ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ከሀገረ ስብከቱና ከክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሐላፊዎችና ሠራተኞች ጋር ትውውቅና ውይይት አካሄዱ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ከሀገረ ስብከቱና ከክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሐላፊዎችና ሠራተኞች ጋር ትውውቅና ውይይት አካሔዱ ።
ግንቦት 15/2017 ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው መመደባቸው የሚታወስ ነው።
በመሆኑም ብፁዕነታቸው በዛሬው ከሀገረ ስብከቱና ከክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሐላፊዎችና ሠራተኞች ጋር ትውውቅና ውይይት ያደረጉ ሲሆን ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
ሥራ አስኪያጁ በንግግራቸው የሀገረ ስብከቱ ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተና ያለውን ተስፋ እንዲሁም ወደ ፊት የሚጠበቀውን ሥራ ገለጻ አድርገዋል።
ቀጥሎም የሀገረ ስብከት ሠራተኞች በመወከል መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ተክለ ማርያም አምኜ የትምህርትና ማሰልጠኛ ዋና ክፍል ሐላፊ፤ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችን በመወከል ደግሞ መጋቤ ሃይማኖት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ የአዲስ ከተማ፣ ልደታና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና መልአከ ገነት ልሳነወርቅ ተስፋ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የእንኳን ደህና መጡ መልእክትና በብፁዕነታቸውን እንዲተገብር የሚጠበቀውን የሀገረ ስብከቱን እውነተኛ ናፍቆት የሆነው የመልካም አስተዳደር ሥራን ጠቁመው፤ አያይዘውም ውጤት ያለው የአባትነት ጊዜ እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ፣ የሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ስለተደረገላቸው ክብረ አበውን የጠበቀ አቀባበል ምስጋና አቆርበዋል።
አያይዘውም በተልእኮቻቻን ሁሉ ለጋራ እውነትና ሕይወት ለቤተ ክርስቲያን ክብር በመሸነፍ ሐላፊነትን መወጣት ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው የሀገረ ስብከቱን ብሎም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ክብር ማስጠበቅ ይኖርብናል ያሉ ሲሆን ከሀገረ ስብከቱ እስከ ታችኛው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ድረስ ተናቦና ተግባብቶ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሥሩ 260 በላይ አብያተ ክርስቲያናት፣ 464 በሀገረ ስብከቱና ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት እንዲሁም በመንበረ ፓትርያርክ መምሪያዎችና ድርጅቶች የሚሠሩ ሠራተኞች፣ ከ30,000 በላይ የአጥቢያ ሠራተኞችን የያዘ ታላቅና ጥንታዊ ሀገረ ስብከት ነው።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ