ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት ከ፪፻ አገልጋዮች በላይ ክህነት ሲሰጡ የአንድ ቤተሰብ አባላት #አባታቸው የቅስና ሁለት ልጆቹ የዲቁና ማዕረግ ተቀበሉ

መስከረም ፬/፳፻፲፰ ዓ/ም
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለተ ሰንበት በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ከ፪፻ በላይ ለሚሆኑ አገልጋዮች ማዕረገ ክህነት ሰጡ።
ከተቀበሉት አገልጋዮች መካከልም የአንድ ቤተሰብ አባላት #አባታቸው_ቅስና_ሁለት_ልጆቹ_ዲቁና_ማዕረግ_ተሰጥቷቸዋል።
በቦሌ መከብፁዕነታቸው ጋር በመሆን ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ማዕረገ ክህነት የሰጡ ሲሆን መጋቤ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ልዩ ፀሐፊ፣ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለ ማርያም በፈቃዱ የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ የካቴድራሉ የአገልግሎት መሪዎች ተገኝተዋል።
ማዕረገ ክህነት የተቀበሉት አገልጋዮች ከተለያዩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ መምህራን እየተማሩ የቆዩ መሆኑቸው የተገለጸ ሲሆን ማዕረገ ክህነት ሊቀበሉ ሲመጡም በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ መመሪያ ሰጭነት በሀገረ ስብከት ደረጃ ተፈትነው ያለፉ ናቸውም ተብሏል።
በመሆኑም በዛሬው ዕለተ ሰንበት 13 ዲያቆናት የቅስና እንዲሁም 200 ደቀ መዛሙርት የዲቁና ማዕረግ መቀበላቸው ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ክህነት ለተቀበሉ አገልጋዮች ቡራኬና አባታዊ ትምህርት ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው ስለክህነት ክቡርነትና የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥንቁቅነት ያስታወሱ ሲሆን ዋጋ ላለው ሰማያዊ አገልግሎት ራሳቸውን በማዘጋጀት ማገልገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በበኩላቸው የሁሉም መጀመሪያም መጨረሻም እግዚአብሔርን በመፍራትና በቀና ልብ ሆኖ ማገለገል እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡ ሲሆን የተቀበሉትን የክህነት ክብርና ሕይወት በሥርዓትና በአግባብ እየተመላለሱ መጠበቅ እንደሚገባቸውም መክረዋል።
ብፁዕነታቸው አያያዘውም በዛሬው ዕለት የአንድ ቤተሰብ አባላት አባታቸው ቅስና ሁለት ልጆቹ ደግሞ የዲቁና ማዕረግ የተቀበሉ ሲሆን ይህም ቅዱሱን የክህነት አገልግሎት በቤተሰብ የማስቀጠል ትልቅ አገልግሎት መሆኑ ገልጸዋል።