ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋምን ጎበኙ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋምን ኀዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ጎብኝተዋል።
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ደረጃ ያደረሷት አባቶቻችን ዝም ብለው ሳይሆን አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው፣በእሳት ተቃጥለው በብዙ መከራና ውጣ ውረድ መሆኑን በመረዳት እኛ ልጆቻቸው ደግም ከአባቶቻችን የተረከብነውን አደራ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እንደ ሀገረ ስብከታቸው የታቀዱ ሰፋፊ ሥራዎች በመኖራቸው ደቀመዛሙርት በካህናት ማሰልጠኛው ቆይታቸው ዋጋ በመክፈል ቀን ማታ ሳይሉ ጠንክረው መሰረታዊ እውቀት በመጨበጥ፣ የገጠሪቷን ቤተክርስቲያን ሄደው እንዲያገለግሉ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ አባታዊ ምክራቸውን ከአደራ ጋር ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸዉ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ሐዋርያት ፲፪ ሆነው ዓለምን በወንጌል ጨውነት ካጣፈጡ እናንተ ደግሞ በቁጥር ፳፮ ናችሁ ቁርጠኝነት ካለ ለሀገረ ስብከታችን ትልቅ ተስፋዎች ናችሁና በርቱ በማለት ደቀ መዛሙርቱ በትምህርት አቀባበላቸውና ፍላጎት ላይ ባላቸው ቁርጠኝነት መደሰታቸዉን ገልጸው፤ ሰልጣኞች በማሰልጠኛዉ በሚቆዩበት ወቅት የሚያስፈልጋቸዉ ነገሮች እንዲሟላላቸዉ ለማሰልጠኛዉ ኃላፊዎች አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸዉ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛን ለማሳደግ በካህናት ማሠልጠኛው ግቢ ውስጥ ለሚሠራው “የካህናት ማሠልጠኛና አብነት ት/ቤት” ሕንጻ ግንባታ የተዘጋጀውን ሳይት ጎብኝተው ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው ሥራው እንዲጀመር መመሪያ ሰጥተዋል::
