“በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል”
በመምህር ሣህሉ አድማሱ
በዐቢይ ጾም ከሚታሰቡት የሳምንታት በዓላት መካከል በ6ኛው ሳምንት የሚታሰበው በዓል ገብርሔር ይባላል፡፡ በዚህ በዓል ወቅት ማለትም ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ በሌሊቱ ስብሐተ እግዚአብሔር (ምስጋና) “ገብርሔር ወገብር ምዕመን ዘበሑድ ምዕመነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እስይመከ ባዕ ውስተ ፍስሓሁ ለእግዚእከ” የሚለው ያሬዳዊ መዝሙር በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይቀርባል፡፡
በጧቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት በዲያቆናትና በቀሳውስት፡ መልእክታት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የዳዊት መዝሙርና ወንጌል በንባብና በዜማ ይቀርባል፡፡ ከላይ እንደተገለፀው በዚህ ወቅት የሚቀርቡት መልእክታት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የዳዊት መዝሙርና ወንጌል እንደሚከተለው ተገልጾዋል፡፡ 2ኛ ጢሞ. 2÷1-16፣ 1ጴጥ. 5÷1-12፣ የሐዋ. 1÷1-9 (መዝ. 39÷8) ማቴ. 25÷14-30 ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች መካከል በዳዊት መዝሙርና በማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡ “ከመእንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፤ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ ÷ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡” አምላኬ ሆይ ፈቃደህን ለማድረግ ወደድሁ ÷ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፡፡
በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራለሁ (መዝ. 39÷8) እግዚአብሔር ሊአየው የሚፈልገው ከእምነት የሆነ መታዘዝና ፈቃዱን ማድረግ፣ ደስ የሚለውን እምነትና ሕጉንም በልቡ ውስጥ ለመሰወር ደስ የሚለውን እምነት ነው፡፡ የንጉሡ የዳዊት ሕይወት በምስጋና የተሞላና የእግዚብሔርን ታማኝነትና ምሕረት ዘወትር ለማወጅ መነሳሳቱን ያሳያል፡፡ ከላይ የተብራራው በዳዊት መዝሙር የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር ሲሆን በማቴዎስ ወንጌል 25÷14-30 የተጻፈው እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
“ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት፤ ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡ ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቈጣጠራቸው፡፡
አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታመነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡
ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍኩበት አለ፤ ጌታውም መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባርያ በጥቂቱም ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታ ደስታ ግባ አለው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ ጌታ ሆይ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት እነሆ መክሊትም አለህ አለ፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡
ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት፡፡ አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፡፡ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት በዚያ ለቅሶና ቅርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡”
ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ የክርስቶስን ዳግመኛ መምጣት ወደ ሌላ ሀገር በሚሄድ አንድ ሰው ይመስለዋል፡፡ በምሳሌ የተጠቀሰው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ልዩ ልዩ ስጦታ ሰጥቷል፡፡ እነዚህ ስጦታዎች ሥጋዊም መንፈሳዊም የተፈጥሮ ችሎታዎችና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ናቸው፡፡ (1ቆሮ. 12÷7) ያለን በጐ ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስለሆነ የራሳችን ነው ብለን የምንመጻደቅበት ምንም ነገር የለንም የራሳችን እንደሆነ የምናውቀው ነገር ቢኖር ኃጢአታችን ነው፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በችሎታቸው መጠንና መሠረት ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም አይነት ስጦታ ይስጠን እንድንጠቀምበት ይፈልጋል፡፡ መሬት ቢሰጠን ተግተን በመሥራት የምግብ እህል እንድናመርትበት ይፈልጋል፡፡ የማስተማር ስጦታ ቢሰጠን ወይም የመምራት ስጦታ ቢሰጠን በትጋትና በጥበብ እንድናስተምርና እንድንመራ ይፈልጋል፡፡ ሀብት ቢሰጠን በተቀደሰ አገልግሎት ላይ እንድናውለው ይፈልጋል፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዱ ሰው ሁሉ ያንኑ የተቀበለውን መልስ እንዲሰጠው አይጠብቅም፡፡ (ማር. 4÷20) የምንችለውን ያህል ሠርተንና አትርፈን እንድንመልስለት ይጠብቃል፡፡ በተለይም ከእኛ ከልጆቹ ፍቅራችንን፣ እምነታችንን፣ መታዘዛችንን እና ታማኝነታችንን ይጠብቃል፡፡ በተሰጣቸው የችሎታ ስጦታ በሚገባ የተጠቀሙ አገልጋዮች ተሸልመዋል፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በምድር ላይ በትንሽ ነገር ታማኞች ሆነው በመገኘታቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊው ክብር ይሾማቸዋል፡፡
ክፉውና ሰነፉ አገልጋይ በመጨረሻው ቀን የራሱን ገንዘብ እንኳን ማስቀረት አልቻለም፡፡ ይልቁንም ተወሰደበት፡፡ ላለውም ተጨምሮ ተሰጠው፡፡ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ እያለን በመንፈሳዊና በሥጋዊ በረከቶቻችን የማንጠቀም ከሆነ ከእኛ ላይ ይወስድብናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን የምናሳዝን ከሆነ ከእኛ ተለይቶን ይሄዳል፡፡ በእግዚአብሔር ስጦታ የምንጠቀም ከሆነ እርሱ አብዝቶ ይሰጠናል፡፡ የተሰጠንን ስጦታ የምንደብቅና ለራሳችን ፍላጐት የምናውለው ከሆነ የስጦታው ባለቤት እግዚአብሔር መልሶ ይወስድብናል፡፡ የእግዚአብሔርን ስጦታ አላግባብ የሚጠቀም ሰው ቅጣቱም ከባድ እንደሚሆን ከታሪኩ መረዳት እንችላለን፡፡