ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስሊቀ ጳጳስ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመመረቂያ ጋውን ጸሎተ ቅዳሴ ላከናወኑት ካህንና የደብሩ አለቃ አስተዳደራዊ ርምጃና ቀኖና ሰጡ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ “በመመረቂያ ጋውን” ጸሎተ ቅዳሴ ላከናወኑት ካህንና የደብሩ አለቃ አስተዳደራዊ ርምጃና ቀኖና ሰጡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድሳት መጻሕፍትን መሠረት፣ ትውፊትን እንደመቀነት ቀኖናን እንደአጥር አድርጋ ሥርዐተ አምልኮን እስካሁን ባለመለወጥ እያከናወነች የምትገኝ ድንቅና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት።
ይሁንንና መነሻቸው የተለያየ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ሥርዐት በመላእክት ምስጋና የምታመሰግንበት ድንቅ አገልግሎት ሳይቀር ሥርዐተ አበውን ወደ ጎን በመተው በማናለብኝነትና ሥጋዊ ደማዊ አመለካከትን #መንፈስ_ቅዱስ በሚመራት ቤተ ክርስቲያን ደባል ማድረግ ከጀመረ ዋል ሰንበት ብሏል።
ለዚህ እንደማሳያ በቅርቡ በጀሞ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውና በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር የቆየው ለብዙዎችም መነጋገሪያና የመሪ ያለህ ጩሆት የተሰማበት ኢቀኖናዊ ድርጊት ለሥርዐተ አበው ቦታ አለመስጠትና ለግል አመለካከት መገዛት ምልክት ስለመሆኑ ብዙዎች እንደማሳያ ያቀርባሉ።
ኢቀኖናዊ ድርጊቱ ሰኔ 29/2017 ዓ/ም በዕለተ ሰንበት የቅዳሴ ማጠናቀቂያ ሥርዐት ላይ የቀደሰው ዲያቆን “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ በእደ ገብሩ ካህን ከመ ይባርከነ/ይባርክሙ የሚለው ለመጨረሻው ማስናበቻ ቡራኬ ዝግጁ ማድረጊያ ጸሎትን ሥርዐተ ቅዳሴው ከሚያዘው ውጪ ኢቀኖናዊ በሆነ አለባበስ “የመመረቂያ ጋውን” በመልበስ ጸሎቱን ያከናወኑ ሲሆን ሀገረ ስብከቱም ይህንን ኢቀኖናዊ ድርጊት በሰነድና አጣሪ ልኡክ በመመደብ ካጠራ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አስተዳዳራዊ ርምጃ ወስደዋል ቀኖናም ሰጥተዋል።
ቀኖናው የተሰጣቸው አገልጋዮች ኢ ቀኖናዊ በሆነ መልኩ (በመመረቂያ ጋውን) በጸሎተ ቅዳሴ የተሳተፉት ካህንና የደብሩ አለቃ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ሳያስጠበቁ በዝምታ በማለፋቸው እንደሆነ ተጠቅሷል።
ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (የሐዋርያት ሥራ ፳፥፳፰) እንደሚለው ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያን በተባለው ልክ የመጠበቅ ሐላፊነት አለባቸው።
ቤተ ክርስቲያን በምትመራባቸው ሌሎች የሥርዐት መጻሕፍት በተለይም በዲዲስቅልያ በፍትሕ መንፈሳዊና በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጠቅሶ ይገኛል።
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፬፡፷፭ እንደተቀመጡ ሊቀ ጵጵስና ሃይማኖትን የመጠበቅና አማኞችን በመንፈሳዊና በሕጋዊ መንገድ የመምራት ሐላፊነት እንዳለበት ይናገራል።
“ሊቀ ጵጵስና ሃይማኖትን ስለመጠበቅ ምእመናን በመንፈሳዊና በሕጋዊ ሥራ ለማስተዳዳር በዚህ ዓለም ስለክርስቶስ ነው” ይላል ።
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፶፬:፫ እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መተደዳሪያ ደንብ አንቀጽ ፲፩፡፫ እንደተደነገገው ሊቀ ጳጳስ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማስጠበቅ ሐላፊነት እንዳለው ይጠቅሳል።
“የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት፤ የሀገር ፍቅርና አንድነት በሰላም ተጠብቆ እንዲኖር እንዲሁም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናቸውን እና ኦርቶዶክሳዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ብርቱ ጥበቃ ያደርጋል”ይላል።
በዚህም ከላይ በተጠቀሱት የሥርዐት መጻሕፍት መነሻነት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የተፈጸመውን ድርጊት አስመልክተው ድርጊቱን ለፈጸሙና በዝምታ ለተባበሩ ሐላፊነታቸውን ላልተወጡ የደብሩ አስተዳዳሪያና የዕለቱ ቀዳሽ ሠራኢ ዲያቆን ቀኖና ሰጥተዋል።
ስለሆነም አንደኛ ቀሲስ ሀብታሙ ቢነጋ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አክብረው ማስከበር ሲገባቸው የቀደሱበትንና የከበረውን ልብሰ ተክህኖ አውልቀው በኮሌጅ የመመረቂያ ጋወን አድንኑ በማለት ለፈጸሙት ስህተት ከ21 ቀን ደመወዝ ቅጣት ጋር ቀኖና እንዲሰጣቸው የተደረገ ሲሆን ከነሐሴ ጀምሮ 1 እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለ3 ሱባኤ (21 ቀናት) በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በቀኖና ተወስነው እንዲቆዩና ቀኖናውን በአግባቡ መፈጸማቸውን የሚገልጽ ማረጋገጫ ከገዳሙ ጽ/ቤት ይዘው ሪፖርት እንዲያደርጉና ደብሩም ቅጣቱን ከደመወዛቸው ተቀናሽ አድርጎ ገቢ እንዲያደርግ፤
ሁለተኛ መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ጎበዜ የደብሩ አስተዳዳሪ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን አክብረው ማስከበር ሲገባቸው የሚያስነቅፍ ሥራ ሢሰራ በቸልተኝነት በመመልከታቸው እንደ መጀመሪያ ጥፋት ተቆጥሮ ቀኖና እንዲሰጣቸው የተደረገ ሲሆን ከነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለ3 ሱባኤ (21 ቀናት) በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በቀኖና ተወስነው እንዲቆዩና ቀኖናውን በአግባቡ መፈጸማቸውን የሚገልጽ ማረጋገጫ ከገዳሙ ጽ/ቤት ይዘው ሪፖርት እንዲያደርጉ በማለት ብፁዕነታቸው ቀኖናውን ሰጥተዋል።
ድርጊቱ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና አኳያ ክህነት የሚያሲዝና ሌላ ተጨማሪ አስተዳደራዊ ርምጃ የሚያስወስድ ቢሆንም የድርጊቱ ፈጻሚና ተባባሪ በመጸጸት ይቅርታ ስለጠየቁና ቤተ ክርስቲያናችንም ይቅርታ ለሚጠይቅ ደጇ ሁልጊዜም የተከፈተ በመሆኑ ቀኖና እና መጠነኛ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።
ቀኖናው የተሰጠው ኢቀኖናዊ ድርጊቱ ከቅዱስ መጽሐፍና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌዎች አንጻር ሲታይም ድርጊቱ የማይፈቀድና ከወዲሁ ሊታረም የሚገባው መሆኑን አያጠራጥርም።
ጸሎተ ቅዳሴ በቤተ ክርስቲያናችን ያሉ የትምህርት ጉባኤያት ሁሉ ብሉያቱ፣ ሐዲሳቱ፣ ሊቃውንቱ፣ድጓው፣ አቋቋሙ፣ ዝማሬው፣ ቅኔውና ንባቡና ትርጓሜው በአንድነት ካህናትና ምእመናን በሰቂለ ሕሊና በአንቃዕድዎ ልቡና በመላእክት የምስጋና መንገድ የሚሰለፉበት ልዩ ሥርዐት ነው::
በዚህ የክርስቶስ ሥጋና ደም ለሁሉም ለኃጢአት ሥርየት ለሃይማኖት ጽንዐት ለሥጋ ቅድስና ለነፍስ ንጽሕና ለዲያብሎስ ድል መንሻና ለመንግስተ ሰማይ መውረሻ እንዲሆን የሚሰጥበት ሰማያዊ ዙፋን ነው::
ታዲያ ይህ የአገልግሎት ምዕራፍ የነፍስ መሻገሪያዋ ሥርዐተ ጸሎት የሚከናወነው ሁሉንም በሥርዓት ያዘጋጀና የፈጠረ እግዚአብሔር እንዳስተማረን ቅዱስ ጳውሎስ እንተናገረው ሁሉም በአግባብና በሥርዐት ይሁን እንዳለው (1ኛ ቆሮ.14:40) ወዲህ ደግሞ ለነገሮች ከተቀመጠላቸው በላይ ያለአግባብ እንዳንዘል ከተጻፈው አትለፍ በሚል ቃል የልክነት ውበት በማስጠንቀቂያ ያሳስበናል፡፡
ስለሆነም ይህ ሥርዐተ ቅዳሴ የሚከናወነው በተለየ ድንቅ በሆነ ትውፊታዊ ሥርዐት ነው፡፡
ሥርዐቱ ከሚከናወነባቸው ንዋያተ ቅድሳት መካከልም ልብሰ ተክህኖ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
የቅዳሴ ልብሰ ተክህኖ በኦሪቱ ሥርዓት የመገናኛ ድንኳንና የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ለነበሩት አባቶቻችን የተሰጠው የሥርዓት ልብስ መሠረት ተደርጎ በሐዲስ ኪዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ድንቅ በሆነና በልዩ የአገልግሎት ልብስ ጸሎቱን ታከናውናለች ::
ልብሰ ተክህኖ ስንል ካባ ላንቃ፣ ሞጣሕት የካህናትና የዲያቆናት ቀሚስ፣ አክሊልና ቆብ፣ መጎናጸፊያና ሌሎችንም ያከተተ ነው።
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 12: 479 ና በሥርዐተ ቅዳሴ ቁ.62 እንደተቀመጠው ቅዳሴ የሚቀደሰው በግል ልብስ ሳይሆን በተለየና በተባረክ በቀለማቸውም ነጫጭ በሆኑ አልባሰት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡
“የሚቀድሱባቸው የቅዳሴ ልብሶች ነጫጭ ይሁኑ ፡ ቀለም ፡ የገቡ ያይደሉ፡፡ (ሥርዐተ ቅዳሴ ቁጥር 62_64)
ከዚህ በተጨማሪም በሀገራችን 1946 ዓ/ም በተካሄደው ሁለተኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የቅዳሴ አልባሳትን በተመለከተ እንዲህ በሚል ውሳኔ አሳልፏል።አ
ስለ ቀሳውስት ልብስ “ቀሳውስት በቅዳሴ ጊዜ የሚለብሱት እጅ ሰፊ ቀሚስና እንደተለመደው ነጭ ካባ ላንቃ እንዲለብሱ በራሳቸውም ላይ በፊትና በኋላ አረንጓዴ መስቀል የተሰራበት ነጭ ቆብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ዲያቆናት ንፍቀ ዲያቆናት በደረቱና በጀርባው አናጉንስጢሳውያን በቅዳሴ ጊዜ የሚለብሱት እጀ ሰፊ ቀሚስ ትዕምርተ መስቀል ያለው እንዲሆንና በግራና በቀኝ ትከሻቸው በወገብ የሚተላለፍ መታጠቂያ ያለው (በድረሺን እንዲሆን) ይገባል ። በእራሳቸውም ላይ በጫፉ መስቀል ያለበት ከጨርቅ የተሠራ አክሊል ሊያደርጉ ይገባል”በማለት ይገልጻል።
(ሁለተኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ገባኤ ውሳኔ ጥቅምት 1946 ዓ/ም)
በአጠቃላይ በጸሎተ ቅዳሴ የሚለበሱት አልባሳት ሰፊ ትርጉም፣ ምሳሌና ምሥጢር ያላቸው ሲሆኑ ከነዚህም
በገነት አዳም የለበሰው የጸጋ ልብስ፣ በመገናኛው ድንኳን መቅደስ ሲገባ የሚለበስ፣ ልጆቹ የሚካኑበትና የሚቀቡበት የተቀሰው የአሮን ልብስ፤
በደብረ ሲና ከእግዚአብሔር ለመባረክ እስራኤላውያን ለብሰውት የቀረቡት ንጹሕ መባረኪያ ልብስ፣
በምስጋና በረከት የምንቀደስበት ያዕቆብ የተመረቀበት መልካሙ ልብስ፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር የታየበት የብርሃን ልብስ፣
ቀራንዮ ዐደባባይ በሚገኘው ቤተ መቅደስ በልጁ ሠርግ የምንታደምበት ልብሳችን፤
ትምህርተ ተዋሕዶን የምንሰብክበት አብነታችን፣
ከቅዱሳን መልእክት ጋር በትንሣኤው ምስክርነት የምንተባበርበት መልካችን
የመንግሥተ ሰማይ የአንድነት ምስጋና ልብሳችን ምስጢራዊ ማስረጃችንንና ማስተማሪያ ምሳሌያችን ስለመሆኑ ሊቃውንት ያስተምራሉ መጻሕፍት ይናገራሉ።
የቅዳሴ ልብሰ ተክህኖ ጸሎተ ቅዳሴው ሳይጠናቀቅ ማውለቅም ሆነ መቀየር አይቻለም። ሳፈጸመም አቋርጦ መውጣትም ሥርዐት አይፈቅድም።
“ልብሱን ፈጽሞ ከመልበሱም በፊት የሚያገለግለው ዲያቆን ምናልባት እንዳለ ይመልከት ። የሚያገለግልና ለተልእኮ የሚራዳው ዲያቆን ባይገኝ ካህን ከለበሰ በኋላ ልብሱን ያወጣ ዘንድ አይገባውምና ።
(ሥርዐተ ቅዳሴ ቁጥር 64)
ለዚህ ሥርዐት የቀሲስ አባ ብንያሚ ሕይወት ሁነኛ አስረጅ ነው።
ሐምሌ 1 ቀን ዕረፍቱን የምናከብረው መስተጋድል ቅዱስ ቀሲስ ብንያሚ የአባቱ የዕረፍት ቀን በቀረበ ጊዜ በዚያን ሰዓት ሥርዐተ ቅዳሴ ያከናውን ዘንድ የቅዳሴ ልብስ ለብሶ ቤተ መቅደስ ነበረ። መልእክተኞች ወደ እርሱ መጥተው “አባቱ ለመሞት እንደተቃረበና እርሱንም እንደሚፈልግ ነገሩት”።
ቀሲስ ብንያሚም የቅዳሴ ሥርዐት ሳልፈጽም ልብሰ ተክህኖውን አላውልቅም ፤ አባቴን በሕይወት እንዳየው እግዚአብሔር ከፈቀደ ይቆይልኛል ካልሆነም የእግዊአብሔር ፈቃድ ይሁን አለ።
አባቱም ሁለት ሦስት ጊዜ እንዲመጣ መልእክት ላከ የአባ ብንያሚን ግን ሥርዓተ ቅዳሴውን ከፈጸመ በኋላ ልብሰ ተክህኖውን አውልቆ ወደ አባቶ ሄደ ሙቶም አገኘው።
እንደ አባ ብንያሚ መስቀሉን የሚሸከም፣ በምስጋናው የሚተባበርና በአገልግሎቱ የሚጸና አገልጋይ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም”(ማቴ10:37) ለሚለው ሕያው ቃል ራሱን አሳልፎ የሰጠ ነው።
ክርስትና መኖር ሆነ አለመኖር ለክርስቶስ መሆን እንዳለበት ቅዱስ ጳውሎስ በቃለም በሕየወት መስክራል።
ጸሎተ ቅዳሴ እንዲህ ባለ መንገድ የሚከበር ሕይወትና የሚጠበቅ ሥርዐት መሆኑን የቅዱሳት መጻሕፍትና የቅዱሳን አባቶቻችን ሕይወት ያስተምራል።