ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ የ2017 ዓ/ም የአእላፋት ዝማሬ የጥናት መርሐ ግብርን አስጀመሩ
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ2017 ዓ/ም የአእላፋት ዝማሬ የጥናት መርሐ ግብርን አስጀመሩ።
የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያው ጀንደረባው ትውልድ የሚዘጋጀው የእላፋት ዝማሬ በ2016 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን በርካታ ኦርቶዶክሳውያን በምስጋናው ተባብረዋል።
የዝማሬ መርሐ ግብሩ በዚህ ዓመት የሚቀጥል ሲሆን ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተዋሕዶ ሚዲያ ማእከል የበላይ ጠበቂ ቡራኬ የአእላፋት ዝማሬ ዝግጅት መጀመሩን አብሥረዋል ።
ብፁዕነታቸው የጌታ ልደት እኛም የመዳናችን መንገድ፣ መመለሳችን ዋስት፣ የመክበራችን እውነትነት ማረጋገጫና እግዚአብሔር ሰውን የወደደበትን ፍጹም ፍቅር የተረዳንበት ነውና በበረት ለተወለደው ጌታ እረኞችና መላእክት በአንድነት እንዳመሰገኑት እኛም ልናመሰግነው ልንገዛለት ይገባናል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ይህንን መነሻ አድርጎ የሚከናወነው #የአእላፋት ዝማሬ የምስጋና ማዕድ ባለፈው ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተገኙበት ድንቅ የምስጋና መርሐ ግብር በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ዐውደ ምሕረት መከናወኑን አስታውሰዋል።
ብፁዕነታቸው በባለፈው #የአእላፋት ዝማሬ የምስጋና መርሐ ግብር
በርካታ ሰዎች የተባረኩበት፣ እግዚአብሔር ከማይከበርበት ሕይወት ያመለጡበትና ቤተ ክርስቲያንም የወንጌል መረቧን ያሰፋችበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ስለሆነም ይላሉ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ በዚህ ዓመት የአእላፋት ዝማሬ በጌታቸውን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ዋዜማ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ/ም በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ዐውደ ምሕረት እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል።
ለዚህም የዝማሬ ጥናት ቅድመ ዝግጅት የአእላፋት መላእክት ክበረ በዓል በሚከበርበት ቀን ከትናንት ኅዳር 13/2017 ዓ/ም ጀምሮ መጀመሩን ብፁዕነታቸው ያበሠሩ ሲሆን ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ እንዲሳተፍ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።