ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ሀገር ጠቀምና ትውልድ ተኮር ሥራዎችን በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ

ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ሀገር ጠቀምና ትውልድ ተኮር ሥራዎችን በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በ 2017 ዓ.ም በነበረው የአገልግሎት አፈጻጸም ከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጋር በጋራ ሲሠሩ ለነበሩ ባለድርሻ አካላት የምስጋና መርሐ ግብር ነሐሴ 18 በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አከናወነ።
በምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና የሀዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ንጉስ ለወደደው እንዲህ ይደረግለታል በሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሠረት ዛሬ ለምስጋና የተመረጣችሁ የሥራ ሐላፊዎች እግዚአብሔር ስለወደዳችሁ ነው። ሙሴ እና አሮን ተባብረው ሲሠሩ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተቀጧል ። ዛሬም ቤተ ክህነቱ ከቤተ መንግሥቱ ጋር በትብብር መስራት መልካም ነው ።“ዚአከ ለዚአየ ዚአየ ለዚአከ” አንተ ለኔ እኔ ላንተ እየተባባልን አንዳችን ለአንዳችን ምሳሌ በመሆን በመተባበር በመነጋገር በመወያት በኅብረት ልንሠራ ልንተጋገዝ ያስፈልጋል ያኔ በጋራ ውጤታማ እንሆናለን። “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ለሀገርን ለዓለም ድኅነት ትጸልያለች ጸሎት ብቻም አይደለም በልማትም ትሳተፋለች ብለዋል።
ዛሬ ለምስጋና የተመረጣችሁ የመንግስት ኃላፊዎች ምስጋናው የተሰጣችሁ ኦርቶዶክሳዊ ስለሆኑ ብቻ አይደለም ስለሠራችሁት መልካም ስራ ነው። ሰው የሚመሰገነው በሠራው ሥራ ልክ ነው ከዚህ የበለጠ የምትሰሩበትን እድሜ ከጤና ጋር እግዚአብሔር ያድልልን ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በምስጋና መርሐግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሴን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱና የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች እና የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች ተገኝተውበታል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በ 2017 ዓ.ም ከይዞታ መረጋገጫ እና ከጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ጋር በተያያዘ ከቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን መሠራቱ የሚታወስ ነው ።