ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ “የአብነት ትምህርት ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ትምህርት” በሚል መሪ መልእክት ዐውደ ጥናት አካሔደ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ “የአብነት ትምህርት ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ትምህርት” በሚል መሪ መልእክት ዐውደ ጥናት አካሂዷል።
በዐውደ ጥናቱ የግዕዝ ቋንቋ ጥናት ለኢትዮጵያ የዕውቀት እና የምርምር ዘርፍ ስላበረከተው አስተዋጽኦ በዘርፉ ታዋቂ ምሁራን የጥናት ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ሙሉቀን አንዱዓለም (ዶ.ር) ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ የግዕዝ ቋንቋን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የሦሥተኛ ዲግሪ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዓለም ላይ በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግዕዝን እያስተማሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ ዓለም ላይ ግዕዝን የሚያስተምሩ ቁጥራቸው 31 የሚደርሱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መመልከታቸውንም አንስተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉትም በምክንያት መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ግዕዝን የሚማሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ሀገር ዜጎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ ቁጥራቸው ጥቂት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ ግዕዝን እንደሚያስተምሩ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ብዙ ታሪኮች ቢኖራትም በትክክል አልተጠናችም ነው ያሉት። ስለ ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገሮች አጥንተው ከሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ግዕዝን በመማር ታሪክን በማንበብ እና በመመርመር ማንነቷን ሊናገሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድ ግዕዝን በመማር ይህን እንዲረዳ እና እንዲነቃ ለማድረግ ዐውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ የራስን ቋንቋ መማር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በግዕዝ ቋንቋ ትልልቅ መጽሐፎች መጻፋቸውን ነው የተናገሩት። እነዚህን ጥንታዊ መጽሐፍትን ለመረዳት እና ለመመርመር የግዕዝ ቋንቋ መማር አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል።
አሁን ላይ ያለው ትውልድ ግዕዝን በመማር የሀገር እና የአባቶችን ታሪክ በማጥናት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባውም አንስተዋል።
ግዕዝ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ መኾኑንም ተናግረዋል። ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ዐውደ ጥናት ማዘጋጀቱ ሊቀጥል የሚገባ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።
በዐውደ ጥናቱ የማጠቃለያ መርሐ ግብርም “አብነት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት” በሚል ርዕስ በተለያዩ ምሁራን የተጻፋ ጥናታዊ ጽሐፎችን በማደራጀት የተዘጋጀ እና በመርሻ አለኸኝ (ዶ.ር) አርትኦት የተሠራለት መጽሐፍ ተመርቋል።
መረጃው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው።