቲያናዊ እንደሆነ ሲገልጥ “እኔ ክርስቲያን ሆኜ እውል ዘንድ ክርስቲያን ሆኜ አድር ዘንድ፣ ክርስቲያን ሆኜም እተኛ ዘንድ፣ ክርስቲያን ሆኜም እነሣ ዘንድ ክርስቲያን ሆኜ ሞቼ ክርስቲያን ሆኜ እነሳ ዘንድ እወዳለሁ” በማለት ይገልጻል።
ክርስርስትና እምነትን ከምግባር አስተባብሮ የመኖር ሕይወት ነው።
በኦርቶዶክሳዊት ክርስትና በተግባር ከምነገልጻቸውና ዋጋ ከምናገኝባቸውና የሰማያዊ ሥርዐት የመንግሥተ ሰማይ ሕይወትን ከምንለማማዳቸውን የተግባር የሕይወት መንገዶች መካከል ጾምና ጸሎት ይገኙበታል።
የጾም ቀጥተኛ ፍች በታወቀ ጊዜ በተመጠነ ሰዓት ሥጋን ከምግብ መከልከል መተወ እንደሆነ መጻሕፍት ይናገራሉ።
ጸሎት ደግሞ ቃሉ በሱርስት ቋንቋ ጸሉታ የሚለውን ቃል መሠረት የሚያደርግ ሲሆን ነፍስና ሥጋ መንፈስና አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ሥምረት የሚጠቁም ሆኖ ይገኛል ።
ጸሎት ስንል በውስጡ ምስጋና ምልጃና ልመና እንዲሁም ምስክርነትን (ጸሎተ ሃይማኖት እንዲል)የሚያጠቃልል ነው።
ጾምና ጸሎት እነዚህ ሁለቱ በክርስትናችን አዳም ሳይበድል ሔዋንም ሳትሳሳት በገነት የነበሩትን የቅድስና ሕይወት የሚያስታወስ፤
በዚህ ባለንበት የዓለም ኑሮ ሥጋችንን ለነፍሳችን ነፍሳችንን ለእግዚአብሔር የምናስገዛበትና ጸጋ ክብር በረከት የምናገኝበት ተግባር
የማይሞቱ የማይበሉ ምስጋናና ስግደት የማያቋርጡ መላእክትን የምንመስልበት የትንሣኤ ልጆች ልጆች ስለሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው እንዳለ ጌታ በወንጌል ከሞት በኋላ ያለው የማይበላበትን የማይጣበትን የማይሞትበትን ምስጋና የማይቋረጥበትን የመንግሥተ ሰማይ ሕይወትን የምንለማመድበትና የምንሰብከት ሕይወት ነው።
በአጠቃላይ ጾምና ጸሎት ራሳችን ዝቅ አድርገን ከችግሮች በላይ የሕይወታችን መሪ ለሆነው አምላካችን የምናቀርበው ምስጋና ምስክርነት ልመናና ምልጅ እንዲሁም ለሕይወታችን መቃናት ከፍቅሩ የተነሳ የምንተወውንና መታዘዛችንን የምናረጋግጥበትን የክርስትና ሐሳብ የያዘ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ በሚጾሙ አጽዋማት በዓመት ከ365 ቀናት ውስጥ ከ180 በላይ ቀናት በጾም የሚበዛውን ቀን ለነፍስ ክብር ለሥጋ ሕይወት ታውለዋለች።
ከ7ቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከነሐሴ 1_16 ቀን ድረስ ከሕጻን እስከ አዋቂ በተለያዩ ሥርዐቶች ደምቆ የሚጸመው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም አንዱና ዋነኛው ነው።
ጾሙ መሠረት የሚያደርገው ቅዱሳን ሐዋርያት ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች የሆነች ድንግል፣ ተዋሕዶ የተጸመባት ማኅጸን፣ ነጻነታችን የተጻፈባት ሰሌዳ፣ የእግዚአብሔር ሀገሩ የቅዱሳን ከተማ፣ ከእሷ ውጭ ፍጡር የማይጠራበትን የተግባር ስም የተገባት የወላዲተ አምላክ እመ ብርሃን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ለማየት ይታደሉ ዘንዱ የጾሙት ጾም ነው።
ምክንያቱም የአዳም ተስፋ የተባለች የፍጥረታት ናፍቆት፤ እግዚአብሔር ዓለም ላይ ያገኛት የሚወደድ መዐዛ ያላት ብላቴና፤ ቅዱስ ወንጌሉ የተነበባት ፊደል፣ መከራን የምታውቅ መከራ አቅላይ ጭንቅት የምታውቅ ርኅሩኅ እናት ስለሆነች እመቤታችን በእጅጉ ትናፈቃለች።
ቅዱሳን ሐዋርያት ለእመቤታችን ያላቸውን ፍቅርና ክብሯን ለማየት ያደረጉት ምኞት ብቻ አልነበረም ይልቁንም በሁለት ሱባኤ በጾም በጸሎት ተወስነው ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ለማየት በቁ ተደረገላቸውም።
ለዚህ ነው የቤተ ክርስቲያን የአደባባይ ጌጧ የውስጥ ውበቷ ቅዱስ ያሬድም በድጓው “ተመየጡ ኀቤየ ወተሐይዉ በጾም ወበጸሎት ወበርትዕት ሃይማኖት” (በጾም በጸሎት በእውነተኛ ሃይማኖትም ወደ እኔ ተመለሱ ትድናላችሁም)
ሁላችን በሕይወታችን፣በሀገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በየሥራ መስካችን ናፍቆት የሆኑን እንዲደረጉልን የምጓጓቸው ብዙ የምንወጣበት የምንወርድበት፣ ሰዎቸን የምናማክርበት ተቋም የምንገነባበት አልሆን ሲል ሌላ አማራጭ የምንፈልግባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው።
ለዚህ ሁሉ ሁነኛ መፍትሔው ጥብርያዶስ በሆነው የሕይወት ባሕራችን ጌታ እየተራመደ ይመጣ ዘንድ፣ በበርካታ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች መነሻነት በተዘጋው ቤታችን ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እንዲለን፣ ብዙ የደከምንባቸው ፊታችንን አንዴ በላብ ሌላ ጊዜ በእንባ ያጠብንባቸው አጋጣሚዎችን አጽናቹ አምላክ ልባችን እንዲደግፍ ሥራችንንም እንዲባርክ በእውነተኛ ንስሐ በጾም በጸሎት ወደ እርሱ በመመለሰ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን በረከት ልንሳተፈና ከናፍቆታችን ልንገናኝ ይገባናል።
ለዚህም በጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሌሊቱ የሰዓታት ጸሎት፣ በጥዋቱ ስብሐተ ነግህና ቅዱስ ኤፍርም የደረሰው ውዳሴ ማርያምና የአባ ሕርያቆስ የደረሰው ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፤ የቅዳሴ መዳረሻ ትምህርት ወንጌል፣ የሰማያዊው ሠርግ ጸሎተ ቅዳሴ ከዚም 11 ሰዓት የሠርክ የምሕላ ጸሎት እና ቅዱስ ወንጌል የሚሰጥበት አገልግሎት እንደናፈቀን የሚጠናቀን የሁለት ሱባኤ አገልግሎሎት ከራሳችን ጋር እንድንታረቅ ከሕይወት ናፍቆታችን ጋር እንድነገናኝና ጸጋና ሰላም እንድናገኝ ትልቅ መደላድል ነው።
በመሆኑም በእንዲህ ባለያለ ሥርዐት አገልግሎቱ የሚቀርብበት ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ካህናቱና ምእመናኑን በኅብረት ለእግዚአብሔር መገዛታችን የምናሳይበትና ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም በረከት ጸጋ የምናገኝበት በመሆኑ ሥርዐተ አበውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ከእንኳን አደረሳችሁ ጋር የምናስተላላፈው መልእክታችን ነው።
በዚህም በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት
1. በሊቃውንቱ በኩል ስብሐተ ነግህ፣ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ እና ከቅዳሴ በኋላ ዕጣነ ሞገር በአግባቡ
እንዲፈጸም፣
2. በካህናቱ በኩል ሌሊት ሰዓታት ቀን ቅዳሴው የቤተ መቅደሱ ሥርዓት በጥንቃቄ እንዲከናወን፣
3. የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ከሰኞ እስከ አርብ የቅዳሴ መግቢያ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሲሆን በዕለተ ሰንበት ቅዳሜ እና እሑድ በተለመደው ሰዓት እንዲሆን፣
4. ሰባክያነ ወንጌል ለሕዝበ ክርስቲያኑ ተገቢ የሆነ የክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል በማስተላለፍ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሰላምን የሚሰጥ የሚያጽናና እና ወቅቱን የዋጀ ትምህርት እንዲሰጥ፣
5. በደብሩ ወይም በገዳሙ የሚገኙ የቢሮ ሠራተኞች እንደደረጃቸው እንዲያገለግሉና ጾሙን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያስቀድሱ፣
6. ማንኛውም አገልጋይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዳሴ ጊዜና በሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎት ሰዓት ሞባይል እንዳይጠቀም፤
ስለዚህ ከላይ የተዘረዘሩቱን መመሪያዎች በተግባር ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች ጀምሮ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እንዲሁም የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች እና ሰበካ ጉባኤያት ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉ እናሳስባለን።
እንኳን ለጾመ ፍልሰታ ለማሮያም በጤና አደረሳችሁ!
መልስ ያለው የጾም ጸሎት ሱባኤ ያድርግልን!
“ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና
እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን
አእምሮውን ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን።
አባ ሕርያቆስ
የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት
ሊቀ ጳጳስ
የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
የቦርድ ሰብሳቢ
ሐምሌ ፴/፳፻፲፯ ዓ/ም
አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ