“ቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን መንፈሳዊ ሐላፊነትና አደራ ሁላችንም እጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ እንደምንወጣ ተስፋ አደርጋለሁ” ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ
“ቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን መንፈሳዊ ሐላፊነትና አደራ ሁላችንም እጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ እንደምንወጣ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተናገሩ።
በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ወደ ሀገረ ስብከቱ መግባታቸውን አስመልክቶ የእንኳን ደህና መጡ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ሌሎች በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ መጋቢ ተአምራት የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ ሐላፊዎችና ሠራተኞች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ጅማሬ መጋቤ ሃይማኖት አባ አብርሃም ገረመው የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ጸሐፊ የብፁዕነታቸውን የሹመትና የአደራ ደብዳቤን ያነበቡ ሲሆን ቀጥሎም ጸሎተ ወንጌልና ኪዳን ደርሷል እንዲሁም በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቱ ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል።
በመቀጠልም በመጋቤ ምሥጢር አፈወርቅ ተክሌ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ና በመምህር አባ ክነፈ ርግብ የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል አገልጋይ ቅኔያት ቀርበዋል።
የእንኳን ደህና መጡ ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ሁኔታ ምን እንደሚመስል አጭር ገለጻ አድርገዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም በሀገረ ስብከቱ ያሉትን መልካም ዕድሎች ያብራሩ ሲሆን በተለይም ለመመራት ምች የሆኑ ምእመናን፣ ወጣት ሰንበት ተማሪዎች እንዲሁም ካህናት መኖራቸውን ጠቁመው ከከተማ አስተዳዳሩ እና ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ያለውን የመተባበርና የመደጋገፍ ሁኔታዎችንም በመልካምነት አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ይላሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሀገረ ስብከቱ ብዙ እጆች የሚበዙበት ፣ ከሁሉም አካባቢ የአገልጋዮች ፍልሰት ወደ ሀገረ ስብከቱ በመሆኑ ምክንያት ብቸኛ ሥራው መቅጠርና ማዛዋር ሆኗል ብለዋል ።
በመሆኑም ከዚህ አዙሪት ለመውጣትና የሚናፈቀውን ኦርቶዶክሳዊ ተልእኮ በአግባቡ ለማሳካት ይቻል ዘንድ በየገጠሩ ያሉ መምህራንና አገልጋዮች ካህናት ባሉበት ቦታ ተገቢውንና የሚገባቸውን በማድረግ ፍልሰቱን መቀነስና ያለውን በቂ የሰው ኃይል በተገቢው መልኩ በመጠቀም ሕያውን ተልእኮ ማሳካት እንደሚቻል ተጠቁመዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሐዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው በተደረገው ክብረ አበውን የጠበቀ አቀባበል ሀገረ ስብከቱን አመስግነዋል።
ብፁዕነታቸው ቀደም ሲል ከሊቀ ጵጵስ ማእረግ በፊት በነበራቸውን የአስተዳዳሪነት ሐላፊነት ወቅት ብዙ ብፁዓን አባቶችን መቀበላቸውንና ማሳለፋቸውን አስታውሰው በአሁኑ ጊዜ ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ ተረኛ ሊቀ ጳጳስ በመሆናቸው በተሰጣቸው ጊዜና ሐላፊነት የበኩላቸውን አገልግሎት ለማከናወን እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።
በዚህም ሐላፊነቱ የጋራ በመሆኑ “ቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን መንፈሳዊ ሐላፊነትና አደራ ሁላችንም እጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ እንደምንወጣ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
የመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሲዊዲንና የአካባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።” ፩ኛ ጴጥ ፪፥፭ በሚል ሕያው ቃል መነሻነት አባታዊ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ አምኖባቸው የሾማቸውን ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሕርያቆስን በማገዝና በመተባበር ዘመኑን የዋጀ ለቤተ ክርስቲያን ክብር የቆመ ተግባር ማከናወን ይገባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለው አንድ እጅ አያጨበጭብምና ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከታች ያለችሁት ተሿሚዎችና አገልጋዮች ከብፁዕነታቸውን ጋር በቤተ ክርስቲያናዊ ፍጹም ፍቅር፣ በዓላማ አንድነት አብራችሁ ከተጓዛችሁ እንዲሁም እናንተ እውነተኞች ከሆናችሁ ብፁዕነታቸው አይሳሳቱም ያሉ ሲሆን ለቤተ ክርስቲያን ክብር በመሸነፍ በሕያው እውነት በመታመን ነፍሳቸውን ከሚያድኑ ቤተ ክርስቲያናቸውን ከሚያተርፉ ወገኖች ልትሆኑ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ቡራኬና ጸሎት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ