ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከልን ጎበኙ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከልን ጎበኙ።
ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና ሰብአዊ መተሳሰብን እንዲሁም ኅብረታዊ አንድነት መሠረት ያደረገ ነው የተባለው ሰንሻይን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከልን ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቦታው ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል።
ከብፁዕነታቸ ጋር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ማእምራን ዘበነ ለማ (ፕሮፌሰር) በሰሜን አሜሪካ በሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ የቂርቆስ ልደታ አዲስ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሌሎች የሀገረ ስብከቱና የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ተገኝዋል።
በጉብኝቱ ወቅት በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንንና አረጋውያትን የጠየቁ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ለአረጋውያን የሚሰጠውን አገልግሎት በተለይም የጤና አገልግሎት መስጫ ክሊኒክ፣ የአረጋውያንን መኖሪያ ሁኔታና የዕደ ጥበብ ሥራ መሥሪያ ፣ የልብስ ማጠቢያና የምግብ ማብሰያና የመመገቢያ ቦታዎችን ቃኝተዋል።
በአዲስ አበባ ሰሚት ተብሎ በሚጠራው ሠፈር አካባቢ የሚገኘው ሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከል በከተማ አስተዳዳሩ መልካም ፈቃድ የ30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አዘጋጅነትና በሰንሻይን ኮንስትራክሽን አማካኝነት ከ635 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የግንባታ ወጪ እንደተገነባም ተገልጿል።
የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በቦታው ተገኝተው ማእከሉን ስለጎበኙ አመስግነው ከአረጋውያንና ከአረጋውያት ጋር የሚደረገው የመስቀል በዓል የጋራ ምሳ መርሐ ግብር በየዓመቱ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ፍፁም ደስታ እንደሚሰማቸውና የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ዋነኛ ዓላማ አድርጎ ከሚሠራቸው ትውልዳዊ ሥራዎች መካከል ከትምህርት ቀጥሎ ይህ የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ተጠቃሽ መሆኑ አስረድተዋል።
በማእከሉ ካሉት አረጋውያን መካከል ሁሉ ሦስት አረጋውያን ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን ለአቶ ሳሙኤል ታፈሰና ቤተሰቦቻቻው ያላቸውን ክብር ገልጸው ብፁዕነታቸው እዚህ ድረስ መጥተው ስለጎበኙን እጅግ ተደስተናል እናመሰግናለን ብለዋል።
ሊቀ ማእምራን ዘበነ ለማ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት የክብር ዶክተር ሳሙኤል ታፈሰ የሕይወት ሩጫቸውን ዓለም ከናቃቸው ጊዜ ከተጣላቸው ዘመድ ከተዋቸው ወገኖች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሩጫውን ያሸነፉ በጎ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ያዩት የአረጋውያን መጦሪያ ከሰሙትና ከጠበቁት በላይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የክብር ዶክተር ሳሙኤል ታፈሰ ባይኖር ኖሮ መንገድ ላይ የሚወድቁና ፀሐይና ዝናብ የሚፈራረቅባቸው ብዙ ወገኖች ይሆኑ እንደነበር አስታውሰው።
አክለውም ለመልካም ተግባራቸው የክቡር ዶክተር ሳሙኤልን ከነቤተሰቦቻቸው አመስግነዋል እግዚአብሔር በመልካሙ በረከት ይባርክህ ብለዋል።
ማዕከሉ መስከረም 3/2016 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተመረቀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቁጥራቸው 205 የሚሆኑ አረጋውያን ያሉ ሲሆን ድርጅቱ እስከ 700 አረጋውያን የማስተናገድ ዕቅድ እንዳለው ተገልጿል።