በጸጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት የተገደሉት ሁለት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት በቦሌ ክፍለ ከተማ ሥር በሃያ ሁለት አካባቢ ቀበሌ ሃያ አራት ልዩ ስሙ አፍሮ ጽዮን አዋሳኝ በሚባለው ባዶ ሥፍራ ዙሪያ ለሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ተከታይ ምዕመናን ይሆን ዘንድ የአምልኮ ሥፍራ ማለትም ቤተ-ክርስቲያን ለመስራት በአካባቢው ምዕመናን ትብብር ጊዜያዊ መጠለያ ሠርተው በተቀመጡት አማንያንና ቦታው ለአረንጓዴ ልማት የተከለለ ነው በሚሉ የጸጥታ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት ሕግ ለማስከበር ጥር 27 ከሌሊቱ 7፤30 ላይ በተወሰደው እርምጃ ለሁለት ዜጎች መሞትና በደርዘን ለሚቆጠሩ ወገኖች ደግሞ መቁሰል ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህንን ግፍ የተሞላበትና ጨለማን ተገን አድርጎ በተወሰደው የመንግሥት የጸጥታ አካላት የግድያና የማቁሰል ድርጊት በከተማችን አዲስ አበባ በተሰማበት ወቅት ከቅዱስ ፓትርያሪኩ መግለጫ ጀምሮ በርካታ የእምነቱ ተከታይ ምዕመናንና ፖለቲከኞች እርምጃው መንግሥታዊ ኃላፊነት የጎደለው ከመሆኑም ባሻገር ቸልተኝነትና ማን አለብኝነት የታየበት እኩይ ተግባር ነው ሲሉ ተደምጠዋል ክስተቱንም አውግዘዋል፡፡
በዚሁ እኩይ ድርጊት የቆሰሉትን ወደ ህክምና ቦታ ከመውሰድ በዘለለ ለሞቱት ሁለት ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች ደግሞ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ብጹዓን አባቶችና በርካታ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ካህናትና ሊቃውንት እንዲሁም ለቁጥር የሚያዳግት ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ሥርዓተ ፍትሐት ተደርጎ ልብን በሚሰብር የሀዘን ድባብ በደማቅ ሁኔታ በገርጂ ምሥ/ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጸመ፡፡
በግፍ የተገደሉትንና በአካለ ሥጋ የተለዩትን ወንድሞች ለመሸኘትና ለመሰናበት የወጣው የእምነቱ ተከታይ ምዕመናን ኃይል የእግዚአብሔር፤ማዳን የእግዚአብሔር፤ጥበብ የእግዚአብሔር አንመካም በጉልበታችን በማለት በተፈጸመው ግፍ የተነሣ የተሰማቸውን ውስጣዊ ቁጭትና ቁጣ በመዝሙር ከመግለጻቸውም በላይ በቤተ-ክርስቲያኒቱና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን በደል የሀገሪቱ መንግሥት ችላ ማለቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳይተዋል፡፡
የሚዲያ ክፍላችን በሽኝት ሥርዓቱ ላይ የተገኙትን ኦርቶዶክሳውያን ባነጋገረበት ወቅትም መንግሥት እንደሚለው ምንም እንኳን ቦታው ለአረንጓዴ ልማት የተከለለ ቢሆንና መንግሥት ለራሱ መሠረተ ልማት ማስፈጸሚያ ቢያስከብረውም በሥራ አስፈጻሚዎቹ አማካኝነት ሕጉን ለማስከበር ጨለማን መከታ አድርጎ በጸጥታ አካላት በኩል የወሰደው እርምጃ ግን ፈጽሞ ዜጎችን እጠብቃለሁ፤ የሕግ የበላይነትንም አስከብራለሁ፤ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ በውይይት እፈታለሁ ከሚለው የለውጥ ኃይል የማይጠበቅ የማን አለብኝነትና ቸልተኝት ስሜት ከማሳየቱም ባሻገር ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ መሆኑን አውሰተው ከዚህ አረመኒያዊ ድርጊት ይልቅ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት ጋር መወያየትና ለጉዳዩ ዕልባት መስጠት ይቻል ነበር ካሉ በኋላ በሌላ መልኩ ደግሞ የቤተ-ክርስቲያናችን የበላይ መሪዎችም በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን በየጊዜው እያዩና እየተነጋገሩ ሕግና ሥርዓት በሚፈቅደው መልኩ ከመፍታት ይልቅ ዘመኑን የማይዋጅ አሠራር መከተል፤ በለዘብተኝነት መንፈስ መጠመድ፤ መንፈሳዊውን አደራ ጠብቆ መንጋውን ከመሰብሰብና ከማስተማር ይልቅ ከመንጋው የሚገኘውን ገንዘብ እያሰቡ የዓላማ መሳት ውስጥ መግባታቸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚታዩ ወቅታዊና አፋጣኝ መልስ የሚያስፈልጋቸው አንገብጋቢ ችግሮች ሲሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ማነው? ለምንስ ይህ ሁሉ ዝምታ አስፈለገ? ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል በማለት ሐሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
የተከሰተውን ድርጊትና የቤተ ክርስቲያኒቱን ምዕመናን አስተያየት መነሻ ያደረገው ሚዲያ ክፍላችንም በመንግሥት የጸጥታ አካላት የተፈጸመው ድርጊት እኩይ ከመሆኑም በዘለለ መንግሥት ለዜጎቹ ያለውን ጥበቃ ጥርጣሬ ላይ የጣለ፤ከሃይማኖት ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት የጀመረውን ጠንካራ ግንኙነት የሚያጠለሽና ሆድና ጀርባ የሚያደርግ አጸያፊ ድርጊት መሆኑን ተገንዝቦ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሥራ አስፈጻሚዎቹ ጋር ቁጭ ብሎ ጥፋቱን ሊገመግምና የጥፋቱ ተሳታፊ አካላቱንም በሕግ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚገባ ሲሆን በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ከአዳዲስ አብያተ ክርቲያናት ተከላና ማስፋፋት ጋር ተያይዞ ያሉትን በርካታና ውስብስብ ችግሮች ቁጭ ብሎ ሊመክርበት፤ የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግ በጠበቀ መልኩ ገዥ የሆኑ ሕጎችንም አውጥቶ ሊተገብር አዳዲስ አብያተ-ክርስቲያናት ሲመሠረቱም ከግለሰባዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ተቋማዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲመሠረቱ ሊያደርግ ይገባል፡፡
እግዚአብሔር ለተጎዱት መጽናናትን ይስጥልን!!!
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ