ቤተ መዛክርት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ማዕከል ብቻ ሳትሆን የምጣኔ ሀብታዊ፤ማህበራዊ፤ሥነ ጥበባዊ፤የሥልጣኔ እና የነገሥታት ገድሎች ዜና መዋዕሎች መረጃ መዕክል ናት፡፡ለምሳሌ ያህል ፡-የኩሱም፤ላሊበላ፤ደብረ ብርሃን ሥላሴ ፤ጣና ሀይቅ እና  የመሳሉትን ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል፡፡በአዲስ አበባም ታሪካዊና አስደናቁ የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች በብዛት የገኛሉ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉም ታሪካዊ ሙዜሞች ቢሆኑም ሙዜዬም  ሠርተው በሙዜየም ደረጃ ከሚያስጎበኙ ገዳማትና አድባራት መካከል፡-

 

  1. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሙዜም፤
  2. የገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ ሙዜም፤
  3. የርዕስ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ማርያም ቤ/ክ ሙዜም ፤
  4. የታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ቤ/ክ ሙዜምና ወዘተ መጥቀስ ይቻላል

በእነዚህ ሙዜሞች ወስጥ ደረጃቸውን በጠበቀ በዘመናዊ  አደረጃጀትና ጥበቃ ተይዘው በመጎብኘት ላይ ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ውድና ማራኪ የሆኑ ቅርሶች በዋጋ ሊተመኑና በምንም ሁኔታ ሊተኩ የማይችሉ ናቸው የተሰጡትም ከቀድሞ ነገሥታት፣ ከእቴጌዎቹ፣ ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ መንግሥት ልዑላንና ልዕልቶች፣ ከቀድሞ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖችና ከ5ቱ አኅት አቢያተ ክርስቲያናትም ጭምር ሲሆን ደኅንነታቸውም ለረጅም ዘመናት በሚባ ተጠብቆላቸው ከዚህ ትውልድ ደርሰዋል፡፡
የተሠሩትም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከመሳሰሉት ማዕድናት ሲሆን የወርቅና የብር ቅቦችንም ያጠቃልላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ የተዘጋጁ የቤተ መቅደስ አልባሳት፣ ድባብ ጥላዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይልቁንም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ጸሐፍትና አርእስት በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ ሃይማኖታዊ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍትም በእነዚህ ሙዜሞች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በ6ኛው መ/ክፍለ ዘመን በቅ/ያሬድ በ8 የዜማ ምልክቶችና በ3 የዜማ ቅኝቶች ከተደረሱት አምስቱ የዜማ መጻሕፍት ውስጥ አንዱና ከ5ዐዐ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆረጠው ድጓ ተብሎ የሚታወቀው መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በጣዕመ ዜማው በእጅጉ ከሚመስጡትና ከሚያስደንቁት ዋነኛው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከእነዚህ ከ3ቱ ቅኝቶች ውጭ የሆኑ የዜማ ስልቶች የሏትም አትጠቀምም፡፡ ቅኝቶቹም ዘመን የማይሽራቸው ጊዜ የማይገድባቸውና የማይሰለቹ ሰማያዊ ስጦታዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመንፈሳዊው ምንጭ የተቀዳ የራሷ የሆነ ፊደል፣ አኃዝ (ቁጥር)፣ ቀናትና አዝማናት መቁጠሪያ (ካላንደር) ያላት በመሆኗ ከሌላው የዓለም ክፍል ይልቅ በዚህ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበቧ የተለየች ያደርጋታል፡፡

የሙዚየሞቹ ዋና ዓላማ

 

  • ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የሆኑትን የቤተክርስቲያን ቅርሶች በሙዚየም ውስጥ በማደራጀት በልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ይዞ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጐብኝዎች በማስጐብኘት የቤተክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ገጽታ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ፣
  • እነዚሁ አስደናቂ ታሪኮችንና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በጥንቃቄ ጠብቆ በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል በየክፍላቸው መድበን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1ኛ. ከታሪካዊ ቅርሶች

 

  • የነገሠታቱ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ዙፋኖች፣
  • የነገሥታቱ የአርበኝነት አልባሳት፣
  • በሞዛይክ ቅርፅ የተዘጋጀ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ምስል (ፖርትሬት) እና ሌሎችም፣ 

2ኛ. ከሃይማኖታዊ ቅርሶች

 

  • በተለያየ ዲዛይን የተሠሩ መስቀሎች፣
  • ልዩ ልዩ ጽዋዎችና ጻሕሎች ከነእርፈ መስቀሎታቸው፣
  • የተለያዩ ወርቀ ዘቦና የብር ጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ ካባዎችና ድባብ ጥላዎች፣
  • የተለያዩ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍት ገበታቸው በወርቅና በብር የተለበጡ ጭምር፣
  • ከዕንቀ፣ ከብርና ከሞዛይክ የተሠሩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ ሥነ-ስቅለትና የመሳሰሉት ይገኛሉ፣

የሰጭዎቹም ዘርዝር

 

  • ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ከሌሎችም አባቶች፣
  • ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣
  • ከቀ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣
  • ከንግሥት ዘውዲቱ፣
  • ከእቴጌ ጣይቱ፣
  • ከእቴጌ መነን፣
  • ከልዑላትና ከልዕልቶቹ፣
  • ከቀድሞ ቤተ መነግሥት ባለሥልጣናት፣
  • ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖች፣
  • ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌላም

እነዚህ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይልቁንም ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቱሪዝም ሴክተሩ እንቅስቃሴ ቢጠቀምባቸው በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል እንላለን፡፡ሙሉውን መረጃ ለማግኘት መጥታችሁ ትጐበኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በአክብሮት ትጋብዛችኋለች፡፡