ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የዓብይ ጾም መግባትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ

በቤተክርስቲያንችን ቀኖናዊ ሥርዓተ እምነት መሠረት በጾምና በጸሎት ከምንዘክራቸውና ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ከምናስገዛበቸው አጽዋማት መካከል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ በአርዓያነት ያሳየን ጾመ ኢየሱስ ወይም ዓብይ ጾም አንዱ ነው፡፡

በዚሁ የገዳመ ቆሮንቶስ ጾም ወቅት የሰውን ልብ በእጅጉ የሚገዳደሩና ለውድቀትም የሚዳርጉ የኃጢአትና የበደል ምክንያቶች ሁሉ በክርስቶስ ባሕሪያዊ ገንዘብ በሆነው በኃይሉ ችሎት ከመንገዳቸው ወጥተዋል የሰይጣንም ሽንፈት ተረጋግጧል፡፡

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም ይህንን አስመልክተው በዛሬው ዕለት በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትና የተለያዩ የሚዲያ አካላት በተገኙበት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ሥፍራ ተስጥቶት በሰፊ አገልግሎትና ጸሎት የሚዘከረውን  ዓብይ ጾም አገልጋዮችና ምእመናን እንዴት አድርገው መጾምና ማገልገል እንዳለባቸው ሰፊና ጥልቅ መግለጫ  ከመስጠትም ባሻገር ዘመኑ የጭካኔና የመለያየት እየሆነ ስለመጣ ክፉውን ለማስታገስ፤ ተቋማዊም ሆነ ሀገራዊ ችግሮቻችን ለመፍታትና ወደ አንድነታችን ለመመለስ ብቸኛው መፍትሔ ጾምና ጸሎት በመሆኑ አብዝተን እንድንጸልና እንድንጾም እንዲሁም እጆቻችንን ለምጽዋት እንድንዘረጋ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላለፉ፡፡

የሀገረ ስብከቱ የሕትመትና ሚዲያ ክፍልም እየተቀበልነው ያለው ጾም ራሳችንን የምንገዛበት፤ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ የምናገኝበትና ከአምላካችንም ሆነ ከወገኖቻችን ጋር ያለንን መስተጋብራዊ ግንኙነት የምናጠናክርበት እንዲሆን እየተመኘን ቅዱስነታቸው  የተሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ጊዜ ሰጥታችሁ ሙሉውን ታነቡት ዘንድ ከታች ባለው ክፍል አስቀምጠናል፡፡

የምሕረት ጌታ የብርሃን አባት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ እስመ ኅሊናሁ ለነፍስትነ ፀሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ፤

      የሥጋችን አስተሳሰብ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ”(ሮሜ ፰፡፯)

እኛ ሰዎች ከሁለት ነገሮች የተገኘን ውሕድ ፍጥረቶች መሆናችን ከእግዚአብሔር ቃል በተጨማሪ በየዕለቱ የምናሳየው እርስ በርሱ የተቃረነ ድርጊት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፤

ከዚህ አኳያ ሰው ሁሉ ከአንድ ምንጭ የተገኘ በመሆኑ ከመንፈስና ከሥጋ የተገነባ ድንቅ ፍጡር ነው፤ ሥጋና መንፈስ በሰው ዘንድ በተዋሕዶ ይኑሩ እንጂ ፍጹም ስምምነት ያላቸው ነገሮች ግን አይደሉም፤ ይልቁንም በመካከላቸው ከባድ ተቃርኖ እንዳለ “እስመ መንፈስኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ ሥጋ ወሥጋኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ መንፈስ; መንፈስ ሥጋ የማይወደውን፣ ሥጋም መንፈስ የማይወደውን ይወዳል” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡

የሁለቱ ነገሮች ተቃርኖ በዚህ ብቻ የሚያበቃም አይደለም፤ ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ አበጋዝና የሚያስገኙት ውርስም አላቸው፤ የሥጋዊ ምኞት ምንጭ ዲያብሎስ ሲሆን በባሕርዩ ለእግዚአብሔር የማይገዛ ስለሆነ የእግዚአብሔር ጠላት ነው፤ ለተከታዮቹም ሞትን ያወርሳል፤ የመንፈሳዊ ምኞት ምንጭ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነውና በባሕርዩ ለእግዚአብሔር ታዛዥ; ተገዥና የዘላለም ሕይወትን የሚያወርስ ነው፤

ከዚህ አንጻር ሰው ለሥጋዊ ምኞቱ ተገዢና በሥጋዊ ፈቃድ ተሸናፊ በሆነ ጊዜ ለሥጋውና ለነፍሱ የሚተርፍ ጉዳትን እንደሚያከማች፣ በአንጻሩ ደግሞ ለመንፈሳዊ ምኞቱ ተገዢና ተባባሪ በሆነ ጊዜ ለሥጋውና ለነፍሱ የሚተርፍ ሀብተ ሕይወትን እንደሚያፈራ ዛሬም ግልፅ ሆኖ ይታወቃል፤ ለዚህም የቀዳማዊ አዳም ሥጋዊ ዝንባሌና መንበርከክ፣ የዳግማዊ አዳም (ክርስቶስ) መንፈሳዊ ምከታና ድል ማድረግ ተጨባጭ ማረጋገጫዎቻችን ናቸው፡፡

ቀዳማይ አዳም የዲያብሎስን ምክር ሰምቶ፤ ጣዕመ መብልዕን ሽቶ፣ ለፈቃደ ሥጋው አድልቶ፤ በራሱና በልጆቹ ነፍስና ሥጋ ላይ የሞት ውርስን አውርሶአል፤ ዳግማይ አዳም የተባለ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በተቃራኒው ጣዕመ መብልዕን ትቶ፣ በኃይለ መንፈስ ተዋግቶ ፣ የዲያብሎስን ፈተና በእግዚአብሔር ቃል መክቶ የአሸናፊነትና የዘላለማዊ ሕይወት ርስትን ለእኛ ለልጆቹ አውርሶአል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ የዚህ ዓለም ወዳጅ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ሲል ሜዳው ሸንተረሩ፣ ሣሩ ደንጊያው ወይም ከተማው ገጠሩ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም በዚህ ዐውደ ሐሳብ ዓለም ተብሎ የተገለፀው ፍሬ ሐሳብ እግዚአብሔርን የሚቃወም ማንኛውም ፈቃደ ሥጋ ነው፤ ይህ ዓይነቱ ፈቃደ ሥጋ ለእግዚአብሔር የማይገዛ ብቻ ሳይሆን ጠላትም ነው፤ በሰው ላይም ሞትን የሚያመጣ ነውና “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ” ተብሎ ተጻፈ

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

        በነገው ዕለት የምንጀምረው የጾም ሱባዔ ሁለት ዓላማ ያለው ነው፤ ይኸውም አንደኛው ጌታችን በመዋዕለ ጾሙ ፈቃደ ሥጋንና የእርሱ አበጋዝ የሆነው ዲያብሎስን በፈቃደ መንፈስ ድል ማድረጉን ለማሰብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሥራው ሁሉ እንድንመስለው ባስተማረን መሠረት እኛም  በኃይለ ጾም መሣሪያነት እየታገዝን እንደሱ ፈቃደ ሥጋንና ዲያብሎስን በመዋጋት የፈቃደ ነፍስ ልዕልናን ለማረጋገጥ ነው፤ ይህንም ውጊያ በድል ለማጠናቀቅ የሥጋ መሣሪዎችን ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊ ነው፤ ሥጋ ነፍስን የሚወጋባቸው የታወቁ መሣሪያዎች አሉት፤ ቅዱስ መጽሐፍ እነሱን እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጦአቸዋል፣

        ይኸውም­፡-

  • ዝሙት                    – ቊጣ      
  • ርኵሰት                    – አድመኛነት
  • መዳራት                    – መለያየት
  • ጣዖትን ማምለክ             – መናፍቅነት
  • ምዋርት                    – ምቀኝነት              
  • ጥል                       – መግደል
  • ክርክር                     – ስካር
  • ቅንዐት                     – ዘፋኝነትና ይህንን የሚመስል ሁሉ ይላል፤

በማያያዝም እንደነዚህ ያሉትን የሚያደርጉ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሎ ይደመድማል፡፡

      ዲያብሎስ እነዚህ የጥፋት መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ አዳምንና ሔዋንን ባሳተበት ስልት ሥጋችንን በማስጐምጀትና ጠቃሚ ነገሮች እንደሆኑ አስመስሎ እነሱን በኅሊናችን ውስጥ በማቀጣጠል ወደ መሥገርተ ሞት ወጥመዱ ይከተናል፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በየጊዜው የምንጾመው እነዚህ የሥጋና የዲያብሎስ የሆኑ መሣሪያዎችን የመንፈስ መሣሪያዎች በሆኑ፡-

  • በፍቅር፣                        – በቸርነት፣
  • በመንፈሳዊ ደስታ፣               – በእምነት፣
  • በሰላም፣                        – በበጎነት፣
  • በትዕግሥት፣
  • በየዋህነትና ራስን በመግዛት ለመሰባበርና ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

 ከላይ እንደ ተመለከትነው የመንፈስ ቅዱስና የዲያብሎስ መሣሪያዎች ምን ምን እንደሆኑ ተገንዝበናል፤ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በሀገራችን ያለውን የሁለቱ አሰላለፍ ምን እንደሚመስል ማስተዋሉ የሚከብድ አይሆንም፤ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ተጠቅሞ፣ የዲያብሎስ መሣሪያ የሆኑትን ጥሎ፣ የመንፈስ ፍሬዎች ወይም መሣሪዎች የሆኑትን አንግቦ፣ ፈቃደ ሥጋንና ዲያብሎስን ቢመክት ኖሮ አሁን እየሆነ ያለው ሁሉ አይከሠትም ነበር፤

ነገር ግን “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ፤ ሰው በተፈጥሮ አዋቂና ክቡር ሆኖ ሳለ በተሰጠው ዕድል መጠቀም አላወቀበትም” ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል እንደተገለፀው ያለመታደል ጉዳይ ሆኖ ሊሆን አልቻለም፤ ይሁንና ተወደደም ተጠላ በመጨረሻው ቀን ማለትም በጌታ ቀን ዲያብሎስና መሣሪያዎቹ በኃይለ መንፈስ መሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ከገጸ ምድር ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸው አይቀሬ መሆኑ ቅዱስ መጽሐፍ ስለሚነግረን እስከዚያውም ቢሆን በሚጠፋ ነገር ከምንጠፋፋ የማይጠፉትን የመንፈስ መሣሪያዎችን ጨብጠን በሕይወት መኖርን ምርጫችን ብናደርግ ከጥበበኞች ሁሉ የምንበልጥ ጥበበኞች እንሆናለን ፡፡

ለመጪው ሕይወት ብቻ ሳይሆን አሁን ላለንበት ጊዜያዊ ሕይወትም ቢሆን፡-

  • ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣
  • ከጥል ይልቅ ፍቅርን፣
  • ከቊጣ ይልቅ ትዕግሥትን፣
  • ከመናፍቅነት ይልቅ እምነትን፣
  • ከርኵሰት ይልቅ ቅድስናን፣
  • ከመግደል ይልቅ ማዳንን፣
  • ከአድመኝት ይልቅ ሰላምን፣
  • ከስካር ይልቅ ራስ መግዛትን፣
  • ከዘፋኝነት ይልቅ ዘምሮን እጅግ እንደሚበልጥ ሁላችንም እንስማማበታለን፤ ነገሩ እውነትና ዘላቂ ሐቅ ስለመሆኑ ከስምምነታችን የበለጠ ማስረጃ ሊገኝ አይችልም፤ ስለሆነም በዚህ የጾም ወቅት እነዚህን ለመተግበር ክርስቲያኖች በቀንም፣ በሌሊትም ሊተጉ ይገባል፡፡

በመጨረሻም

መዋዕለ ጾም ማለት ፈቃደ ሥጋን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን ለፈቃደ ነፍሳችን ብቻ የምንታዘዝበት፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ብቻ እየሰማን ለእርሱ  የምንገዛበት ጊዜ ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅም ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መሆኑን ተገንዝበን ከሁሉ በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ነዳያን ወንድሞቻችንን  በመመገብና በማልበስ ሁሌ ከጎናቸው ሳንለይ ወርኃ ጾሙን እንድናሳልፍ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ወርኃ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው

በሰላም ያድርሰን

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

 ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የካቲት ፳5 ቀን ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ