ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በመገንባት ላይ ያለውን የፍል ውሃ መድኃኔዓለም ሕንፃ ቤተክርስቲያን ጎበኙ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ፣ የሐድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነትና የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰባኪያን ኅብረት ሰብሰቢና ሥራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት በልዩ ሁኔታ በመገንባት ላይ ያለውን የአያት የፍል ውሃ መድኃኔዓለም (አያት ጸበል) ሕንፃ ቤተክርስቲያን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ብፁዕነታቸው ሕንፃ ቤተክርያኑን ከታች እስከላይ ድረስ የጎበኙ ሲሆን ወደ ዐውደ ምሕረቱ ተመልሰውም ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሲሰጡ ብፁዕነታቸው የአካባቢውን ምእመናን ከዚህ በፊት የሚያውቁትና ዛሬ ደግሞ በሌላ ገጽታ የተዋወቁት መሆኑን ገልጸው እግዚአብሔር የሥራ ዘመናቸው እንዲያቀና የምዕናኑ በጸሎት መትጋት ወሳኝ ሚና እንዳለው አሳስበዋል።
አክለውም በክቡር የደብሩ አስተዳዳሪ አስተባባሪነት፣ በሚለከታቸው የቤተክርስቲያኗ ኀላፊዎች ድንቅ ተሳትፎ እና በምዕመናኑ የማይዝል ትከሻ እየተሠራ ያለው ሕንጻ ቤተክርስቲያን የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ ለፍጻሜ እንዲተጉ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው መመሪያ ከመስጠት ባሻገር ምዕመናን በደሙ ፈሳሽነት የዳንን አማኞች መሆናችንን የሚያጠይቅና መዳናችን የሚረጋገጠው በቅድስት ቤተክርስቲያን እስካለን ድረስ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።
ይህንኑ ትምህርት ሲያጎላምሱ የወፍ መኖሪያ በዛፍ ላይ የዓሳ መኖሪያው በውሃ ውስጥ ሆኖ ሳለ ቦታ ብንቀያይራቸው ግን መኖር እንደማይችሉ ሁሉ ክርስቲያኖችም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ መሆን ከውሃ እንደወጣ ዓሳ ወይም ወደ ጥልቁ እንደገባች ወፍ ማለት ነው በማለት ክርስቲያኖች በቤታቸው ጸንተው እንዲኖሩ የሚያስገነዝብ ትምህርት ሰጥተዋል።
በጉባኤው የተገኙ ምዕመናን በተደረገላቸው መጎብኘት አብዝተው ደስታቸውን በእንባና በእልልታ የገለጹ ሲሆን ክቡር የደብሩ አስተዳዳሪም ዝናብ፣ጭቃና ምሽት ሳይበግርዎ በዚህ ሥፍራ የምንገኝ ልጆችዎን ስለጎበኙን፣ በቃሉ ዘንግነት ቀስቅሰው ስላጽናኑን እያመሰገንን ለወደፊትም ይኸው የአባትነት ጉብኝትዎ እንዳይለን ስል በዚህ አጥቢያ በሚገኙ ምዕመናን ስም እማፀናለሁ በማለት ብፁዕነታቸውን ጠይቀዋል።
በመጨረሻም መርሐግብሩ እስከ ምሽቱ 2:00 ድረስ በዝማሬ እና በወንጌል አገልግሎት ቀጥሎ አምሽቷል።
የዘገባው የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት ድምጸ ተዋሕዶ ነው።