ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በአቃቂ ደብረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው በደብሩ የተሠሩት የልማት ሥራዎች አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ባረኩ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአቃቂ ደብረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው በደብሩ የተሠሩት የልማት ሥራዎች አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ባረኩ።
ከብፁዕነቻው ጋር የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች አብረው ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸው የመጀመሪያውን ጉብኝት በአቃቂ ደብረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ያደረጉ ሲሆን ደብሩ ጋ ሲደርሱ የአባቶችን ክብር በጠበቀ መልኩ በክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣በደብሩ የአስተዳደር ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች፣በደብሩ ማኅበረ ካህናት፣በደብሩ ሰ/ት/ቤት አባላት፣ በመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣በአከባቢው ወጣቶችና ምእመናን የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ልሳነወርቅ ተስፋ ለብፁዕነታቸው፣ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና ለልዑካኑ በቅድምያ “የእንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክት አስተላልፈዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን ፋንታነው እርቅይሁን አስቀድመው በደብሩ ያለውን የወንጌልና መንፈሳዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ በተጨማሪም በደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የተሠሩትን ቤተልሔም፣ የእንግዳ ማረፊያና ራስ አገዝ የልማት ሥራዎች በተመለከተ ለብፁዕነታቸው፣ለዋና ስራ አስኪያጁና ለልዑካኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው በደብሩ የተሠሩትን የልማት ሥራዎች አድንቀው ቤተክርስቲያን ምእመናንን በመንፈሳዊ አገልግሎት ከማገልገል ባሻገር የተለያዩ ድጋፎች መስጠት ትችል ዘንድ እንዲህ ያሉ ራስ አገዝ የልማት ሥራዎች በእጅጉ ያስፈልጋሉ ብለዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላትና የአስተዳደር ጽ/ቤት ሠራተኞች ምእመናንንና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ላከናወኑት ተግባር ብፁዕታነታቸው አመስግነው ከዚህ በላይ እንዲሠሩም መክረዋል።
በደብሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ አስቀድመው በተዘጋጁ ጉድጓዶች የችግኝ ተከላ መርሐግብርም ተካሂዷል።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ