ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲሁም የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ እና የመስቀል በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ በተገኙበት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ከከተማው አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት እና በከተማው አስተዳደር በሚደረገው ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል መስቀል ዓደባባይን ጨምሮ በ 2375 አድባራትና በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ላይ የሚከበር መሆኑ በመጥቀስ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በደመቀና ባማረ መልኩ እንዲከበር፤ የከተማው አስተዳደር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ አባቶች እና የኮሚቴው አባላት እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የበዓሉ ዋና ባለቤትና በዓሉን የምትመራው፣ የምታስተባብረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብትሆንም፤ የመስቀል ደመራ በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በአደባባይ የሚያከብረው የአገር ሀብት፣ የከተማችን ድምቀት እንዲሁም የቱሪዝም መስህብ ነው ብለዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበር፤ እንዲሁም አብሮትን በሚያጠናክር መልኩ እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ለሌሎችም የአደባባይ ክብረ በዓላት የሚያደርገውን ድጋፍ የከተማው አስተዳደር እያደረገ ይገኛልም ብለዋል ከንቲባዋ።