ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ልደትን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የ2011 ዓ/ ም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትን አስመልክቶ በርካታ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳትና የሚድያ አካላት በተገኙበት በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ። ጋዜጣዊ መግለጫውም “ሰላምን ሻት ተከተላትም” በሚል የመነሻ ሐሳብ የሰላም ዋጋ ምን ያክል ውድ እንደ ሆነና ሰላም ካልተጠበቀ በቀር ሊወሰድ የሚችል መለኮታዊ ስጦታ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዝህም ጋር ተያይዞ ወቅታዊውን የሀገራችን የሰላም ችግርና የህዝብ እንግልት ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት እንደምትመለከተውና ስለ ሰላምም አብዝታ እንደምትጸልይም ተናግረዋል። የተሰጠውን ሙሉ ጋዜጣዊ  መግለጫ  ከታች እንደሚከተለው ቀርቧል።

መልካም በዓለ ልደት ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞታችን ነው።

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ወሀቤ ሰላም የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመት ምሕረት የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!

“ኅሥሣ ለሰላም ወዴግና፤ ሰላምን ሻት ተከተላትም

ቅዱስ መጽሐፍ ደጋግሞ እንደሚነግረን እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ጸጋዎች አንዱ የሰላም ጸጋ ነው፤ የሰላም ጸጋ ሰው ሲፈጠር አብሮ የተፈጠረ አምላካዊ ሀብት ቢሆንም በአግባቡ ካልተያዘ በሰዎች ድርጊት ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፤ እኛም በተጨባጭ የምናየው ሐቅ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታትን በፈጠረ ጊዜ ሁሉም በሰላም በፍቅርና በአንድነት ተሳስረው እንዲኖሩ ፍጹም ሰላሙን አድሎአል፤ የሰላም አለቃቸው ደግሞ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረው ሰው ነበረ፤ ይሁን እንጂ ፍጥረታትን አንድ አድርጎ በሰላም እንዲያስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠው ሰው የበላይ መሪው እግዚአብሔር ባስቀመጠለት መርሕ መመራት ባለመቻሉ ሰላሙ ተነጠቀ፤

ከዚህ አንጻር ሰላም በሰው መታዘዝ ምክንያት በፍጡራን ጸንቶ የሚኖር፣ በአንጻሩ ደግሞ ሰው ለእግዚአብሔር  ባልታዘዘበት ጊዜ የሚወሰድ ስጦታ እንደሆነ ታወቀ፤ በመሆኑም የሰው ሰላም ሲደፈርስ የሌሎች ፍጥረታትም አብሮ ደፈረሰ፡፡

 ብርሃን ከሌለ ጨለማ እንደሚነግሥ ሁሉ ሰላም ከሌለም ጠብና ፍጅት ይነግሣልና የሰው ሰላም ሲወሰድ ፍጥረታት በሙሉ መለያየትን መጣላትን እርስ በርስ መፋጀትን ገንዘብ አደረጉ፤ በዚህም ምክንያት ሕይወት በጨለማ ተዋጠች፤ ኑሮም መራራ ሆነች፤ ሰላም ድሮም የተሰጠች ኋላም የተወሰደች በእግዚአብሔር መለኮታዊ ውሳኔ ነበርና ለፍጥረቱ አዛኝ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ እንደገና ሰላምን ለሰው ልጆች ለማደል ወሰነ፤ ሰላሙንም የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው በመሆን ገለፀው፤ እግዚአብሔር ሰውን የታረቀው ለመሆኑ ዋናው ማረጋገጫ የሰውን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ፣ ባሕርየ ሰብእን የራሱ ባሕርይ አድርጎ መወለዱ ነው፤

 ዘላለማዊው እግዚአብሔር ወልድ በተዋሕዶተ ትስብእት ሰው ሲሆን፣ ሰውም በተዋሕዶተ ቃል ምክንያት አምላክ ሆኖአል፤ በዚህ ምሥጢረ ሥጋዌ ባሕርየ ሰብእ ወይም የሰው ባሕርይ በተዋሕዶተ ቃል የባሕርይ አምላክ ሆኖ እንደገና የፍጥረታት ሁሉ ገዢ ለመሆን በመብቃቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ አስተማማኝና የማይናወጥ ሰላም ማግኘቱን እንገነዘባለን፤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰማያውያን የሆኑ ሠራዊተ መላእክት “ክብር በአርአያም ለእግዚአብሔር ይሁን” በማለት እግዚአብሔርን ያመሰገኑበት ምክንያት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በተዋሕዶተ ቃል የተገነባ፣ ፈጽሞ የማይፈርስ፣ የማይደፈርስና የማይናወጥ ሰላምን አጎናጽፎት ስላዩ ነው፡፡

በመሆኑም ከልደተ ክርስቶስ ወዲህ ያለው ዘመን እግዚአብሔር ሰውን የታረቀበትና ሰላምን ያጎናጸፈበት ብቻ ሳይሆን ባሕርየ ሰብእን ከመለኮቱ ጋር አዋሕዶ በመንበሩ ላይ በክብረ አምላክነት ደረጃ ያስቀመጠበት ግሩም ዘመን ነው፤ ከዚህ በኋላ ሰው በመንበረ ፀባዖት ላይ በነገሠው አካሉና ባሕርዩ እየተሳበ በሱታፌ አምላክነት ከብሮ ይኖራል እንጂ እንደገና ሰላምን አጥቶ መንፈሳዊ ሕይወቱ የሚናጋበት ሁኔታ የለም፤ እሱ በተዋሕዶተ አምላክ ወሰብእ ጊዜ አብቅቶአል፤ ለዚህም ነው ከልደተ ክርስቶስ ወዲህ ያለው ዘመን “ዓመተ ምሕረት” ተብሎ የተሰየመው፤ ምክንያቱም ምሕረትና ሰላም ለሰው ልጅ በአስተማማኝ ሁኔታ ተሰጥቶአልና ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የሰላም እጦት በተዋሕዶተ ቃል ወሰብእ ተወግዶ በልደቱ ዕለት ፍጹም ሰላም የተበሰረ ቢሆንም በሰውና በሰው መካከል ያለው ሰላም ግን አሁንም እክል እያጋጠመው እንደሆነ የማይካድ ነው፤ ይህ ሁኔታ ከዳግም ምጽአት በኋላ እንደሚያከትም ቢታወቅም እስከዚያው ድረስ በዚህ ዓለም ክፉ መንፈስ ተዋናይነት ፈተናው እንዳልተቋረጠ እያየን ነው፤ እርግጥ ነው እኛ ሰዎች በቃለ ቅዱስ ወንጌል በመመራትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታገዝ ክፉውን መንፈስ ማሸነፍ እንደምንችል እናውቃለን፤ ሆኖም  ዛሬም ሰዎች ለእግዚአብሔር ያለን ታዛዥነትና ታማኝነት ዝቅተኛ በመሆኑ ከክፉው መንፈስ ጫና ነፃ መሆን እንዳልቻልን ገሐድ ሆኖ ይታያል፤ ከዚህም የተነሣ በየትኛውም የዓለም ዙርያ የሰላም መደፍረስ ሁኔታ ሲደርስ እናያለን፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ዓለም አካል እንደመሆኗ መጠን ከዚህ አላመለጠችም፤ በመሆኑም በዚህ ወቅት በክፉው መንፈስ ምክንያት የሰላም ሀብቷ ርቆ በዜጎችዋ መካከል አለመተማመን፣ ሥጋትና መጠራጠር ከዚያም አልፎ መገዳደል መፈናቀልና መዘራረፍ ወዘተ እየተበራከቱ፣ ሴቶችና ሕጻናት በሚያሳዝን ሁኔታ እየተንገላቱ፣ የሰቆቃ ኑሮ እየገፉ ናቸው፤ በውኑ እግዚአብሔር  በሚታወቅባትና በሚመለክባት በኢትዮጵያ ምድር እንደዚህ ያለ ችግር መከሠት ነበረበት ወይ? የሚለውን ጥያቄ ስናነሣ መልሱ ፍጹም መከሠት አልነበረበትም ነው፤  ምክንያቱም የእግዚአብሔር የሆነ ሕዝብ ይህንን ያደርጋል ተብሎ አይታሰብምና ነው፤አስተዋዩና አማኙ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን አሳፋሪ ድርጊት እንደሚጸየፈው እንጂ እንደማይቀበለው እናውቃለን፤ ይሁን እንጂ ጥቂቶቹስ ቢሆኑ ከዚህ ለመድረስ በቂ ምክንያት ነበራቸው ወይ? ቢባል አሳማኝ መልስ ይኖረዋል ብለን አናምንም፤ ምክንያቱም ጭካኔ፣ ግድያና መለያየት በምንም መመዘኛ አሳማኝ ሆኖ አይገኝምና ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

እስካሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ይህ ነው የሚባል የርስ በርስ ቅራኔ እንደሌለ ነው፤ ሕዝቡ አሁንም አንድነቱን ይወዳል፣ ሕዝቡ በሰላም፣ በወንድማማችነት በእኩልነት፣ በስምምነት፣ ተጋግዞና ተረዳድቶ በአንድነት መኖር ለድርድር የማይቀርብ ምርጫው ነው፤ ሕዝቡ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሰላም መረጋገጥ፣ በዜጎች እኩልነትና ሰብአዊ መብት መከበር የጸና አቋም እንዳለው ጥርጥር የለውም፤ የሀገራችን ሰላም ፈተና እያጋጠመው ያለ በፖለቲካ ኃይሎች ሽኩቻና አንዱ አንዱን ጥሎ ለማለፍ የሚደረገው ቅድድሞሽ ያስከተለው ችግር እንደሆነ አሌ የማይባል ሐቅ ነው፡፡

በመሆኑም ሀገራችን አሁን ከገጠማት የሰላም መደፍረስ አጣብቂኝ በአፋጣኝ ለመውጣት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሰፊ የውይይት መድረክ በመክፈት በሀገር አንድነት፣ በሰላም መጠበቅ፣ በዜጎች እኩልነትና ሰብአዊ መብት መከበር የጋራ አቋም በመያዝ ሰላምን ሊያረጋግጡ ይገባል፤ ሕዝቡም በተለይም ወጣቱ ትውልድ ተረጋግቶና ሰከን ብሎ በማሰብ ወገንን ከመተናኮል፣ ከማፈናቀል፣ ከማሳደድና መንገዶችን ከመዝጋት ሊቆጠብ ይገባል፡፡ ወጣት ልጆቻችን የነገ ሀገር ተረካቢ ባለአደራዎች ስለሆናችሁ ግሎባላይዜሽን ካመጣው የባህል ወረርሽኝ፣ ከሱስና ከአደንዛዣ ዕፅ ተጠብቃችሁ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሰላሟና ለልማቷ የተጋችሁ እንድትሆኑ በአጽንዖት እንመክራችኋለን፡፡

መንግሥትም የጀመረውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን የማስፈን በጎ ተግባር ለማጠናከር  ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በማሳተፍና በማወያየት የሀገሪቱን ሰላምና አንድነትን እንዲያረጋግጥ፣ የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር፣ እንደዚሁም የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ የሚያውኩ ድርጊቶችን እንዲያስተካክል በዚህ አጋጣሚ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

በ መ ጨ ረ ሻ ም

“ሰላም በምድር ሁሉ ይሁን” እያልን የገናን በዓል ማክበር ብቻው በቂ ስላይደለ ለሰላም መስፈን የኛ ተሳትፎም ወሳኝ ሚና አለውና ሕዝቡ በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ወገንን ከማፈናቀልና ከማሳደድ ተቆጥባችሁ ለሀገር አንድነት፣ ለሰላም መጠበቅና ለሰው ልጅ መብት መከበር በአንድነት እንድትቆሙ፣ የፖለቲካ ኃይሎችም ችግሮችን ሁሉ በውይይትና በውይይት ብቻ በመፍታት ሀገሪቱንና ሕዝቡን በቅንነት ለማገልገል አጥብቃችሁ እንድትሠሩ በእግዚአብሔር ስም አደራ ጭምር አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የገና በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ታሕሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ